Saturday, January 24, 2015

ለኢትዮጵያ የዋልክላትን ውለታ የሚመልስልህ ሆድህ ብቻ ነው !!! 24 January 2015 at 10:02

ምኒልክ ዘጎጃም ዘመነ ትዝታ ቅፅ -  ክፍል - ፪

ፊት አውራሪ ገሞራውን ድፍን የጎጃም ሰው ያውቃቸዋል ። ገሞራው የጦር ሜዳ ስማቸው ነው እናት እና አባቶቻቸው ያወጡላቸው ስም ሸዋፈራሁ ነው ነገሩ ስምን መላእክ ያወጠዋል ነው ። ወራሪ ኢጣሊያንን አይቀጡ ቅጣት ሰጥተው በጀግንነት ጣሊያንን ድል ከነሱ አርበኞች አንዱ ናቸው ። የእነ በላይ ዘለቀ ጦር ሶማ በረሃ ላይ ኢጣሊያ ዶግ አመድ ሲያደርጉ የእነ ፊት አውራሪ ኃይለ ኢየሱስ (አባ ፍላቴ) ጦር ደግሞ የጨረቃ ላይ ኢጣሊያንን እንዳልነበር አደረገው ። በእነ ፊት አውራሪ ገሞራው የሚመራው ጦር ደግሞ ደጋ ዳሞት ላይ በእሳተ ገሞራዊ ጥቃት አጋዬው ። ፊት አውራሪ ገሞራው ከሁለት ሺ አምስት መቶ በላይ የኢትዮጵያ አርበኞችን ይዘው ነበር ለአምስት አመታት ኢጣሊያንን ተዋግተው ያሸነፉት ። ኢጣሊያን የእነ ፊት አውራሪ ገሞራው ጦር መቋቋም ከሚችለው በላይ ሁኖበታል ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ ለማጥቃት ይነሳል ድንገት እንደ እሳተ ገሞራ የፊት አውራሪ ገሞራው ጦር በኢጣሊያን የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ይሰነዝራል አሁን ገሞራው ሸሸ ሲባል እንደ እሳተ ገሞራ ደንገት ይፈነዳል በዚህ የተነሳ ኢጣሊያን ፊት አውራሪ ገሞራውን ለማግባባት ሽማግሌ ይልካል ይኸኔ ፊት አውራሪ እንዴት ቢንቀኝ ነው ይህ ሶላቶ እጄን እንድሰጥ እና ሀገሬን እንድሸጥ ባንዳ ሁኜ ክብሬን እንድለውጥ የሚያግባባኝ በማለት እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ለሽማግሌዎች እንድ ነገር ላስቸግራችሁ ይችን መልእክት አድርሱልኝ አሏቸው ፦


እኔ ሸዋፈራሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምኒልክ የቴዎድሮስ ልጅ ነኝ ሀገሬ ደግሞ ለወራሪዎች አትሆንም እናንተ አታውቁንም የመጣችሁ እናንተ ናችሁ በባርነት ልትገዙን ያሰባችሁ መሬታችንን የረገጣችሁ እናንተ ናችሁ ኢትዮጵያ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በደማችን የታተመች በአጥንታችን ዘልቃ የገባች ሁሉ ነገራችን ነች ። ስለዚህ ሀገራችን ለቃችሁ ውጡ ጮጨ ተራራ ላይ ያሰፈራችሁትን ጦር ነገ የማታስወጡ ከሆነ ሌት እመጣ ቀን እመጣ አታውቁትማና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁኝ ። ወንድ ልጅ እጁን ሳይሆን ደረቱን ለጦር አንገቱን ለሰይፍ ነው የሚሰጠው እኛ ኢትዮጵያውያን ለማንም የማንበረከክ ሕዝቦች ነን !!!

