Friday, September 22, 2017

09/18/17 ሰላም ለነጻነት አፍቃሪዎች ሁሉ እየተመኘሁ ከዚህ ቀጥዬ በአስመራ ስለነበረኝን ቆይታ ስሜቴን ለመግለጽና የተሰማኝን ለማካፈል ያህል ወደመጣሁበት ስመለስ መንገድ ላይ (በአይሮፕላን ውስጥ) የጻፍኩትን እንደ ልምድ ያለው ጸሃፊ ጽሁፍ ሳይሆን ስሜቱን ለመግለጽ እንደሞከረ አንድ ተራ ሰውና የግል አስተያየት ተረዱልኝ።

የአግ7 አንደኛ አጠቃላይ ጉባኤ ኤርትራ ውስጥ እንደሚደረግ ስሰማ እዛ ያሉትን ጓዶቻችንን በአካል ማግኘትና ስላለውም አጠቃላይ ሁኔታ በቅርበት ለማየት እድል ስለሚፈጥር ደስታ ተሰማኝ ለመሄድም አሰብኩ ነገር ግን እድሉን ማግኘት በመፈለግ ብቻ የሚሆን ስላልነበረና ለመሄድ የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ማሟላት ብቻ ሳይሆን መሄድ የሚፈልገው ከተሰጠን ኮታ በላይ ስለነበረ ውድድርም ይጠበቅብን ነበር፤ ለማንኛውም በመመሪያውም መሰረት የተጠየቀውን በማሟላቴና ለመሄድም ለውድድር ቀርበን ከሌሎች ጓዶቼ ጋር ስለተመረጥኩ ለመሄድ ዝግጅት ጀመርን በዚሁ አጋጣሚ የነበረው አጭር ግዜም ቢሆን በአስቸኳይ የድርጅታችን አባላቶች በመነጋገር ለዳር አገር ላሉት ጓዶቻችን የሚሆኑ ነገሮችን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ በማዋጣት፣ የማህበረ ኢትዮጽያ (የዲሲ ግብረ ሃይል) አባላትም የአቅማቸውን ገንዘብ በመስጠት እንዱሁም መሄዳችንን የሰሙ አገር ወዳዶች ይጠቅማል ያሉትን ሁሉ በመስጠት ላሳዩት ጓዳዊ ድጋፍ አርእያነታቸውን ሳላመሰግን አላልፍም። ወደ መንገዴ ልመለስና ለመሄድ እየተዘጋጀን እያለ ወሎ ሰፈር በመባል የሚታወቅ የፌስ ቡክ ገፅ የጉባዬተኞችን ስም ዝርዝር በሁለት ዙር በማውጣት ለማስፈራራት ይሁን መረጃ ይደርሰኛል ለማለት ፈልጎ ወይም ስማችንን በመለጠፉ ፈርተው ይቀራሉ ብለው አስበው ይሁን ባይገባኝም የለጠፉትን አይተንላቸው ነበር፤ እኛን ግን እንኳን ሃሳባችንን ሊያስቀይር ይቅርና እንደውም በእልህ ለመሄድ ተወዳዳሪዎችን አበዛብን እኔንም ስሜን አሳስተው በመፃፋቸው ቅር አሰኙኝ። ለማንኛውም ትግሉ ብዙ የሚጠይቅ መሆኑን አውቀን የገባንበት ስለሆነና ወያኔም የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ስለምንረዳ እነሱ በሚሰሩት ስራ የሚደናገጥ ሳይሆን የቆረጠና የማይፈራ የሚሰራውን ስራ ለምን እንደሚሰራ ጠንቅቆ የተረዳ አባላት ያሉት ድርጅት ውስጥ በመሳተፌ ደስ እያለኝ ዝግጅታችንን አጠናቀን ጉዟችንን ወደ ዳር አገር ለማቅናት(Sep 1st) ከወዳጅ ዘመድ ተሰነባብተን ከጓዶቼ ጋር በተቀጣርንበት ቦታ በግዜ ብንገኝም የያዝነው ቫን መኪና እቃ ከአሰብነው በላይ በመብዛቱና ሁሉንም መያዝ ባለመቻሉ መኪና መቀየር ግድ ሆነብን ወቅቱም