Friday, January 30, 2015

Golgul/ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ

ማክሰምና መሰንጠቅ – ባንዳና ባርነት
(ርዕሰ አንቀጽ)
http://www.goolgule.com/splitting-and-destroying-the-way-o…/
ህወሃት በዘረፈውና በሚዘርፈው ሃብት ተጠቅሞ ለወዳጆቹ የሚያኮራ፣ ትውልድ ለሚላቸው የሚበጅ ተግባራት እያከናወነ እንደሆነ ይነግረናል፤ ይነግሩናል። ውስን ባለሥልጣናትና አበሮቻችው በሃብት ተመንድገዋል። በንዋይ ሰከረው የሚያደርጉት እስኪጠፋቸው ናጥጠዋል። የት ጋር አንደሚያበቃ ባይታወቅም፣ የተደሰቱ፣ የተከፉ፣ የተናቁ፣ የተሰረቁ፣ የሚሰረቁ፣ እየሰረቁ ያሉ፣ የተትረፈረፈላቸው፣ በስማቸው የሚነገድባቸው፣ ባሪያዎችና ባንዳዎች፣ ቀን የሚጠብቁ፣ ጥርሳቸውን የነከሱ፣ … ወዘተ “አብረው” አሉ፡፡

ዘመን፣ ወራትና ቀናት ቅዠትን በመሰሉበት ዓለም፣ ቁራሽ ለሚሞላው ከርስ ራሳቸውንና ማንነታቸውን፣ ከዚያም አልፎ የትም የማይደበቁትን ኅሊናቸውን ያቆሸሹ፣ የአገር “እንግዴ ልጆች” ወይም “ውርጃዎች” ለህወሃት የማከሰምና የመግደል ሴራ ተላላኪ ሆነው የህዝብን ክብር ሰልበው ረክሰው ያረከሳሉ። ከዚህም በላይ ነገ እንደ ውዳቂ ላንቲካ መጣላቸውን እያወቁ፣ አሽከርነት፣ ከሃዲነት፣ ውርደት፣ መለያቸው እንዲሆን መርጠው ተሳቅቀው ይኖራሉ። እነሱን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባመነበት መንገድ እንዲጓዝ ለመታገል የሚውተረተሩትን ተኩላ ሆነው ያስበሏቸዋል።
ቅንጅትን በሉት። ቅንጅትን አሳረዱት። ተቀራመቱተ። የውስጥ ችግሩ እንዳለ ሆኖ እነርሱ ግን ዕጣ መድበው ተጣጣሉብት። አየለ ጫሚሶና ባልደረቦቻቸው “የክህደት ዋንጫ” ተሞላላቸው። ከዚያም ተጣሉ።
አሁን “ምርጫ” ደርሷል፤ ድንጋጤ ጨምሯል፤ የሕዝብ ሱናሚ አስፈርቷል፤ የህንጻውና የመንገዱ ሁኔታ አልበቃም፤ የሰዉ ህይወት ከመቅለሉ የተነሳ ለሚዛን አልበቃ ባለበት አገር ህይወቱ “በቀላል ባቡር ሊቀልል” ሽር ጉድ ይባላል፤ “ሥራ ላይ ነን፤ ምርጫ ደርሷላ”፤ አስተናጋጇ ህወሃት በለመደችው መንገድ ልታባብል ብዙ ትጥራለች፤ በየማዕዘኑም እያደባች ነው፤ እስከ “ምርጫ” ቤቷን አሳምራ ቄጠማ ጎዝጉዛ፣ ዕጣኗን አጫጭሳ “እንኮምር” እያለች ነው፡፡ ግን አልበቃትም፤ አላመነችም፤ ተጠራጥራለች፤ ተጨንቃለች፤ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን በተለይም አንድነትን ለማጥፋት “ቡና ጠጡ” በማለት የሚላላኩላት የቦርዱ “ምሁራን” ላይ ታች እያሉ ነው። ኃላፊው ለምን ይህንን የተላላኪነት ሥራ እንደፈለጉት ባይታወቁም የቦርዱ አሽከርካሪ ምክትላቸው ግን “የዜግነት” ድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ “ለወገን ደራሹ ወገን” አይደል የሚባለው! ስለዚህ ህወሃት የሰፈረውን “የሚያገለማ ጽዋ” ለመጋት ርኩቻው ደርቷል። ፕሮፌሰርነት ከሚሰጠው ክብር ይልቅ “ተላላኪነት” ኩራት ሆነ!
