በጅንካና በተለያዩ የዞኑ ከተሞች የሚገኙ ነጋዴዎች በዘፈቀደ የተጣለውን ግብር አንከፍልም በሚለው አቋማቸው መጽናታቸውን የአካባቢው ነጋዴዎች ገልጸዋል። የዞኑ መሪዎች ፣ የነጋዴዎች ማህበር አመራሮችን በመጥራት ነጋዴዎችን እንዲያሳምኑ ቢማጸኑም የማህበሩ አመራሮች ግን “ በማናውቀው መንገድ የተጣለውን ግብር ለማስከፈል የማሳመን ስራ የመስራት ሃላፊነት ወይም ግዴታ የለብንም” በማለት መልስ ሰጥተዋል። በነጋዴዎች ማህበር መልስ ያልተደሰተው አገዛዙ፣ ከነጋዴዎች መካከል የተወሰኑትን በመምረጥና ኮሚቴ በማቋቋም ፣ ነጋዴዎችን በተናጠል እየጠራ ለማግባባት ቢሞክርም አልተሳካለትም። አብዛኞቹ ነጋዴዎች፣ በአገዛዙ የተወከሉትን ነጋዴዎች “ አርፋችሁ ተቀመጡ” በማለት ማስጠንቀቂያ እየሰጣቸው ሲሆን፣ ቀደም ብለው ግብራቸውን የከፈሉ አንዳንድ ነጋዴዎች “አሁን አገዛዙ ግብር በግማሽ ቀንሻለሁ” ብሎ ሲናገር ሃፍረት እንደተሰማቸውና አንዳንዶችም አገዛዙ ባቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ ገብተው ሌሎችን ነጋዴዎች ለማሳመን ሲሞክሩ መታየታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዞኑ የሚታየው የኑሮ ውድነት እጅግ እየተባባሰ መምጣቱን ህዝቡን ስጋት ላይ ጥሎታል። ምንም እንኳ አካባቢው አርብቶ አደሮች የሚኖሩበትና እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦም በአንጻራዊ መልኩ በደህና ዋጋ የሚገኝበት አካባቢ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የዋጋ ንረት በታሪካችን አይተነው አናውቅም ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። የበሬ ዋጋ 15 ሺ ብር ፣ በግ 4 ሺ ብር እንዲሁም ዶሮ እስከ 380 ብር መሸጡትን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ስኳርና ዘይት ከገበያ ጠፍተዋል።
በሌላ በኩል በዘንድሮው አዲስ ዓመት የዋጋ ንረቱ በእጥፍ ጨመሩን እና የኑሮ ውድነቱ በሁለት አሃዝ ማደጉን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ከዓመት ዓመት የኑሮ ውድነት ከሚጨምርባቸው አገራት ተርታ በቀዳሚነት የምትሰለፈው ኢትዮጵያ በዘንድሮው አዲሱ 2010 ዓ.ም የአመት በዓል ገበያ የዋጋ ንረቱ ካለፈው ዓመት በእጥፍ መጨመሩን የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የገበያ ጥናት ሪፖርት አስታወቀ።
ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በአቃቂ ገበያ ከ1 ሽህ 700 እስከ 3 ሽህ 200 ብር የነበረው የበግ ዋጋ፣ በዘንድሮ በአል ዝቅተኛው 2 ሽህ 500 ብር ከፍተኛው ደግሞ 5 ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቷል። የፍየል ዋጋ በበኩሉ አምና ከ1 ሽህ 300 እስከ 4 ሺህ ብር የነበረው ዘንድሮ ከ2 ሺህ እስከ 7 ሽህ 500 ብር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናግረዋል።
የቁም ከብት የበሬ ዋጋ እንደየመጠኑ ከ12 ሺህ ብር እስከ 35 ሺህ ብር ዋጋ የሚገኝ ሲሆን ይህም ባለፈው አመት ከነበረው የበሬ ዋጋ ሲነጻጸር በአማካኝ እስከ 6 ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የበግ ዋጋም ባለፈው ዓመት ከ1 ሽህ 900 ብር እስከ 4 ሺህ ብር የነበረው ዘንድሮ ከ2 ሽህ 500 እስከ 7 ሺህ ብር ተሽጧል።
በአቃቂና በሣሪስ ገበያ አንድ ዶሮ ከ150 እስከ 450 ብር የሚሸጥ ሲሆን በመሿለኪያ አካባቢ ደግሞ ከ250 እስከ 500 ብር ተሽጧል። እንቁላል በአብዛኞቹ አካባቢዎች አንዱ በ3 ብር ከ50 ሳንቲም ሲሸጥ 1ኛ ደረጃ ቅቤ በኪሎ በሣሪስ ገበያ በ250 ብር ይሸጣል፡፡ የበርበሬ ዋጋ በዓሉ ከመድረሱ በፊት በኪሎ እስከ 180 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን በበዓሉ ሰሞኑን ወደ ከ220 ብር በላይ አሻቅቧል። አይብ በኪሎ 120 ብር የነበረ ሲሆን በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ 135 ብር መድረሱን ሸማቾች ይናገራሉ፡፡
በፒያሳ አትክልት ተራ ቲማቲም በኪሎ 18 እና 20 ብር፣ ቀይ ሽንኩርት16 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 55 ብር፣ ቃሪያ በኪሎ 40 ብር፣ ካሮት 24 ብር፣ ዝንጅብል በኪሎ 80 ብር፣ ድንች በኪሎ ሰባት ብር እየተሸጡ ነው። በአዲሱ ገበያ ገበሬ ነጋዴዎች እንደተናገሩት አንድ በሬ ከ11 ሺህ 200 ብር እስከ 40 ሺህ ይሸጣል፡፡
የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ጽ/ቤት በበኩሉ በመላው ኢትዮጵያ ያለው የኑሮ ውድነት በሁለት አሃዝ መጨመሩን አስታውቋል። የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት በሁለት አሃዝ ማሻቀቡ በዜጎች የኑሮ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት እየፈጠረ ነው። ገዥው ህወሃት ኢህአዴግ ባለ ሁለት አሃዝ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት አምጥቻለው ቢልም ኢትዮጵያዊያን ግን የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኗቸዋል።
No comments:
Post a Comment