የ (Labor Day) ሳምንት ስለነበር ሌላ መኪና ለማግኘት ትንሽ ግዜ ቢወስድብንም የምንፈልገውን ግን አገኘን፤ በቂ ግዜም ስለነበረን እንደርሳለን ብለን ጉዟችንን መነሻችን ወደሆነው የኒዮርኩ (JFK) አይሮፕላን ማረፊያ አደረግን ነገር ግን ለመሄድ እንደነበረን ጉጉት መንገዱ አልተባበረንም ነበርና በሰአቱ መድረስ አልቻልንም ነበር፤ በእለቱም ሌላ የነበረን አማራጭ ስለሌለ አድረን በቀጣዩ ቀን መንገዳችንን ለመሞከር እዛው ማደር ስለነበረብን በአካባቢው የሚገኙ ቤተሰቦቼ ጋር ለመሄድ መንገድ ስንጀምር በደህና ደረሳችሁ ለማለት ለአንደኛው ጓዳችን ባለቤቱ ስልክ ስትደውልለትና የሆነውን ሲያስረዳት የሰማ ሌላኛው ጓዳችን አንድ ቀልድ ልንግራችሁ ብሎ የነገረን ቀልድ ንዴታችንን አጥፍታ እየተሳሳቅን የምንሄድበት አደረሰን። ምን አለን መሰላችሁ " አንዲት የቅንቡርስ ባለቤት ባሏ ዘመቻ ሊሄድ ሲነሳ ድግስ ደግሳ ዘመድ ወዳጆቻቸውን ጠርታ በትልቁ ስንብት ተደርጎለት ይለያያሉ ባለቤትም ብቻዋን እንዳትሆን ዘመዶቿ ጋር ቆይታ ስትመጣ ዘማቹ ባለቤቷን ከሩቅ እቤታቸው ውስጥ ታየውና በድል ተመለሰ ብላ እልልታዋን ስትለቀው ባለቤቷም ኧረ ዝምበይ ዝምበይ ገና መቼ ሄድኩና አላት እሱ ለካ እዚያው ሲርመጠመጥ ቆይቶ ነበር ሲለን ከኛ ሁኔታ ጋር ስለተገጣጠመብን በጣም ነበር ያሳቀን" ለማንኛውም እንዲህ እንዲህ እያልን ደርሰን ግዚያችንን ከቤተሰብ ጋር አሳልፈን በንጋታው በድጋሚ እንዳያመልጠን በግዜ ወደ ኤርፓርት ሄደን ቅጣታችንን ተቀብለን ጉዞ ወደ ካይሮ አደረግን፤ ካይሮ ስንደርስ ወደ ኤርትራ የሚወስደንን አይሮፕላን ለመያዝ 12 ሰአት መጠበቅ ነበረብን ስለዚህ ሁሉ ለበጎ ነው እንዲሉ ፒራሚድን፣ የአባይ ወንዝን፣ ጣህሪር አደባባይን (Tahrir Square) ጨምሮ የተለያየ ቦታዎችን ጎብኝተን ያላሰብነውን አይተን ሰአታችን ሲደርስ ጉዞ ወደ መድረሻችን ወደሆነችው ኤርትራ ጀመርን፤ መድረስም አይቀር ከቤት ከወጣን በ4ተኛ ቀናችን በማታ አስመራ ደረስን።
አስመራም እንደደረስን ጥሩ አቀባበል ተደርጎልን ወደተያዘልን ታዋቂው ኒያላ ሆቴል አመራን (ሌሎች ሆቴሎችም ያረፉ አሉ)፤ በቆይታችንም የበአሉ ግርማን “ኦሮማይን” እያስታወስን በንጋታው ከተለያዩ አካባቢ ከመጡ ጓዶቻችን ጋር ተገናኘን በተጨማሪ ለአንድ ቀን የተቀሩ አባሎቻችንን እየጠበቅን ሁላችንም ለአርበኞቹ ከየአካባቢያችን ያመጣናቸውን እቃዎች ለድርጅቱ ጽ/ቤት አስረከብን። በቀጣዩም ቀን (Sep 6th) ተያይዘን ጉዞ ወደ ጉባኤው የሚደረግበት ቦታ ጀመርን በመንገዳችንም ላይ የይለፍ ችግር እንዳያጋጥመን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን አብሮን ይሄድ ነበር እንደአጋጣሚም የተቀመጥኩት ከሹፌሩ ጀርባ የመጀመሪያው መቀመጫ ከዳር ስለነበረ እሱም