በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የግድያና የዝርፊያ ወንጀል ተፈፀመባቸው
- ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል
በደበብ አፍሪካ በሚገኙና በተለያየ የንግድ ስራ ላይ በተሰማሩ የውጪ ዜጎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ የዝርፊያ፣ የድብደባና የግድያ ወንጀል ሲፈፀም የቆየ ሲሆን ከሰሞኑም በኢትዮጵያውያንና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ላይ የጥቃትና የዘረፋ ወንጀል ተከናውኗል። በደርባን ከተማ በሀገሪቱ ስራ አጥ ወጣቶች የተካሄደው ይኼው የተቀናጀ ዝርፊያ ባለፈው ሰኞ ለአራት ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን ከሟቾቹ መካከልም አንድ ኢትዮጵያዊ እንደሚገኝበት የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል። ሮይተርስ በዚሁ ዘገባው ሟቹ ኢትዮጵያዊ ቤት ሰራሽ ቦምብ በሱቁ ላይ እንደተወረወረበት አስተውቋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ 50 ሚሊዮን የህዝብ ብዛት ያላት ደቡብ አፍሪካ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞችን ይዛለች። ከነዚህም ውስጥ ብዙዎቹ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ሲሆኑ ኢትዮጵያኖችን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን ተቀጥረው እንደዚሁም የሸቀጣሸጥ ሱቆችን ይዘው ይነግዳሉ።
ግድያውና የዝርፊያው መባባስ ያሳሰባቸው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በሀገሪቱ ህግን በማከበሩ ረገድ ፖሊስ እንደዚሁም የሀገር ውሰጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንት ዙማ በዚሁ ንግግራቸው ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ለመስጠት ህገ ወጥ ንግድ እንዲቆም፣ እንደዚሁም በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ገብተው በተለያዩ ስራ ላይ የተሰማሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ለፖሊስ በማመልከት በህጋዊ መንገድ ወደ የሀገሮቻቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል። ዙማ በደቡብ አፍሪካ ያሉ በርካታ ስደተኞች ከተቻለ በፈቃዳቸው ካልሆነ በፖሊስ እየታደኑ ወደ መጡበት እንዲመለሱ በተለያየ አቅጣጫ ግፊት እየተደረገባቸው በመሆኑ፤ ፖሊስ ወደዚህ እርምጃ የሚገባ ከሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። ጥቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመሄዱ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞች ከለላ ፍለጋ በስደተኞች መጠለያ ለመሰባሰብ የተገደዱ ሲሆን ስደተኞቹን ባሉበት በመርዳቱ ረገድ የተባበሩት መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛ እንዲያደርጉ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጥሪ ያቀረበ መሆኑን በሀገሪቱ የሚታተመው ሲቲ ፕሬስ ጋዜጣ በዘገባው አትቷል።
ጋዜጣው ማክሰኞ እለት ባሰራጨው ዘገባ ዘረፋው ተባብሶ በመቀጠሉ መንግስት ልዩ የፖሊስ ሀይል በደርባን ከተማ ለማሰማራት የተገደደ መሆኑን አመልክቷል። ሜል ጋርዲያን አፍሪካ ድረገፅ በበኩሉ ባፈው አርብ በደርባን በተነሳ ዝርፊያና አመፅ ሁለት ኢትዮጵያውያን በሱቃቸው ውስጥ እንዳሉ በተጣለባቸው ቤት ሰራሽ ቦምብ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ለመግባት ተገደዋል። የደቡብ አፍሪካ መንግስት ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው በመመለስ የዜጎቹን የስራ እድል ለማስፋት በተደጋጋሚ ቃል በመግባት ላይ ሲሆን ይህ የመንግስት ቃል ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። መንግስት አመፁ ከተነሳባት ደርባን ከተማ ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል እንዳይስፋፋ ስጋት ስላደረበት የፀጥታ ኃይሉን በማጠናከር ላይ ነው።
Wednesday, 15 April 2015 14:01
በፀጋው መላኩ የፅሁፍ መጠ Sendeqe news paper
No comments:
Post a Comment