መልእክተኞችም የእነ ገሞራውን መልስ ይዘው ወደ ኢጣሊያን የጦር ሰፈር አመሩ የተባሉትንም መልእክት አደረሱ በዚህን ጊዜ ኢጣሊያን ተሸበረ ጥብቅ ጥበቃ በዐራቱም አቅጣጫ እንዲሆን ተደረገ የካቲት ፳ ፲፱፻፴፩ ዓ.ም በውድቅት ሌሊት የእነ ሸዋፈራሁ ጦር የኢጣሊያንን ጦር ፊት ለፊት መተግተግ ጀመረ የኢጣሊያንን ጦር ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ እስከ ሌሊቱ አስር ሰዓት የሞት ሽረት ፍልሚያ አደረገ በተለይ በሌሊት ወደ ላይ የሚተኮሰው ባውዛ እነ ሸዋፈራሁን አላንቀሳቀስ አላቸው ፊት አውራሪ ገሞራው ለጦራቸው አንድ ትዕዛዝ አስተላለፉ ጎበዝ ይህ ሶላቶ አሁን ወደ ፊት የምናደርገውን ግስጋሴ በሚተኩሰው ባውዛ ገድቦናል አሁን ባለነበት ላይ እንከላከል ጧት ላይ ሁሉም ነገር ያበቃለታል ያኔ ፀሐይ ለሁላችንም እኩል ናት ኧረ እንደውም ለእኛ ታደላለች ጦራቸውም ትዕዛዙን ተቀበለና እስከ ጧቱ ፲፪ ሰዓት ባሉበት የመከላከል ውጊያ ሲያደርጉ አደሩ ይኸኔ ኢጣሊያን የሸዋፈራሁ ጦር ከዚህ በላይ መዋጋት አይችልም ስለዚህ መልሶ ማጥቃት እንሰንዝር አለ ። ጨለማው ለቀኑ ተራውን አስረክቦ ብርሃን መፈንጠቅ ሲጀምር ሸዋፈራሁ ተነስ ጎበዝ ወደ ምሽግ አለ ድንገት እንደ እሳተ ገሞራ የፈነዳው የእነ ገሞራው ጦር ኢጣሊያንን ከጮጨ ተራራ ላይ አንደርድሮ ወደ ፍኖተ ሰላም ማበረር ጀመረ በወቅቱ የኢጣሊያኑ የጦር አዛዥ የለም ስንለው ድንገት እንደ እሳተ ገሞራ እየፈነዳ መቋቋም አልቻልንም ወደ ፍኖተ ሰላም እየሸሸን ነው በማለት የሬድዮ መልእክት ለባይ አመራሮቹያስተላልፋል ። ከዚህ በኋላ የሸዋፈራሁ ስም ገሞራው ሁኖ ቀረ ።
ፊት አውራሪ ገሞራው አስደናቂ ጀግና አርበኛ ናቸው ታዲያ እኒህ ታላቅ የሃገር ባለውለታ አርበኛ ከአያቴ ጋር የተዋወቁት የክብር የጀግንነት ሜዳይ ሽልማታቸውን ለመቀበል አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ነበር ። ከዚያ በኋላ ከአያቴ ጋር ቤተ ዘመድ ይሆናሉ ይጠያየቃሉ ። ፊት አውራሪ ገሞራው ጠላት ድል ተነስቶ ሃገራችንም ነፃ ወጥታ አፄ ኃይለ ሥላሴ በኦሜድላ በኩል ወደ መንቆረር የአሁኗ ደብረ ማርቆስ ሲገቡ አቀባበል አድርጉ ሲባሉ እኔ አላድረገውም ፈርቶ የሄደን ሰው በጀግንነት አልቀበልም በማለት አቀባበሉ ላይ ሳይገኙ ይቀራሉ ። ይህ ነገር ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ይደርሳል በብዙ ማግባባት ፊት አውራሪ የሚለውን ማዕረግ እና የክብር ኒሻናቸውን ከአርበኞች ጋር እንዲወስዱ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ በዚህ ሰዓት በባንዳነት ሃገርን ሲሸጡ ሕዝቡን በመርዝ ጋዝ ሲያስጨርሱ የነበሩ ባንዳዎች ስልጣን ተሰጥቷቸው ቤተ መንግሥት ላይ ሲያዘጠዝጡ ፊት አውራሪ ገሞራው ያያሉ “ እኔ ሸዋፈራሁ ከባንዳ ጎን አልቆምም ሃገሬን ነፃ አውጥቻለሁ በቃ አርሼ እበላለሁ ። ” ይሉና ሥርዓቱን አቋርጠው ወደ ማረፊያቸው ይሄዳሉ አፄ ኃይለ ሥላሴ ገሞራው የታለ ሲሉ አሟቸው ሂደዋል ይባላሉ ። በዚህን ሰዓት ሌሎች