በሚቀጥለው ረድፍ በዳር ስለነበር ከሱጋር ለማውራት እድሉ አጋጥሞኝ ነበር፤ እኔን የገረመኝ በመንገዳችን ላይ በምናገኛቸው ኬላዎች ሁሉ ለሚሰሩ ሰዎች ያሳያቸው የነበረው ትህትና እንዲሁም እጠይቀው ለነበሩት ጥያቄዎች ያለመሰልቸት የሚሰጠኝን መልስ እየሰማሁ አስቸጋሪ የሆነውን "ልበ ትግሬ" የሚባልና ሌሎች ጠመዝማዛ መንገዶችን እያለፍን በታሪክ የማውቃቸውን ብዙ መስዋእትነት የተከፈለባቸውን እንደ ባረንቱ፣ ከረን ያሉ ቦታዎችን እያየሁ ምን አይነት አስቸጋሪ ጦርነት እንደነበር በአይነ ህሊናዬ እየቃኘሁ ከረጅም ጉዞ በኋላ ጉባኤው የሚካሄድበት ቦታ ደረስን፤ በቦታውም ስንደርስ እንደኛው ከየምድባቸው ተወክለው የመጡ የአርበኞቻችን ተወካዮች ደማቅ ወታደራዊ አቀባበል አደረጉልን መቼም በአይን ስንተያይ የነበረው ሁኔታ ለመግለፅ በጣም ያዳግታል በአጠቃላይ ስሜቱን መቆጣጠር የቻለ ነበር ለማለት ይቸግራል የአቀባበል ስነስርአቱንም የድርጅታችንን መዝሙር በመዘመር ጨርሰን ከወንድምና እህት ታጋይ ወገኖቻችን ጋር ተቃቅፈን እንደ ለረጅም ግዜ ተለያይቶ እንደተገናኘ ቤተሰብ እርስ በርስ ተቃቅፈን ስንተዋወቅ ቆይተን በመጨረሻ የመክፈቻ ዝግጅት ወደሚካሄድበት አዳራሽ በጋራ በመግባት የኤርትራ ባለስልጣናት እና የትህዲን መሪ በተገኙበት ስለ ነፃነት ሲሉ የተሰዉ ወገኖቻችንን በማሰብና ተወካዮችም ንግግር በማድረግ የጉባያችን የመክፈቻ ዝግጅት ተጀመረ፤ የተዘጋጀውንም እራት በአንድላይ ተመግበን ስንጨርስ ለዝግጅቱም ድምቀት አርቲስት ሻንበል በላይነህን ጨምሮ የድርጅቱ የኪነት ቡድን የተለያዩ አዝናኝ ዘፈኖችን በማቅረብ ታዳሚውን ሲያዝናኑት አመሹ። 
በቀጣዩ ቀን መደበኛው ጉባኤ በጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመመራት በድርጅቱ የሰራዊት አመራር ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት በሰራዊቱና በአመራሮቻችን የተደረገውን ጥረትና ችግሩም የተፈታበት ሁኔታና ችግሩም ላያዳግም መፈታቱን መገለጹ ምን ያህል አስተዋይ ሰራዊትና አመራሮች እንዳሉን ያመላከተንና ያኮራን አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን እየተካሄደ ያለውን ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመፍጠር ትግል ምን ያህል ብሩህና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ያሳየንና ለጉባኤ የሄዱ እህትና ወንድሞቻችን እዛው ከሰራዊቱ ጋር በመቅረት ትግሉን ለማካሄድ የቆረጡበትን ሁኔታ የፈጠረ በሰራዊቱ ውስጥም ከፍተኛ መነሳሳትን ያሳየ በአጠቃላይ አባላቱን የዚህ ድርጅት አባል በመሆናችን ያኮራንና በውጭ የምንቀሳቀሰውንም ምን ያህል ወደፊት ብዙስራ እንደሚጠበቅብን