Sunday, March 26, 2017

"(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)" ******************************* ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ




የስልጣን ዕድሜን ከማራዘምና ከማራዘም ባለፈ ምንም አይነት ህልም የሌላቸው የወያኔው ቡድን ባለስልጣናት የህዝብና የአገርና ጥቅም ከቶ አይታሰብም። የህዝቡ የኑሮ መሻሻልና የመልካም አስተዳደር ባለቤትነት አስጨንቋቸው አያውቅም። የሃገር ሉዓላዊነት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ወዘተ ለደቂቃም ቢሆን አሳስቧቸው አያውቅም። ስልጣናችንን ይጋፋናል ወይም ይነጥቀናል ብለው የሚሰጉት ማናቸውም በተናጥልም ሆነ በግል የሚደረጉ የህዝባዊ ወገንተኝነት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለማዳፈን የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም። ይገድላሉ፣ያስራሉ፣ለመግለጽ በሚያስቸግር መልኩ ይደበድባሉ፣ያስፈራራሉ … በአጠቃላይ አገዛዙ ከህዝብ ጋር የሚያቆራኘውና በስልጣን እንዲቀጥል የሚያስችል ቅንጣት ታክል የሞራል ልዕልና የለውም። በተስፋ መቁረጥ ተዘፍቆ የሚያደርገው ጠፍቶት የሚባዝን ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ስርዓቱ ከሚታወቅበት መሰረታዊ አቋሙ ተንሸራቶ የባጥ የቆጡን ሲዘላብድ ለተመለከተው የዕውር ድንብር ጉዞ ውስጥ እንዳለ ይገነዘባል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ከተመሰረተ አንስቶ አገርና ህዝብን እያጠፋ ካለው ወሮበላው የወያኔ ቡድን ጋር ሁለንተናዊ ትግል እያካሄደ ይገኛል። 
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአንድ ሳምንት ባካሄደው ጥልቅ ስብሰባ የንቅናቄውን ስትራቴጂ የፈተሸበትና ወቅታዊ የአገራችንን ሁኔታ በስፋት የታየበት ሙሉ መግባባት የደረሰበት ነው። በድርጅቱ ውስጥ ያሉ አጠቃላይ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት ለችግሮቹም የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀመጠበት ነው። በህዝባችን ላይ በሃይል የተጫነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንድምታ የተቃኘበትና ከአዋጁ ጋር በተያያዘ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች የወሰነበት ነው። በተለይም አገር ውስጥ ባለው የሕዝባዊ አመጽና የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ላይ አመራሩ ሙሉ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም የለውጥ ትግሉ ለማፋጠን በአገራዊ ወኔ ተነሳሽነት መንፈስ የተነሳበት ነው። በአገር ውስጥና በውጭ ያለው የፖለቲካ አሰላለፍ የታየበትና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ከወዲሁ እነደ ድርጅት በተናጥልና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ስምምነት የተደረሰበት ነው። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከንቅናቄው ስትራቴጂ በመነሳት የስራ ቅደም ተከተል በማስቀመጥ ከስራው ጋር በተገናኘ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማደላደል በቁርጠኝነት መንፈስና በተናበበ አሰራር የአገር ውስጥ የለውጥ ትግሉ ከነበረው የበለጠ አቅም ለመገንባት የወሰነበት ነው። 
በአብዛኛው የአገራችን ኢትዮጵያ ክፍሎች ህዝቡ ያደረገውንና እያደረገ ያለውን ትግል ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በጭካኔና በጉልበት ለመቀልበስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣ ቢሆንም ዛሬም ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ ያለውን አይበገሬነት ከበፊቱ በተጠናከረና የወያኔን ጥቃት እንዳመጣጡ በመመከት አኩሪ ተጋድሎዎችን እያደረገ ነው። አርበኞች ግንቦት ሰባት ከህዝቡ ጋር በመሆን በሁለንተናዊ መልኩ የለውጥ ጥረቱን በመደገፍ፣ በማስተባበርና በመምራት ያለ የሌለ ሃይሉን በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ደራሽነቱን ያረጋግጣል።
አምባገነኑ አገዛዝ በህዝባችን ላይ በግፍ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለመታደግና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መላው የአገራችን ሕዝብ በህዝባዊ እምቢተኝነት፣ በህዝባዊ አሻጥር ፣በህዝባዊ አመጽና በውጪው ዓለም በሚደረገው አገር አድን እንቅስቃሴ ዛሬውኑ በመሳተፍ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣና የተቃዋሚ ሃይላት በትናንሽ ልዩነቶች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ተቀብለውና ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጎናጽፎ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ድርጅቶችን ለስልጣን እስከ ሚያወጣ ድረስ ልዩነቶቻቸውን አጥበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ በጋራ እንዲነሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል። 
 የስብሰባው ተሳታፊዎች ፡-
1, አርበኛ ታጋይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ሊቀመንበር
2, አርበኛ ታጋይ መአዛው ጌጡ - ምክትል ሊቀመንበር
3, አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወልደስላሴ - የፖለቲካ መምሪያ ሃላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
4, አርበኛ ታጋይ ገበየሁ አባጎራው - የመረጃና ደህንነት መምሪያ ሃላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
5, አርበኛ ታጋይ ተስፋሁን ተገኘ - የስልጠናና ትምህርት መምሪያ ሃላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
6, አርበኛ ታጋይ ታሪኩ ግርማ - የአስተዳደር መምሪያ ሃላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
7, አርበኛ ታጋይ ኮማንደር አሰፋ ማሩ - የወታደራዊ መምሪያ ሃላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
8, አርበኛ ታጋይ ኑርጀባ አሰፋ - የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
አንድነት ሃይል ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
መጋቢት 16/2009 ዓ/ም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

No comments:

Post a Comment