Friday, March 24, 2017

አየር ኃይል ውጥረት ውስጥ ገብቷል፤ 11 አብራሪዎች ታስረዋል

በደብረ ዘይት የሚገኘው የአየር ኃይል ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሆነ ምንጮች ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያውያን ፓይለቶች አታበሩም ተብለው ግራንድ ከተደረጉ በኋላ ከምስራቅ አውሮፓ የመጡ ቅጥረኞች ብቻ እንዲያበሩ መወሰኑን ተከትሎ 40 የሚሆኑ አብራሪዎች የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል፤ መልቀቂያ ያስቡት አብራሪዎች ግዳጃቸው እስከሚቀጥለው ሐምሌ ወር ድረስ ብቻ እንደሚሆንም ታውቋል፡፡
የአገልግሎት ጊዜያቸው ገና በመሆኑ ምክንያት መልቀቅ የማይችሉት አብራሪዎች ሥራቸውን ጥለው እየጠፉ እንደሆነ የሚናገሩት የመረጃ ምንጮች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ አራት የዐማራና ሰባት የኦሮሞ ተወላጅ አብራሪዎች ሲጠፉ ተይዘው ታስረዋል ተብሏል፡፡ ከታሰሩት አብራሪዎች መካከል አንድ የዐማራ ተወላጅ አብራሪ የደረሰበት እንደማይታወቅና ከጎንደር የሔዱ ቤተሰቦቹ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ሊያገኙት እንዳልቻሉ ነው የተነገረው፡፡
ሌላው ለውጥረቱ መንስኤ ነው የተባለው በከፍተኛ ጀነራሎቹና በታችኛው እርከን ላይ ባሉት መካከል ልዩነት መፈጠሩ ነው ያሉት ምንጮች ወታደራዊ እዝና ተዋረድ መተግበር ካቆመ እንደሰነባበተ ገልጸዋል፡፡ ለአየር ኃይል አባላት በየትውልድ ቦታቸው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተፈቅዶላቸው የነበረውን አፈጻጸም ላይ ችግር መኖርም ሌላው የውጥረቱ መንስኤ ነው ብለዋል፡፡ የአየር ኃይል እማኞች እንደሚሉት በአየር ኃይል ግቢ ውስጥ የተፈጠረው ውጥረት ከመቼውም ጊዜ የተለየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
Muluken Tesfaw

No comments:

Post a Comment