ያመላከተ በአጠቃላይ ትግላችን በአጭር ግዜ አመርቂ ውጤት ለማምጣት እንዲችል ሞራላችንን የገነባንበትና ቃል የገባንበት ሁኔታ የፈጠረ ነበር፤ በተጨማሪ የቀድሞው የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር አርበኛ መአዛው ጌጡ መልእክቱን ለታዳሚው በገለጸበት ወቅት ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ ከታዳሚው ያገኘበት ሲሆን ድርጊቱም ለሁላችንም ታሪካዊና ትምርታዊ ነበር፤ ጉባኤውም ያለ ውጪ አካላት ታዛቢነት ፕሮግራሙን በድርጅቱ መሪ አስተናባሪነት በመቀጠል ሲያካሂድ ቆይቶ የጉባኤው አባላት ከተለያዩ የስራ አስፈፃሚ እባላት የቀረበለትን ሪፖርት አድምጦ በመወያየት መሻሻል የሚገባውን በማሻሻል አስፋላጊ ነው ብሎ ያመነበትን በማፅደቅና በመጨረሻም አስመራጭ ኮሚቴ በመምረጥ ለቀጣዩ 3 አመታት ይሄንን ሀላፊነት ይወጡልኛል ብሎ ያመነባቸውን ወኪሎቹንና አመራሩን በመምረጥ ጉባኤውን (Sep 11th) በአዲስ አመት አዲስ ተስፋን ሰንቆ በመጨረስ አመት በአሉንም በጋራ አንድላይ በስኬት አክብረናል።

እዚህ ላይ በስብሰባው ግዜ አከራካሪ ጉዳዮች ቢነሱም በተለይ የሰራዊቱ ተወካዮች ያሳዩት የነበረው በሳልነት የተሞላው አስተያየት የሚገርም ነበር፤ ምንም እንኳን ከተለያየ አካባቢና የኑሮ ደረጃ የመጡም ቢሆን ንቃተ ህሊናቸው የዳበረ ነገሮችን አርቀው የሚያስቡ ከገመትኩት በላይ ነገሮችን ያየሁበት ነበር፤ በውጭም የሚናፈሱት ነገሮች አሉባልታዎች እንደሆኑ የተረዳንበት በአጠቃላይ በነበረን ግዜ ሁሉ ከነእርሱ የተረዳሁት ምን ያህል የነፃነት ትግሉን በአጭር ለመጨረስ በእነሱ በኩል ዝግጁ እንደሆኑና በአዲስ መንፈስ ትግሉን ለማካሄድ እንደተነሱ በጉባኤውና በውጤቱም በጣም ደስተኞች እንደሆኑ ስረዳ ከእኛ በኩል ደግሞ ምን ያህል ስራ መስራት እንዳለብን የተረዳሁበት ነበር፤ ስለዚህ እኛም ከአሁን በኋላ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል መቼም እድሉን አግኝታችሁ ለማየት ብትችሉ ምን ያህል ጥሩ ነበር፤ ምንም እንኳን በአካል ማየት እድሉ ባይኖራችሁም ግን በአጭር ግዜ ውስጥ አኩሪ ስራዎቻቸውን እንደምታዩ ግን አልጠራጠርም ሞራል ባላቸው በወጣቶች የተገነባ አኩሪ ሃይል እንዳለን ግን በልበ ሙሉነት መናገር እችላለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ከጉባኤው በኋላ በአስተናጋጅ ሃገሯ ኤርትራ በመቆየት ያየሁት ነገር ቢኖር ለእኛ ያላቸው ጥሩ አመለካከት በተለያየ ግዜ እሰማው ከነበረው እውነታ ወጣ ብሎ አግኝቼዋለሁ ብዙ ከሚባልለት ኮሎኔል ፍፁም ጀምሮ ብዙ የተዛቡ ነገሮችን አይቼና ሰምቼ በመምጣቴ ምን ያህል ወሬ (propaganda) ነገሮችን የማዛባት አቅም እንዳለው