መቀሌ
ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓት መቀሌና ሀራሬ ሁነኛ የፖለቲካ ክስተት ተፈጥሯል። የመቀሌው ይፋ የወጣ አይደለም። በህወሀት አፍቃሪያን ድረገጾች የተተነፈሰ ወሬ ነው። ወ/ሮ አዜብ መስፍን የመቀሌውን ህንፍሽፍሽ ረግጠው ወጡ የሚለው ከውስጥ አዋቂ ያፈተለከው ዜና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በትክክል ከሆነ የሀራሬው ዓይነት መፈንቅለ መንግስት ልናይ የምንችልበት እድል ሰፊ ነው። የጄነራል/ፕሮፌሰር ሳሞራ የኑስ ቡድን በመቀሌው ስብሰባ ከተሸነፈ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ አይሆንም። በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባው ህወሀት በአንዳች ተአምር መከላከያውን ከሳሞራ የኑስ እጅ ፈልቅቆ ካልወሰደ በቀር የወ/ሮ አዜብ መስፍን ኩርፊያና ረግጦ መውጣት የሚያስከትለው መዘዝ ለህወሀት ፍጻሜው ሊሆን ይችላል።
ትያትሩን አድፍጦ መከታተሉ ጥሩ ነው። ያም መጣ፡ ይሄም ሄደ ልዩነት የለውም። ለኢትዮጵያ ህዝብ የትኛውም የህወሀት አንጃ አይበጀውም። ህወህት ቢከፈልም፡ ቢሰነጣጠቅም ያው ህወሀት ነው። ከነስሩ ተመንግሎ፡ ተጠራርጎ መወገድ ያለበት እንጂ ክፋዩ፡ ስንጣቂው ቢተርፍና በስልጣን ላይ ቢቆይ ለኢትዮጵያና ህዝቧ ተውሳክ፡ ነቀርሳ መሆኑ የማይቀር ነው።
ሀራሬ
የዙምቧቡዌ ሰማይ ያልተለመደ አየር ነፍሶበታል። የ40 ዓመቱ የሙጋቤ ስዩመ እግዚያብሄር አገዛዝ ፍጻሜውን አግኝቷል። በስልጣን ላይ በመቆየት የዓለምን ክብረወሰን የጨበጡት ሽማግሌው ሙጋቤ ከነሚስታቸው በወታደሩ ክፍል ለጊዜው በማቆያ ይገኛሉ። ብሄራዊው ቴሌቪዥን ላይ የዚምቧቡዌ ጦር መሪዎች መግለጫ እየሰጡ ነው። በአጭሩ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል። ለዚምቧቡዌ አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል። ሰውዬው በአጥንታቸው ሳይቀር ጨምድደው እየገዟት ያለችው ሀገር በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ወጥታለች። ሁኔታዎች በፍጥነት በሚለዋወጡባት ዚምቧቡዌ የሚሆነው ነገር አይታወቅም። ታሪክ ግን ተቀይሯል።
ዚምቧቡዌ በአንድ ስልጣኑን እስከመቃብሩ ድረስ ላለመልቀቅ በወሰነ ሽማግሌ የስንግ ተይዛ ለ40 ዓመታት ቆይታለች። ኢትዮጵያ በዘርና ጎሳ በተቧደኑ፡ በዘረፋና ሌብነት ሀገሪቱን ለመጋጥ በተሰለፉ የአንድ መንደር ልጆች ከሩብ ክፍለዘመን በላይ ደሟ እየተመጠጠ ያለች ሀገር ናት። የዚምቧቡዌ ጦር የዚምቧቡዌ ነው። የኢትዮጵያ ጦር የኢትዮጵያ አይደለም። በዚምቧቡዌ መፈንቅለ መንግስት ቢካሄድ አዲስ ስርዓት በተስፋ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ግን መፈንቅለ መንግስት የህወሀትን አገዛዝ በመሳሪያ ሃይል የሚያስጠብቅ ሌላ የጨለማ ዘመን የሚያመጣ እንጂ ለውጥ አይኖረውም።
ዕቅድ ወይስ ስንብት?
