Sunday, November 5, 2017

የኢትዮጵያ ሕልውና እዲጠበቅ የጥላቻ ሰነድ ይቀደድ፤የዜጎች መስተጋብር ይጠበቅ የጋራ አጀንዳ ለጋራ ሁለንተናዊ ነፃነት!!! (ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)


ዛሬ ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ ከአገዛዝ ለውጥ ዋዜማነት ባለፈ ብዙ ፈተናዎች ከፊቷ ተደቅነዋል፡፡ የአገዛዙ የጎሳ ድርጅት አባሎች ተስማምተው አገዛዛቸውን ማስቀጠል አቅቷቸው በእርስ በእርስ ሽኩቻ ተጠምደው ገመናቸው በአደባባይ እየዋለ የአገዛዙ ማርጀትና መበስበስ በብዙ ማሳያዎች እየተገለፀ ነው፡፡ 
1ኛ. በመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር እና በብሮድካስት ባለስልጣን እንዲሁም በብሮድካስት ባለስልጣንና በክልል የጎሳ መንግስታት የሚዲያ ተቋማት መካከል የሚታየው መፈራረጅና አለመደማመጥ
2ኛ. በቅርቡ ለፓርላማ ይቀርባል የተባለውን የትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ በፌደራልና በክልል የጎሳ መንግስታት መካከል የተፈጠረው የስልጣን ይገባኛል ጥያቄና አለመደማመጥ
3ኛ. በቅርቡ ለፓርላማ ይቀርባል የተባለውን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ በተመለከተ የሰራተኛ ማህበራት ያነሱት ያልተለመደ ጠንካራና ሊቀጥል የሚችል ተቃውሞ
4ኛ. በአገዛዙ አቅመ ቢስነትና ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በባዶ እጃቸው ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች በመከላከያ ጥይት ተደብድበው ህይወታቸው ማለፉና ዜጎች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየታረዱ ውድ ህይወታቸውን ማጣታቸው
5ኛ. በአንድ ወቅትና ባልተጠና ሁኔታ በተደረገ የዶላር ምንዛሬ ማሻሻያ ምክንያት በዜጎች የእለት ከእለት ኑሮና አጠቃላይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረው ምስቅልቅል
6ኛ. ይህ አስደንጋጭ ሁኔታ ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጭ መሆኑን የሀይማኖት ተቋማት ሁሉ እየተገነዘቡት በመምጣታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገር አቀፍ ምህላ ማወጇ
ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የጠቀስናቸው ማሳያዎች ሀገራችን ያለችበትን ውስብስብ ችግርና የዜጎቿን ትብብርና ቅንነት የምትሻበት ከባድ ፈተና ላይ መሆኗን ያሳያል፡፡ አሁን ለተጋረጠብን ሀገራዊ የብተና አደጋ ዋናው መሰረቱ በልዩነትና በጥላቻ ላይ የተመሰረተው የጎሳ አስተዳደር ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም ከዚህ ከአንዣበበብን የብተና አደጋ ለመዳን አሁን ያለውን በዘር ላይ የተመሰረተ አገዛዝ በመለወጥና ጊዚያዊ የባላደራ መንግስት በማቋቋም ሁሉን አቀፍ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ህጋዊ አስተዳደር ለመመስረት ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ቀዳሚ አጀንዳችን አድርገን ትግላችንን እንድናስተባብር ጥሪያችንን እያቀረብን በሰራተኛ ማህበራትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝበው የወሰዱት አቋም በሌሎች ተቋማትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናሰስባለን፡፡ 
በመጨረሻም የሀገራችን ችግር ከአንድ ፓርቲ አቅም በላይና በጥገናዊ ለውጥ የማይሰተካከል መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት የህብረተሰብ ውክልና የሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲ ነን ባዮች የሀገራችንን ሁኔታ ላለማቀፍ ማህበረሰብ ድርድር በሚሉት ማጭበርበሪያ አቃለው በማሳየት ችግሩን የሚመጥን መፍትሔ በሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዳይወሰድ ከባድ እንቅፋት እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ መፃኢ እድል ላይ እየፈጠሩት ያለው ጠባሳ ታሪክ ይቅር የማይለው ሀገራዊ ክህደት ስለሆነ ይህንን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ እያሳሰብን እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የለውጥ ሃይሎች ሁሉ ተገቢውን ጫና እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ጥቅምት 26 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባImage may contain: 10 people, people standing and outdoor

No comments:

Post a Comment