በአዲስ አበባ የመብራትና የውሃ ችግር መባባሱ ተገለጸ።
በአብዛኛው የከተማዋ አካባቢዎች ውሃ ከጠፋ ቀናት መቆጠራቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥ መኖሩ ደግሞ ነዋሪዎቹን ለከፋ ችግር መዳረጉን ለማወቅ ተችሏል።
ከእነዚህ በተጨማሪ የነዳጅና የስኳር እጥረትም በከተማዋ በመከሰቱ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ነዋሪዎች በምሬት እየተናገሩ ነው።
በሌላ በኩል መንግስት ወደ ውጭ ስኳር በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ከገለጸ ከቀናት በኋላ 7ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲል ትላንት ማስታወቁ ሌላ ጥያቄን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ በድርቅ በተመታችበት በዚህን ወቅት ለኬኒያ በቆሎ መሸጧን የኬኒያ ንግድ ሚኒስቴር ገልጸዋል።
ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሁሉ ነገር ችግር ሆኖባቸዋል። የስልክ ኔትወርክ የለም። ስኳር ጠፍቷል። ውሃ ለቀናትና አንዳንድ ጊዜም ከሳምንት በላይ አያገኙም። የመብራት መቆራረጥም ሌላውና ከፍተኛው ችግር ነው። የነዳጅ እጥረትም ለነዋሪው ብርቱ ፈተናን መደቀኑ ነው የተሰማው።
የውጭ ምንዛሪ የለም። የንግድ እንቅስቃሴው ተዳክሟል። ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው ተብሏል።
ለኢሳት የሚደርሱ መልዕክቶች እንደሚያረጋግጡት በአዲስ አበባ የተከሰተው የውሃ እጥረት ከምንጊዜው በላይ የከፋ ነው። ለቀናት የሚጠፋው ውሃ ከሳምንት በላይ ቆይቶ የሚመጣ ሲሆን ንጽህናው የተጠበቀ ባለመሆኑም ለተለያዩ በሽታዎች መጋለጣቸውን ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
በከተማዋ ከመጠጥ ውሃ በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥ በመከሰቱ መቸገራቸውን የገለጹት ነዋሪዎች ከመብራት ጋር የተገናኘ የገቢ ምንጭ ያላቸው ደግሞ በመኖር ህልውናቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ አምጥቶባቸዋል።
የቀን ገቢ ግምት በዕለት በሚያገኙት ገቢ ላይ የሚተመን መሆኑን በማውሳት በመብራት መቆራረጥና መጥፋት ምክንያት ገቢያቸው በከፈተኛ መጠን በመቀነሱ ግብር ለመክፈል እንደማይችሉ ከወዲሁ ለሚመለከተው የመንግስት አካል እያሳሰቡ እንደሆነም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የከተማዋ ባለሃብቶች የመብራት እና የውሃ አቅርቦት እጥረት ስላጋጠማቸው ፋብሪካዎች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ መስጠት እንደተሳናቸውም ይነገራል።
ጥቂት የማይባሉ የከተማዋ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለኪሳራ እየተዳረጉ እንደሆነም ተገልጿል።
ባለሀብቶች ከውሃና መብራቱ እጥረት በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ባለመቻላቸው ስራ ወደሚያቆሙበት ደረጃ መድረሳቸውን ይናገራሉ።
ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩ ደግሞ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።
በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ለጎረቤት አገራት ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ መብራት መሸጥ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን ለጅቡቲ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ በፓርላማ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።
ይህ የመብራትና የውሃ ችግር በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ መከሰቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዋና ዋና ከተሞች እጥረቱ ሳምንታትን የሚዘልቅ ሲሆን ለወራት የዘለቀ የመብራትና ውሃ መጥፋት የሚከሰትባቸው ከተሞች እንዳሉም ተገልጿል።
በሌላ በኩል ለውጭ ገበያ የስኳር ምርት እንደቀረበ በተገለጸ ሰሞን 7 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ወደ ሀገር ቤት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መንግስት ማስታወቁ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከ2010 አዲስ ዓመት ጀምሮ ከውጭ ስኳር ማስገባት እንደሚያቆም ባለፈው ዓመት ያስታወቀው መንግስት አዲሱ ዓመት በገባ በስምንተኛው ቀን የስኳር እጥረት መከሰቱን በመጥቀስ ከውጭ ሀገር ለማስገባት መወሰኑን የንግድ ሚኒስቴር ትላንት አስታውቋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ ወደውጭ ስኳር መላክ መጀመሯ መገለጹን ያስታወሱ ታዛቢዎች ወደውጭ የሚላክ ስኳር ያላት ሀገር 7 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ የምታስገባው ለምንድን ነው ሲሉ ይጠይቃሉ።
በተያያዘ ዜና የኬኒያው የንግድ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግስትን ማመስገናቸው ተገልጿል። ሚኒስትሩ በኤን ፒ አር ሬዲዮ ላይ ቀርበው ምስጋናቸውን ያደረሱት ኢትዮጵያ በብዙ ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚቆጠር የበቆሎ ምርት ለኬኒያ በመሸጧ ነው።
‘’ኢትዮጵያ ድርቅ ላይ ብትሆንም እንኳን ለእኛ ይሄን ያህል የበቆሎ ምርት በሽያጭ ማቅረቧ ያስመሰግናታል’’ ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
No comments:
Post a Comment