ለአዲስ ስታንዳርድ በቅድሚያ ምስጋና ይገባዋል። ይህ ሰነድ ወይም ዕቅድ ወይም ኑዛዜ ወይም የስንብት ደብዳቤ ይደርሰን ዘንድ የአዲስ ስታንዳርድ ውለታው ላቅ ያለ ነው። ሰነዱ በጣም ጠቃሚ ነው። በጣምም ወሳኝ ነው። ለነጻነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መምጣት ለሚዋደቁ ሃይሎች በተለይም በለውጥ ምጥ ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ዕቅድ ተስፋን የሚያለመልም ነው። በእስከአሁኑ በዚህ ደረጃ የህወሀት መንግስት ውድቀቱን ያመነበት ሰነድ አላየሁም። የጠቃሚነቱን፡ የወሳኝነቱን ያህል ግን ትኩረት አልተሰጠውም። ኢትዮጵያ እንደዚምቧቡዌ ያረጀውንና፡ የጃጀውን ስርዓት ልትገላገለው በዋዜማው ላይ መሆኗን የሚያበስር ዕቅድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ዝርዝር ዕቅዱ የህወሀትን የወቅቱን ቁመና የሚያሳይ ነው። ውስጣዊ ሁኔታዎች በሚል በ10 ነጥቦች የተዘረዘሩትን ከወሰድን ከአንድ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። የህወሀት መንግስት በእርግጥም አብቅቶለታል። በተቃራኒው ያለው የለውጥ ሃይል ጠንካራ ባለመሆኑ፡ ወይም፡ በአንድነት ባለመሰለፉ ወይም በሁለቱም ምክንያቶች የተነሳ እየፈራረሰ ያለውን የህወሀት ስርዓት ወደመቃብሩ መውሰድ ባለመቻሉ ህወሀት ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን እድሜው እንዲቀጥል እየሆነ ነው። የህወሀትን ኑዛዜ ዋና ዋና ክፍሎችን እንመልከተው።
ህዝብ ተስፋ ቆርጦብኛል
ህውሀት አልደበቀም። እንደሁልጊዜውም የህዝብ ተስፋ ነኝ የሚል ባዶ ኩሸት መደለቅ አልፈለገም። በዕቅዱ ላይ እንደተናዘዘው ህዝቡ ተስፋ ቆርጦበታል። ህዝብ በህይወት የመኖር ተስፋው እየቀነሰ፡ እየጨለመ መምጣቱን፡ በስርዓቱ ላይ ተስፋ የመቁረጥና ይህ ስርዓት ይቀጥል ይሆን የሚል ብዥታ ውስጥ መግባቱን ይገልጻል። ህዝቡ የሰላም ዋስትና ማጣቱንም ህወሀት አምኗል። ስጋት ውስጥ የተዘፈቀ፡ በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ላይ እምነት አጥቶ ውዥንብር ውስጥ የገባ ህዝብ ሲልም ያስቀምጣል። ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ሰራዊቱም ተስፋ እንደቆረጠበት ተናዟል። ለህወሀት ትልቁ አደጋ ይሄ ነው። የጸጥታ ሃይሉ ሰላም የማስከበር አቅሙ መጎዳቱን፡ በመንግስት መቆየት ላይ ጥርጣሬ ውስጥ መግባቱን፡ በአጠቃላይ መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ በሰራዊቱ ውስጥ መከሰቱን አትቷል።
ጸረ-ሰላም ሃይሎች(የለውጥ ሃይሎች)
ይህን ዕቅድ ላነበበ አንድ ነገር ግልጽ ይሆንለታል። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሀትን ስርዓት ገንድሶ ለመጣል የተስለፉ ሃይሎች እግር አውጥተው ረጅም ርቀት እየተጓዙ ለመሆናቸው ትልቅ ማስረጃ የሚሆን ሰነድ ነው። ተቃዋሚዎች የታላችሁ? መሳሪያ የታጠቀ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይ? ለሚሉ ሰዎች የህወሀት ዕቅድ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። በዕቅዱ ላይ እንደተገለጸው አርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሀገሪቱ እንደፈለጉ በመፈንጨት ላይ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በፕሮፖጋንዳው ጭምር እንደበለጡትም አምኗል። ሃይላቸው ተጠናክሯል። ህዝብን ከጎናቸው እያሰለፉ ነው። ለጦርነት የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ እየሰበሰቡ ነው። መሳሪያ ግዢው ተጧጡፏል። እነዚህ ሃይሎች መንግስት ተዳክሟል፡ ሀገር ለመምራት አይችልም ከሚል ድምዳሜ ደርሰው ስርዓቱን ሊያፈራርሱ እየተረባረቡ ነው ሲል ህወሀት የመጣበትን አደጋ በግልጽ አስቀምጧል።
ጸረ ሰላም(የለውጥ) ሃይሎች ውስጡን እንደቦረቦሩት ህወሀት በገደምዳሜም ቢሆን ገልጿል። አመራሩ በተለይም መካከለኛውና የታችኛው አመራር በእነዚህ ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ ታጥቦ ተወስዷል የሚለው ህወሀት በሀገሪቱ ለተከሰተው አጠቃላይ ቀውስም የራሱ መዋቅር ላይ ጣቱን ቀስሯል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ የብአዴን፡ ኦህዴድንና ደኢህዴንን መዋቅር ሰብረው መግባታቸውን በመግለጽ በተለያዩ ጊዜያት ለሚወጡ ጥሬ መረጃዎች ማረጋገጫ የሚሰጥ ኑዛዜ ነው። ህወሀት በዚህ ዕቅዱ የተቃዋሚዎች(የጸረ ሰላም ሃይሎች) መጠናከርን የህዝብ ስጋት የፈጠረ ሲል ይገልጸዋል። በእርግጥ ተቃዋሚዎች በዚህ ደረጃ ማንሰራራትና መጠናከር መቻላቸው ለህዝብ ስጋት አይሆንም። መርዶም አይደለም። ተስፋ እንጂ። ተቃዋሚዎችን ፍለጋ በየሰፈርና መንደሩ የሚሰማውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የሚመልስ የወቅቱ ታላቅ የምስራች እንጂ።
ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው
የህወሀት ኑዛዜ በኢኮኖሚው ላይ ያስቀመጣቸው እውነቶች በተለያዩ የነጻነትና የዲሞክራሲ ደጋፊ ሚዲያዎች ሲባል የነበረውን የሚያረጋግጥ ነው። ህወሀት ግብር መሰብሰብ እንዳልቻለ ገልጿል። መንግስት የለም፡ ግብር አትክፈሉ የሚል ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው ብሏል። በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ሳቦታጅ( ዶ/ር ታደሰ ብሩ አሻጥር ይለዋል) እየተፈጸመ መሆኑን አትቷል። ህዝቡን ለልማት ከማሰማራት ይልቅ የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ለግጭትና ለሰላም መደፍረስ ሚና እንዲጫወት እየተደረገ ነው ያለው ህወሀት በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው ክፉኛ መጎዳቱን አስታውቋል። የውጭ ኢንቨስትመንት ተዳክሟል። የቱሪስት ፍሰት ቀንሷል። የውጭ እርዳታ በከፍተኛ መጠን ወርዷል።
የህወሀት ዕቅድ ላይ እንደተገለጸው ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ሀብትና ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ከሀገር እያሸሹ ናቸው። እነማን እንደሆኑ በእርግጥ አልተገለጸም። መረጃዎች የሚያመለክቱት የህወሀት ባለስልጣናትና በዘር መስመር ሀብት ያፈሩ የትግራይ ተወላጆች በዋናነት ሀብት እያሸሹ መሆናቸውን ነው። በነገራችን ላይ ማክሰኞ አንድ ሪፖርት ወጥቷል። የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ከ10ሩ ገንዘብና ሀብት ከሚሸሽባቸው የዓለም ሀገራት ውስጥ አስገብቷታል። በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ በሚሸሸው ሀብትና ገንዘብ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ ነው። ለ28ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ሰርኩላር ተበትኗል። የህወሀት ባለስልጣናት አንዱ የሀብት ማሸሺያ መስመር አሁን ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ታስሯል። የሼህ አላሙዲን መታሰር በህወሀት መንደር ሽብር የፈጠረው ያለምክንያት አይደለም። እናም ህወሀቶች ለጡረታቸው ያሸሹት ሀብትና ገንዘብ ወጥመድ ውስጥ ገብቷል።
ጄኖሳይድ
የዚህ ዕቅድ አስደንጋጩ ክፍል ይሄው ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የጅምላ ግድያ መፈጸሙን ህወሀት ገልጿል። በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሃል በተፈጠረው ግጭት ጄኖሳይድ ተፈጽሟል ያለው የህወሀት የደህንነት ዕቅድ እነማን እንደፈጸሙ፡ ምን ያህል ሰዎ እንዳለቀ በዝርዝር አያስቀምጥም። የፖለቲካ ተንታኞች ህወሀት ሌሎችን ለማጥመድ የስነቀራት ምክንያት ልትሆን ትችላለች የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ። በተለይም የሁለቱን ክልሎች በዋናነትም የኦሮሚያ ክልል መሪዎችን ለማስበርገግ ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ። ሆኖም ህወሀት ሳያስበው ራሱ ላይ ጥይቱን አቀባብሏል የሚሉ ወገኖችም አሉ። ህወሀት በሚቆጣጠራት ሀገር ጄኖሳይድ ተፈጽሞ ከሆነ ይህን የምድረግ አቅም ያለው የህወሀት ጦር በመሆኑ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆነው የህወሀት መንግስት ነው። ለዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥሩ ዱላ ነው። ሌሎች በኢትዮጵያ የተፈጸሙና የተደበቁ የጅምላ ግድያዎች የሚነሱበትና ተጠያቂዎች ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ የሚቀሰቅስ ሊሆን ይገባዋል። በኦጋዴናን በአኝዋክ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጽሙትን ጄኖሳይዶች ማን ይረሳቸዋል?
