በኢትዮጵያ በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችና የተከተለው ቀውስ ምክንያቱ ሕወሃት በመሆኑ ይህን ቡድን ከማስወገድ ውጭ መፍትሄ እንደማይኖር አርበኞች ግንቦት 7 አስታወቀ።
የሕወሃት የስልጣን ዘመን እያበቃ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኦህዴድና ብአዴን ውስጥ ያሉ እውነታውን የተገነዘቡ ወገኖች በመጨረሻው ሰአት ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ስራ እንዲሰሩም አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ አቅርቧል።
የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስመልከት አርበኞች ግንቦት 7 በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው በዚህ መግለጫ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል አዋሳኝን መሰረት አድርጎ እየተከተለ ያለው ግድያና መፈናቀል አሳሳቢ እንደሆነ በመጥቀስ ድርጊቱ ግን ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ባስታጠቃቸው ሃይሎች የሚከወን መሆኑን አመልክቷል።
መታወቂያ እየተጠየቁና ብሔር እየታየ የተፈጸመው ድርጊት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደንጋጭ የማስጠንቀቂያ ደወል መሆኑንም በመግለጫው አስፍሯል።
በዚያው በምስራቅ ኢትዮጵያ በሀረሪ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የተከሰተው ሁኔታ አሳሳቢና ለነዋሪው አደጋ የደቀነ መሆኑን የዘረዘረው መግለጫ ህወሃት በሰሜን ኢትዮጵያ ጎንደር ውስጥ በጭልጋ፣በመተማና በሽንፋ ከፍተኛ የሰራዊት ሃይል ማስፈሩንና ይህ ሃይል በሕዝብ ላይ ጥቃት ለመክፈት የተዘጋጀና ትዕዛዝ የሚጠብቅ እንደሆነም ገልጿል።
በጠገዴ አካባቢ በሕወሃትና ብአዴን መካከል የተደረገው ስምምነት ብአዴኖች የሕወሃት አገልጋይነታቸውን ይበልጥ ያረጋገጡበት እንደሆነ መግለጫው አስታውሷል።
ሰሜን ጎንደርን በሶስት ለመክፈል የተያዘው እቅድ የደቀነውንም አደጋ አመልክቷል።
በአካባቢው እየተወሰደ ያለው ርምጃ ሕወሃት አማራን በአጠቃላይ ጎንደርን በተለይ ለማዳከም ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን እንደሚያሳይም መግለጫው አስታውቋል።
በአጠቃላይ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች ሕወሃት ሰራሾች በመሆናቸው ሕወሃት ሳይወገድ መፍትሄ እንደማያገኙ አርበኞች ግንቦት 7 አስታውቋል።
በመላው የኢትዮጵያ ክፍል ከሕዝብ ጋር ሆኖ ጸረ ሕወሃት የሕዝብ ትግል እያስተባበረ መሆኑንም በመግለጽ ትግሉ ፍሬ እንደሚያፈራም ጥርጥር እንደሌለው አመልክቷል።ለተቃዋሚ ሃይላትም የትብብር ጥሪ አቅርቧል።