በሃረሪ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የሃረሪ ምክር ቤት የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ( ኦህዴድ) አባላትን ጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓም የሰበሰቡት የሃረሪ ክልል ፕሬዚዳንትና የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ሊቀመንበር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ፣ ክልሉን ለማረጋጋት ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚያውጁ አስጠንቅቀዋል። ጉዳዩን ከህወሃቱ አቶ አባይ ጸሃዬና ከምስራቅ እዝ አዛዡ ጄ/ል ማሾ በዬና ጋር እየተነጋገሩበት ነው።
አቶ ሙራድ የክልሉ የምክር ቤት አባል የሆኑትን ኦህዴዶችን በመጥራት፣ “ እኛ ሳናውቅ በግላችሁ ስብሰባ እየጠራችሁ ነው፤ ይህ አመጽ ማካሄድ ነው። ህገ ወጥ ስራ እየሰራችሁ ነው” በማለት ሲናገሩ፣ የኦህዴድ ተወካዮች ደግሞ፣ “ ህዝቡን ወርደን ማነጋገር መብታችን ነው። ብትፈልግ እንደ ድርጅት እንወያይ” በማለት መልስ ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንቱ በኦህዴድ አባላት መልስ በመበሳጨት “ ኦህዴድ ደግሞ ድርጅት ነው፤ ስለ የትኛው ድርጅት ነው የምታወሩት፣ ከዚህ ድርጊታችሁ የማትቆጠቡ ከሆነ ሁላችሁንም ሰብስቤ አስራችሁዋለሁ” ብለዋል። በዚህ መልስ የተበሳጩት የኦህዴድ የምክር ቤት አባላት፣ “ እንግዳውስ እናያለን፤ እስካሁንም በአንተ መመራታችን በእብድ እንደተመራን ነው የምንቆጥረው። የምታመጣውን እናያለን” በማለት ስብሰባው ረግጠው ወጥተዋል። የክልሉ የኦህዴድ ሃላፊ አቶ አለማየሁና የሲቪል ሰርቪስ ሃላፊውን አቶ ሸሪፍን ጨምሮ ሁሉም የኦህዴድ የምክር ቤት አባላት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል።
በምክር ቤት አባላቱ ድርጊት የተበሳጩት ፕሬዚዳንቱ፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን በመሰብሰብ በክልሉ ስለተፈጠረው ችግር እንዲሁም ኦህዴዶች የክልሉን ሰላም እያደፈረሱት መሆኑን ሲናገሩ በስብሰባው ላይ የነበሩት የኦህዴድ አባላት በሙሉ ስብሰባውን ጥለው የወጡ ሲሆን፣ አቶ ሙራድም” በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚያውጁ፣ ሁሉንም የኦህዴድ አባላት ሰብሰብው እንደሚያስሩ” ለተሰብሳቢዎች ተናግረዋል።
አቶ ሙራድ አውጃለሁ ያሉትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም ከአቶ አባይ ጻሀዬና ከምስራቅ እጅ አዛዡ ጄ/ል ማሾ በየነ ጋር እየመከሩ ሲሆን፣ እስካሁን ደረስ ከሁለቱ ባለስልጣናት ፈቃድ አላገኙም። ወትሮም የህወሃትን ባለስልጣናት በከፍተኛ ጉቦ እየደለሉ ስልጣናቸውን ሲያስጠብቁ የቆዩት አቶ ሙራድ፣ በክልሉ ያለውን የህዝብ ቁጣ በህወሃቶች ድጋፍ እቆጣጠረዋለሁ ብለው የሚያምኑ ከሆነ ተሳስተዋል በማለት የኦህዴድ አመራሮች እየተናገሩ ነው። የኦህዴድ የምክር ቤት አባላት ሰሞኑን ከህዝብ ጎን መቆማቸውን በይፋ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር። በክልሉ ያለው አስተዳደርና የስልጣን ድልድል ካልተቀዬረ የኦሮሞ ህዝብ የሚኖርባቸውን ወረዳዎች በመገንጠል ወደ ኦሮምያ ክልል እንደሚወስዱ ሲያስጠነቅቁ ከቆዩ በሁዋላ፣ የሃረሪ ባለስልጣናት የአማራ እና የሌሎችንም ብሄሮች ደግፋ ለማግኘት እየተሯሯጡ ነው። በክልሉ የሚኖሩት ሌሎች ብሄሮች ግን ከኦሮሞ ህዝብ ጎን በመቆም የመብት ጥያቄያቸው እንዲመለሱላቸው እየጠየቁ መሆኑን የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል።
ኦህዴድ በአዲስ አበባ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን፣ የሃረሪ ክልል የኦህዴድ አመራሮችን ማስጠንቀቁም ተሰምቷል።
No comments:
Post a Comment