የጦስ ዶሮ
ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩ ቀውሶች ራሱን ተጠያቂ ከማድረግ ተቆጥቧል። ሶስት አካላት ላይ ጣቱተቀስሯል። ግብጽና ኤርትራ በረጅም እጃቸው ኢትዮጵያን እየበጠበጡ ነው የሚል ክስ በህወሀት ቀርቧል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ ሀገሪቱን በማመስ ተወንጅለዋል። የስርዓቱ አመራሮች ለቀውስ የተመቸ ሜዳ በመፍጠር ጥርስ ተነክሶባቸዋል። በዕቅዱ ላይ አንድም ቦታ ህወሀት ሃላፊነት አልወሰደም። አሁንም ለኢትዮጵያ ህዝብ መላዕክ መሆኑን ይገልጻል። የጦስ ዶሮዎች እየተፈለጉ ነው። በተለይ በስርዓቱ ውስጥ ያኮረፉት ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። መጠነ ሰፊ እስሮች ከፊት እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የዕቅዱ አንድም ግብ እነዚህን አመራሮች ልክ ማስገባት ነው።
የዕቅዱ ግብ ሌሎች ተግባራትንም ያከናውናል። ሰልፎች ታግደዋል። በአስቸኳይ አዋጁ ገደብ የተጣለባቸው መብቶች በተዘዋዋሪ በዚህኛው ዕቅድም ተግባራዊ ይሆናሉ። ዕቅዱ በስም እንጂ በይዘት ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር አንድ ነው። የዕቅዱ ሌሎች ግቦች ከፉከራ ያለፉ አይደሉም። መሳሪያ መንጠቅ፡ ጸረ ሰላም ሃይሎችን መደምሰስ እና የመሳሰሉት ግቦች አሁን ህወሀት ካለበት ቁመና አንጻር የሚሳኩ አይመስሉም።
ማጠቃለያ
የመቀሌው ስብሰባ አልተጠናቀቀም። ህወሀት ሪፎርም ማድረጉንና ከስልጣን የሚያሰናብታቸው አመራሮች እንደሚኖሩ እየተነገረ ነው። It is too late. ምን ዓይነት ሪፎርም? ህወሀት አፈጣጠሩ ለዚህ የሚፈቅድለት አይደለም። ያረጠ ድርጅት ነው። ከተቸነከረበት የስታሊን መስመር ዝንፍ ካለ መጥፊያው ነው። ደግሞም 11ኛው ሰዓት ላይ ሪፎርም አያድነውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሀትን ሊሰናበት ተዘጋጅቷል። ይህ ዕቅድም የስንብት እንጂ የሪፎርም አይደለም። ከመቀሌ የሚጠበቅ ለውጥ አይኖርም። ህወሀት በዕቅዱ እንዳስቀመጠው ህዝቡ መንግስት ይቀጥላል ብሎ አያምንም። ተስፋ ቆርጧል። ስለዚህ ዕቅዱን የስንብት ደብዳቤ ነው ቢባል ያስኬዳል። ኑዛዜም ነው። ይህን ተቀብሎ የማሰናበትና ህወሀትን ከነጥቁር ገጽታው
No comments:
Post a Comment