Sunday, April 26, 2015

ኢትዮጵያዊያንን በሐዘንና በቁጭት ያንገበገበ = አሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን ገደለ

ኢትዮጵያዊያንን በሐዘንና በቁጭት ያንገበገበ ሳምንት = የሟች ቤተሰቦች ሐዘን ተቀምጠዋል – በኢንተርኔት ፎቶና ቪዲዮ አይተው


በሊቢያ የአሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ታጣቂዎች፣ ’30 ኢትዮጵያዊያን ክርስትያኖችን ገድለናል’ ብለው በቪዲዮ የተቀረፀ አሰቃቂ የጭካኔ ግድያ ያሰራጩት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነው። በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በደረሰው ዘረኛ ጥቃት ማግስት፣ በሊቢያ ሲቪል ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የተፈፀመው የአሸባሪ ቡድን ዘግናኝ ግድያ፤ የኢትዮጵያውያን ሐዘንና ቁጭት አክብዶታል።
በኢንተርኔት የተሰራጨው ቪዲዮና ፎቶ፣ የሟቾቹን ማንነት ወዲያውኑ ለማወቅና ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ለብዙዎች አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ለቤተሰቦች ግን አጠራጣሪ አልነበረም። ወላጆችና ቤተሰብ፣ ወንድምና እህት፣ ጎረቤትና ወዳጆች ሁሉ ውስጥን በሚያደማ ቅፅበታዊ ሐዘን ነው የተመቱት።
በአዲስ አበባ የኢያሱ ይኩኖአምላክ እና የባልቻ በለጠ ቤተሰቦች ድንገተኛ መርዶ የደረሳቸው እሁድ እለት ነው። በሰላሳዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩት ኢያሱና ባልቻ በአንድ ሰፈር ውስጥ ያደጉ ጎረቤታሞች ናቸው – በቀድሞው ወረዳ 21 ቀበሌ 25፤ በአሁኑ ወረዳ 10። የሟቾቹ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት አጠገብ ለአጠገብ ስለሆነ ለቅሶውም አንድ ላይ ነው፡፡
ኢያሱና ባልቻ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ወደ ሊቢያ የሄዱት አንድ ላይ እንደሆነ የገለፀልን የኢያሱ ወንድም፤ የሊቢያውን የግድያ ወሬ የሰማው እሁድ ዕለት ነው – ስልክ ተደውሎ። የደወለለት ሰው፣ “የናንተ ሰፈር ልጆች ሊታረዱ ሲሉ የሚያሳይ ፎቶ በፌስቡክ ተለጥፏል” ብሎ ሲነግረው፤ በደንጋጤ “እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀ። “የወንድሜን ስም ጨምሮ ነገረኝ፤ የወንድሜን ስም አያውቅም ነበር” ይላል የኢያሱ ወንድም።
“የኔ ፌስቡክ ስለማይሰራ ጓደኛዬ ጋር ሄጄ አየሁ። በደንብ ስላልታየኝ እንደገና ከምሽቱ አራት ሰአት ስንከፍት ወንድሜን ተንበርክኮ አየሁት። ባልቻን ደግሞ ቀይ ቱታ ካደረጉት መሀል ለየሁት፡፡ ለእናቴ ከመንገሬ በፊት ለሩቅ ዘመዶች ለመናገር እያሰብኩ እያለ እነሱ ቀድመው ሰምተው ለቅሶ ላይ አገኘኋቸው” ብሏል የኢያሱ ወንድም።
ኢያሱ ኳታር ሰርቶ የተወሰነ ገንዘብ ይዞ ስለመጣ የባልቻንም ወጪ ሸፍኖለት ነው አብረው የሄዱት። ከኢትዮጵያ ወጥተው በሱዳን ጉዞ የጀመሩት ከሁለት ወር በፊት ነው። “ሱዳን እያሉ በስልክ እንገናኝ ነበር። ገንዘብ ሲያስፈልጋቸው እልክላቸው ነበር” የሚለው የኢያሱ ወንድም፤ “ወደ ሊቢያ ከተሻገሩ በኋላ ግን ስልክ ቁጥር እሰጥሃለሁ ቢለኝም አንገናኝም ነበር” ብሏል

No comments:

Post a Comment