ሶስት ዓይነት ባርነት
በአገራችን ሶስት ዓይነት ባርነት እንዳለ ይነገራል፡፡ የእነዚህ ባሪያዎች (ባንዶች) ማንነት ገፍቶ የሚወጣው “ምርጫ” በደረሰ ጊዜ ነው፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው ባሪያ “ምርጫ ቦርድ” የሚባለውና ሌሎች መሰል “የተቋም ባሮች” ናቸው፡፡ ሁለተኛው ባሪያ ምርጫ ቦርድን እና ተመሳሳይ ተቋማትን የሚመሩ አመራሮች ናቸው፡፡ ሦስተኞቹ ባሮች ደግሞ ህዝባቸውን ለንዋይ ሲሉ የሚሸጡ አገልጋዮች ናቸው፡፡ በሌላ ቋንቋ ህወሃት የጠፈጠፋቸው፣ ያቦካቸው፣ የሚነዳቸው፣ ሲፈልግ አዋርዶ የሚያባርራቸው ናቸው፡፡ የዘመንና የትውልድ ሁሉ ተጠያቂ ባንዳዎች!
ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ የባርነቱን ዘመን ለማራዘም በለመደ እጁ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ላይ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ጡጫ ለማሳረፍ፣ ለመሰንጠቅ፣ ለማክሰምና ለማፍረስ ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ቅንጅትን በማፍረስ ታማኝ ሎሌነቱን እንዳስመሰከረ ሁሉ አሁንም ለህዝብ የእንግዴ ልጅነቱን ለህወሃት/ኢህአዴግ ደግሞ ታማኝ አሽከርነቱን ለማረጋገጥ እየተባ ይገኛል፡፡
እኛም እንደ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የባንዳዎችን ጥርቅም እናወግዛለን፡፡ ታሪክና ትውልድም ይህንን እንዳይረሱት እናሳስባለን፤ እንመዘግባለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የሚዘርፉትን፣ እየዘረፉ ያሉትን፣ የተዘረፉትን፣ እየተዘረፉ ያሉትን፣ ዘርፈው የሚያደርጉት የጠፋባቸውን፣ በሃብት የናወዙትን፣ በደም የተጨማለቁትን፣ የራባቸውን፣ ምርጫ ቦርድን፣ የኢህአዴግን ሎሌዎች፣ አሽከሮች፣ ሁሉ ይዛ እየነጎደች ነው፡፡ የጥጋቡም የግፉም ማብቂያ መቼ እንደሆነ ባይታወቅም የከፋቸውና ጥርሳቸውን የነከሱ እንዳሉ ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን፡፡ ንጹህ አገር ወዳዶችና እኛም ጎልጉሎች ያንን ቀን አንናፍቀውም፡፡ ባንዶች ግን ይህንን ቀን የማስቀረት አቅም አላችሁና ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ህዝብ ይምረጣቸው ወይም ይጥላቸው አንድነትንም ሆነ ሌሎቹን የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከራሳቸው ችግር ጋር ለህዝብ ውሳኔ ብትተዋቸው ይሻል ነበር፡፡ ነገርግን ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ እናንተም ዳግመኛ ባንዳነታችሁን አስመሰከራችሁ፤ ባርነታችሁንም ቀጠላችሁበት፡፡
*************************
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment