በሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ታስረው የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ ከእስር ተለቀቁ።
አቃቢ ሕግ ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ ኣንዲለቀቁ ያደረገው በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ እመሰክራለሁ በማለታቸው እንደሆነ ጉዳዩን ለሚከታተለው ችሎት ገልጿል።
ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 የስኳር ፕሮጀክት ለዚሁ ተብሎ የተመደበውን በጀት ተቀናሽ በማድረግ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል በሌብነት ተጠርጥረው መያዛቸው ይታወቃል።
ያጎደሉትም ከ2 መቶ 50 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑ በወቅቱ ተነግሮ ነበር።
በዛሬው ችሎት ግን ጄኔራሉ በሌሎች ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ በመሆናቸው ነጻ ተደርገዋል ተብሏል።
ፍርድ ቤቱም የጄኔራሉን በነጻ መለቀቅ አልተቃወመም።ጄኔራል ኤፍሬም ከኦህዴድ የተገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው።
እርሳቸው በወቅቱ ሲታሰሩ ከሕወሃት ወገን በሌብነት የሚታወቁ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይያዙ ለምን በኦህዴድ ላይ እስራቱ አነጣጠረ የሚል ጥያቄ ፈጥሮ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀድሞው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዛይድ ወልደገብርኤል የክስ መዝገብ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ በነበሩት አቶ ሳምሶን ወንድሙና ሌሎች 3 ተጠርጣሪዎች አቃቢ ሕግ ክስ መመስረት አለመቻሉ ተነግሯል።
እናም አቶ ካሳዬ ካቻ የተባሉና በዚሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ግለሰብ በ20 ሺ ብር ዋስ ሲለቀቁ የአቶ ሳምሶን ወንድሙ ጉዳይና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ለነገ ተቀጥረዋል።
በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ 16ኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ ኪዳን አባቡልቃም በነጻ ተሰናብተዋል።
No comments:
Post a Comment