ለመረዳት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል፤ ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ነገሮች ከጠበኳቸው ውጭ የሆነብኝ። ማህበረሰቡ ለኛ ያለው መልካም አመለካከትና ትህትና ከጠበኩት በላይ ነበር በዚሁ አጋጣሚ የኤርትራን ህዝብና መንግስት ስላደረጉልን መስተንግዶ ሳላመሰግን አላልፍም ወደፊትም እርዳታቸው እንደማይለየን ተስፋ አደርጋለሁ። በሄድንበት ቦታ ሁሉ ዝቅተኛ ከሚባለው እስከ ከፍተኛ ቦታ ድረስ ያለ ምንም ችግር ስንዟዟር በመቆየታችን በተወሰነ መልኩ እውነታውን ለማየትና ለመስማት እድል ሰጥቶናል ምንም እንኳን የዲሞክራሲያዊ ስርአት አላቸው ባይባልም ማህበረሰቡ ያዳበረው ጥሩ ስነምግባር ግን የሚያስገርም ነው ከሳምንት በላይ በከተማ ውስጥ ስንቆይ እንድም ፓሊስ ወይም የታጠቀ ወታደር ሳናይ (ከተወሰኑ የትራፊክ ፓሊሶች ወይም ኬላ ከሚጠብቁ በስተቀር) ከርመናል፤ ሌላው ሌብነትና ጉበኝነት የመንግድ ላይ ፀብም እንዲሁ የማይታሰቡ ነገሮች ሁነው ነው ያገኘሁት ወንድ ሴቱ ቀን ከለሊት ብቻቸውን ያለስጋት ሲጓዙ ማየት የተለመደ ነገር ነው፤ የአማርኛ ዘፈኖችም የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲደመጡ ይሰማል። ሌላው አብዛኛው ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ችግር እንዳለበት ያስታውቃል ግን ምን አልባት የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የምግብና ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ችግር አላየሁም ገበያዎቹ ሁሉ የተሟላ ነግሮች አሏችው ከተሞቹ ያረጁ ቢሆኑም በእቅድ የተሰሩ እንደነበር ያስታውቃል ሌላው በጦርነቱ የፈራረሱት እስካሁን በዚያው ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ የጦርነትን አስከፊነት ለመረዳት ብዙ አያስቸግርም፤ ፍልፍል የሚባለውን አሰቃቂ ጠመዝማዛ መንገድ ይዘን ከአስመራ ወደ ምፅዋ ስንሄድም ያየነው ይሄንኑ ነበር ምፅዋም ከነሙቀቷ ምን ያህል እልቂት እንዳስተናገደች አሁን ድረስ የሚታይ እውነታ ነው ፈራርሶ የሚታየው የባህር ሀይል ግቢ እና አካባቢው ልብ የሚነካ ነገር ነው የቀይ ባህር ዳርቻ ንፁህና ጨዋማ ውሃውን ተንጣሎ ሲያዩት ልብን ያስደስታል ገብተንም መሬቱን እያየን ስንዋኝበት ልዩ ስሜትንና ትዝታን ጥሎብን አልፏል። እንግዲህ በአጭሩ በኔ እይታ ጉዟችን የተሳካና ይሄንን የሚመስል ነበር እላለሁ።
አንድነት ሃይል ነው!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ጣሰው (ከዲሲ)

No comments:

Post a Comment