Thursday, January 1, 2015

የህግ የበላይነት እንዲከበር እና የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብቶችን ለመጎናጸፍ በጋራ የመታገል የግድ ነው
‪#‎Ethiopia‬ ‪#‎EPRDF‬ ‪#‎UDJ‬ ‪#‎AEUO‬ ‪#‎Blueparty‬ ‪#‎Medrek‬ ‪#‎MinilikSalsawi‬
Minilik Salsawi : ወያኔ/ኢህኣዴግ የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥሮ መንግስታዊ ሽብርን እያስፋፋ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳቶችን በህዝብ ላይ እያደረሰ መሆኑ የሚታውቅ ሲሆን ህዝቦች አስፈላጊውን የዜግነት መብቶቻቸውን እንዳያገኙ ሞራላቸውን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማሸበር እና በሃይል በመግደል የስልጣን መስፋፋቱን ቀጥሎበታል::
የወያኔ መንግስት ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል ነው እያለ ሲፅፍና ሲናገር እንሰማለን፡፡ ወያኔ/ኢህአዴግ ይህንን ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በአመለካከት ከኔ እስካልተለያየህ ድረስ ማለቱ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በአስተሳሰብ የተለየ እስካልሆንክ ሰው ብትገድል እንኳ በእርቅ ነፃ መውጣት ትችላለህ፡፡ ስልጣንህን ተገን በማድረግ የህዝብ ንብረትና ገንዘብ ብትዘርፍ ዘመነኛ ተብለህ ልትሸለማለህ ትችል እንደሆነ እንጂ ሙሰኛ አያሰኝህም፡፡

የወያኔ ጁንታ የፍትህና የጸጥታ አካላት ህግን ተመርኩዘው በህገወጥነት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል፡፡ እነዚህ የፍትህ አካላት የተባሉት የሚወስዱት ህገ-ወጥ እርምጃ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሳይሆን የወያኔን መንግስት ለሚቃወሙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በአጠቃላይ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመጫን የተመሰረቱ ይመስሉኛል፡፡ በማንኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ ፖሊስ መጀመርያ ግለሰቡን "ከወያኔ/ኢህአዴግ የፖለቲካ ታማኞች" አንዱ መሆኑን እና አለመሆኑን ከወያኔ/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ይሁንታ ካላገኘ የማሰር አቅም አይኖረውም፡፡
የፍትህ አካላትም ክስ የሚመሰረቱበትን የግለሰቡን ማንነት አስቀድመው ከወያኔ/ኢህአዴግ የፖለቲካ ታማኞች ውጭ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላቸዋል፡፡ ዳኞችም እንግዲህ በአንፃሩ ከወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት በአመለካከት ያልተለዩ ከሆኑ ወንጀል ቢፈፅምም ተጠርጣሪ ጠያቂ አለበት ማለት ይከብዳል፡፡ የፖለቲካ ታማኝነቱ ሳይታወቅ የተከሰሰ አባል እንኳ በችሎት ላይ እያለም ክሱ እንዲሰረዝለት የሚደረግበት አጋጣሚ አለ፡፡
የህግ የበላይነት ባልተከበረበት ሀገር ስለዴሞክራሲያዊ መብቶች ማንሳት ተገቢ አይደለም፡፡ ሁለቱን ለብቻቸው ነጥሎ ማየት ሁኔታውን ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ዴሞክራሲ እየገነባ እንደሆነ በየቀኑ ከመቶ ጊዜ በላይ ራሱ በሞኖፖል ይዞ በሚቆጣጠራቸው የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየነገረን ነው፡፡ በየጊዜው ይህንን ሃሰት እና የውሸት ዲስኩር እየሰማን መሄድ ማለት ሃገርን እና ህዝብን እያላሸቁ መሄድ ስለሆነ እያንዳንዳችን ለዲሞክራሲያዊ መሰረታዊ መብቶች መከበር የራሳችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል::የህግ የበላይነት እንዲከበር እና የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መብቶችን ለመጎናጸፍ በጋራ የመታገል የግድ ነው::

No comments:

Post a Comment