አርበኞች ፊት አውራሪ ገሞራውን ማግባባት ይጀመራሉ በቃ ተወው ብዙ መከራ ተቀብለናል ወንድሞቻችን እህቶቻችንን አጥተናል ማዕረጉን እና ኒሻንህን ተቀበል ይሏቸዋል በዚህ ይስማሙና በበነጋቴው ሽልማታቸውን ይቀበላሉ ። ወደ ጦሩ ገብተው በኃላፊነት እንዲሰሩ ይመደባሉ አይ እኔ በቃኝ አርሼ እኖራለሁ ስልጣኑን አልፈልገውም በማለት ወደ ጎጃም ይመለሳሉ መደበኛ ሕይወታቸውንም መምራትይጀምራሉ ። በዚህ መሃል የደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ መገደል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከአፄው ጋር አጣላቸው ። ዘመን ዘመንን ተካና ደርግ ወደ ስልጣን ይመጣል በዚህ ጊዜ ፊት አውራሪ ገሞራው የደርግን የቀይ ሽብር እልቂት ያወግዛሉ ይህ ወጠጤ ይችን ሀገር በደም እየነከራት ነው ይላሉ ። ፊት አውራሪ ገሞራው ነገርን ፊት ለፊት ነው እኔ ገሞራው እንኳን ነገርን ኢጣሊያንንም ፊት ለፊት ገጥሜ ነው ያሸነፍኩት ነው አባባላቸው ። ታዲያ ይህ አቋማቸው በደርግ ባለ ስልጣናት አልተወደደም በተለይ ደርግ አቡነ ቴዎፍሎስን ሲረሽን በአደባባይ አወገዙ ደርግም አንተማ በርዣ ነህ ፀረ አብዮተኛ ነህ በማለት ወደ እስር ወረወራቸው ። የጎጃም ሕዝብ እንዴት እኒህ ጀግና አርበኛ ይታሰራሉ ይህማ አግባብ አይደለም በማለት ቁጣውን ይገልፃል የሕዝቡ ቁጣ ያስፈራው ደርግ ፊት አውራሪ ገሞራውን ከእስር ይለቃል ። መሬታቸውን ግን አስር ጥማድ ብቻ ያስቀርና ይወርስባቸዋል ነገር ግን ፊት አውራሪ ገሞራው በዚህ ብዙም አልተከፉም እኔ ዛሬ በሕይወት አለሁ ብዙ አርበኛ ጓደኞች በጦርነቱ አልቀዋል ሆድ ከሃገር ይሰፋል መቻልን የመሰለ ነገር የለም ይላሉ 
ደርግም ጊዜው ደረሰና በወያኔ ተተካ ወያኔ ፊት አውራሪ ገሞራው በአፄ ኃይለ ሥላሴ እና በደርግ የተበደሉ ናቸው በማለት ሊያቀርባቸው ይፈልጋል ምን ዋጋ አለው ከወያኔም ጋር ገና በጧቱ ተጣሉ ወያኔ ኤርትራን ለሻቢያ ሲሸጥ እንዴት ሁኖ እነ አሉላ አባ ነጋ መስዋዕትነትን የከፈሉባት ሀገሬ እንዴት ሁና ትከፋፈላለች እናንተ ከታሪክ ጋር ችግር አለባችሁ ሕዝቡን አትከፋፍሉት እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ነን አንድ ስለሆንን ነው ጠላትን ድል የነሳነው ይላሉ ። መጨረሻ ላይም ሕዝቡን ያነሳሳል የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ተብለው ወደ እስር ቤት ተወረወሩ የጎጃምሕዝብ በአንዴ ገነፈለ ጀግና አባታችንን ፍቱ ለሕዝቡ ዲሞክራሴ እንሰጣለን ትላላችሁ ትክክለኛ ነገር የሚናገሩትን ወደ እስር ቤት ትወረውራላችሁ በዚህ ሰዓት የሕዝቡን ቁጣ የተረዳው ወያኔ ፊት አውራሪ ገሞራውን ከእስር ይፈታል ቀን ሲጠብቅ የነበረው ወያኔ እርስዎት ቢሮክራሴ ስለሆኑ በማለት ደርግ ያሻውን ወስዶ ካስቀረላቸው ፲ ጥማድ መሬት ላይ ስድስት ጥማዱን አንስቶ ፬ ጥማድ ብቻ መሬት አስቀረላቸው ። ታዲያ በዚህ ወቅት ነው አያቴ እስኪ ፊት አውራሪ ገሞራውን ልጠይቃቸው በማለት እኔን አስከትሎ ወደ ደጋ ዳሞት የሄደው ።

ጉዟችን የተወሰነውን በሎንችና ከተጓዝን ቀሪ የስምንት ሰዓት መንገድ በእግር ዳቦ ቆሎ እና አንድ ጠርሙስ አረቄ ይዘን ነበር አያቴ አርበኛ ነው ጀግናን ይወዳል ከፊት አውራሪ ገሞራው ጋር በጣም ይዋደዳሉ ይህንን ሁሉ እርቀትም ያመጣን ይህ ነው ። እያረፍን እየተነሳን አይደርሱ የለም ደረስን በተለይ እኔ በጣም ደክሞኝ እግሬም ጓጉሎ ነበር ። ልክ ከቤቱ ደረስን አሁን ደርሰናል አለኝ አያቴ ከውጪ አንዲት ልጅ እግር ጉብል አገኘን አያቴ ልጄ እንደምን ዋልሽ ፊት አውራሪ አሉ እንግዳ ይፈልግዎታል በይልን ውሾች ታሰረዋል ? እሺ ብላ እየሮጠች ወደ ቤት ገባች ፊት አውራሪ ብቅ አሉ ብላታ ሁል ጊዜ አንተ ትመጣለህ እኔ እንደ ድሮው እንዳልመጣ ጉልበቴ ደከመ አንገት ለአንገት ተያይዘው ተላቀሱ በቃህ ፊት አውራሪ ከአንተ እኔ እሻላሉ ብዬ ነው የደረሰብህን ሁሉ ሳስበው ሁሌም አዝናለሁ በቃ ተው አታልቅስ ወደ እኔ መጡ ይኸ የልጅ ልጅ ነው አይደል ? ግንባሬን ተሳምኩኝ እኔም ጉልበታቸውን ሳምኩኝ ያሳድግህ ልጄ አነጋገራቸው አሁንም በአእምሮዬ ያቃጭላል ግቡ ተባልን ወደ ውስጥ ገባን የጎሽ አጎዛ ተነጠፈልን በይ እስከ ማዘንጊያ የእግር ውሃ ቶሎ በሉ ልጄ ሞቷል እንደው አይ ብላታ ልጁን ጨምረህ ታደክመው ውሃ መጣ ማዘንጊያ አፍተልትላ በቀዝቃዛ ውሃ እግሬን ስታጥበኝ ደካሙ ሁሉ ጠፋ ። ወዲያው ልጆቻቸው እንግዳ እንደመጣ አውቀው ኑሯል በአንድ እቃ እርጎው በአንድ አቃ ጠላውን ይዘው መጡ አያቴን ሁሉም ልጆች ያውቁታል ጉልበቱን ስመው ተቀመጡ ። ወዲያ አንድ ሙክት ተስቦ መጣ ብላታ በል መርቅ እይ ፊት አውራሪ ይህ እኮ አይገባም አንደው በመጣሁ ቁጥር ድግስ ግዴለም የምን ማስቸገር ሙክቱ ታረደ የእማሆይ ፍቅሬን ቦንብ የሆነ ጠላ እየጠጣን የዳሞትን ገብስ ቆሎ እየቆረጠምን ጭውውታችን ቀጠለ። ይህን ልጅ እያስተማርከው ነው ብላታ አዎ ብያለሁ ከተሳካለት ልጅ ምኒልክ ስንተኛ ክፍል ነህ አምስት የቤተ ክህነቱንስ ዜማ ላይ ነኝ ጥሩ ነው ፍፃሜህን ያሳምርልን ።

በበነጋቴው ከቤተ ክርስቲያን መልስ ጧት ላይ ቡና ተፈላ ጨዋታው ደራ ከአያቴ ጋር ያሳለፉትን ነገር እያነሱ ያወጋሉ በተለይ ከኢጣሊያን ጋር የነበረውን የአምስት አመታት ተጋድሎ ሲያነሱት ይች ሃገር በምን ሁኔታ እዚህ እንደ ደረሰች ማወቅ ይቻላል ። ልጅ ምኒልክ ተጫወት አሉኝ ፊት አውራሪ እሺ አልኩኝ እኔም አንዳንድ ጥያቄዎችን አያቴ ከሚነግረኝ ታሪክ እያነሳሁ እንደው ጦርነቱ እንዴት ነበር ? ከዚያ በኋላ ለእናንተ የተደረገው ነገር ምን ነበር ? መጠየቅ ጀመርኩኝ ፊት አውራሪ ገሞራው በሐሳብ ነጎዱ ከፊታቸው ላይ ትካዜ መጣ አየህ ልጅ ምኒልክ ጦርነቱ በጣም አስከፊ ነበር ኢጣሊያን ዘመናዊ ሰራዊትከ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ጋር ለ፵ ዘመን ተዘጋጅቶ ነበር ኢትዮጵያን የወረረው እኛ ደግሞ ከሃገር ፍቅር ከወኔ እና ከጀግንነት ውጪ ምንም አልነበረንም አንድ ላይ የሚያሰባስበን መሪ እንኳን አልነበረንም እኛው በያለንበት ነበር የምንዋጋው ጎጃም ላይ እኛ እነ ደጅ አዝማች በላይ እነ ኃይለ ኢየሱስ ሸዋ ላይ እነ ሸዋረገድ ገድሌ አምቦ ላይ እነ ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ደብረ ብርሃን ላይ እነ ኃይለ ማርያም እነ ራስ አበበ ብቻ ተበታትነን ነበር ይህ ደግሞ ለኢጣሊያን በጣም ተመችቶታል የሌሊቱ ውጊያው በጣም ሲከብድ ወደ ላይ የሚተኩሰው ባውዛ በጣም ያስቸግረን ነበር በዚያ ላይ ስንቅ የለንም ገበሬው ተረጋግቶ ስለማያርስ ስንቅ ማግኘት ፈተና ነበር በዚያ ላይ በመርዝ ጋዝ በየቀኑ በአውሮፕላን ይጨፈጭፈን ነበር ለኢጣሊያን ያደሩ ባንዳዎች የእኛን መውጫ መግቢያ ስለሚያውቁ ይህ እንደኛው ፈተና ነበር ብቻ ብዙ ነው ግን ከእግዚአብሔር እርዳታ ጋር በሕዝቡ መራር ተጋድሎ ድል አድርገን ዛሬ እናንተ እንገታችሁን ቀና አድርጋችሁ እንድትሄዱ አድርገናል የእኛ ስጦታ ይህ ነው ። ከጦርነቱ በኋላ ንጉሡ ወደ ሥልጣን መጡ እኛ እርስዎት ፈርተው ሸሽተዋል ስለዚህ አይሆንም አልን ይህ ግን የሚሆን አልነበረም ልክ አዲስ አበባ እንደገቡ ከኢጣሊያን ጋር እየተመሳጠሩ ሲያስፈጁን የነበሩትን ወደ ስልጣን አመጥተው አስቀመጧቸው ። አርበኛው ምንም ነገር ሳያገኝ አንዲት ኒሻን አንጠልጥሎ ቀረ በዚህ እኛ አይከፋንም ምክንያቱም እያ የተዋደቅነው ለሹመት ለሽልማት ብለን አልነበረም ሃገራችንን ከወራሪዎች ነፃ ለማውጣት እንጂ እናንተ ልጆቻችን በነፃነት እንድትኖሩ አንገታችሁን እንዳትደፉ ብለው ነው ። አየህ ልጅ ምኒልክ ይች ሃገር ለሚሞትላት አትሆንም ለደማላት ለቆሰለላት አትሆንም ለሚገላት ለሚዘርፋት እንጂ ለዚች ሃገር የለፋ የወደቁ ሰዎች ዛሬ አስተዋሽ የላቸውም ወድቀዋል እኛ ልጆች ስላሉን ያው እንዲሁ አለን በዚች ሃገር ለዋልክላት ውለታ ላደረክላት ነገር ለከፈልክላት ውለታህን የሚከፍልህ ሆድህ ብቻ ነው ። አሁን እኔ ከንጉሡ ከደርግ ከወያኔ ብዙ ስቃይ ደርሶብኛ በዚህ ግን አልከፋም ምክንያቱም ሆዴ ለምን እንደዚህ አልሆንኩኝም አይለኝም ሁል ጊዜ ለሃገር የምትከፍለው ነገር ሁሉ ለህሊንህ ብለህ ነው !!!

አይ ፊት አውራሪ ገሞራ አባባላቸው አሁንም የጮጨ ተራራን አልፎ ጎጃምን አቋርጦ ይሰማኛል ። ይች ሃገር ውለታ ለሚውልላት አትሆንም ለጀግኖቿ አትሆንም በዚች ሃገር ቦታ ያላቸው ባንዳዎች ሃገር ሻጮች ታሪክ ቀባሪዎች ናቸው ። አይ እምዬ ኢትዮጵያ ሃገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ነው አይደል ያለው ያ ጀግና !!!

No comments:

Post a Comment