መጋቢት 12 ቀን 2009 ዓ. ም.
ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሠራዊት አባላት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር በህወሓት/ኢህአዴግ የአገዛዝ ሥርዓት ተቋማት ላይ የተቀናጀ የሽምቅ ጥቃት አድርሰዋል። በማክሰኝት፣ በደጎማ፣ በጯሂት፣ በደንቀዝን፣ በበለሳ፣ በአዲስ ወረዳ፣ በደንቢያ፣ አገዛዙ ቀይ ቀጠና ብሎ በሰየመው በመተማ መስመር በጭልጋ ወረዳ፤ በቆላድባ፣ አብራጂራ፣ በቸንከር ቀበሌ በአገዛዙ የፓሊስ ጣቢያዎችና የጦር ሠራዊት ካምፓች እንዲሁም ቀንደኛ የሥርዓቱ አገልጋዮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሯል፤ በሕዝብ ላይ በደል ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩ የሥርዓቱ ቀንደኛ አራማጆች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዷል። ስለእነዚህ እርምጃዎች በወቅቱ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያሻም።
ይህ የፍፃሜው ጅማሮ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ህወሓት/ኢህአዴግን በማስወገድ ሕዝብ የፓለቲካ ስልጣን ባለቤት ለማድረግ በሚደረግ ትግል ውስጥ ራሱን ለመስዋዕትነት በግንባር ቀደምትነት አሰልፏል፤ የትግሉ ባለቤት ግን ሕዝቡ ራሱ ነው።
እስካሁን በጎንደር በተደረጉ ትግሎች የታየው የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ አበረታች ነው። የጎንደር ሕዝብ ከአብራኩ የወጡትን የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን በመረጃ፣ በስንቅና በቀጥታ በውጊያ በመሳተፍ ረድቷል። ሲራቡ እያበላ፣ ሲቆስሉ እያስታመመ፣ መንገድ እየመራ ግዳጆቻቸውን በስኬት እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል። በተለይ እሁድ መጋቢት 03 ቀን በጎንደር አጼ ፋሲለደስ ስታዲዮም የተገኘው ሕዝብ የአገዛዙን ዛቻ ሳይፈራ ለታጋይ አርበኛ ጎቤ መልኬ የህሊና ፀሎት ማድረጉ ለአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗል። ሰሞኑን እየተወሰዱ ያሉትን ዓይነት የሕዝባዊ አመጽ እርምጃዎች ከጎንደር በተጨማሪ ወደ ሌሎችም የአገሪቱ ግዛቶች እንዲስፋፋ ማድረግ ይገባል።
የአገዛዙ ሠራዊት በርካታ አባላትም ታጋዮችን እያዩ እንዳላዩ በማሳለፍ፤ ጥይት አየር ላይ በመተኮስ እና የይስሙላ አሰሳዎችን በማድረግ አባል በሆኑበት ፋሽስታዊ ሠራዊት ላይ ሕዝባዊ የሆነ አሻጥር በመፈፀም ተባብረዋል። ከፊሎች ደግሞ ከዚህም በላይ በመሄድ መረጃ በማቀበል በውስጥ አርበኝነት አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ለእነዚህ የሠራዊቱ አባላት ያለውን አድናቆትና ክብር ይገልፃል። ለወደፊቱ ከዚህ በላይ የሆነ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል። ኢትዮጵያ አገራችን የሁላችን ናት፤ የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ስም ይዞ ለህወሓት/ኢሕአዴግ ጥቅምና ሥልጣን መቆሙ ማብቃት አለበት። በአገዛዙ የጦር ሠራዊት ውስጥ ያለውን የሀሳብ ልዩነት አርበኞች ግንቦት 7 በቅርበት ይከታተላል። “እኛ ሠራዊቱን የተቀላቀልነው ወራሪ ጠላትን ለመከላከል እንጂ መብቶቻቸውን የጠየቁ ዜጎችን ለመፍጀት አይደለም” በማለት የሚከራከሩ የሠራዊቱ አባላት እንዳሉ ንቅናቄዓችን ያውቃል። እነዚህ የሠራዊቱ ወገኖች አብዛኛውን ሠራዊት ለማሳመን እንዲጥሩ ያ ካልሆነም ሠራዊቱን ጥለው በመውጣት ንቅናቄዓችንን እንዲቀላቀሉ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
የህወሓት ተቀጥያ እና ግንባር ቀደም አጋር በሆነው ብአዴን ውስጥም የሕዝብ እሮሮና እንባ እረፍት የሚነሳቸው ወገኖች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ወገኖች የህወሓት ሎሌዎች በሆኑ የብአዴን አባላት እየተመነጠሩ ከሥልጣንና ከሥራ እንደሚባረሩ፣ እንደሚታሰሩና እንደሚሰደዱ እያየን ነው። ልቦና ያላቸው የብአዴን አባላት ከሕዝብ ጎን ለመሰለፍ ከአሁን የተመቸ ጊዜ ላያገኙ ይችላሉ፤ ስለሆነም ዛሬውኑ ጎራቸውን እንዲለዩ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደረጋል።
በህወሓት የአገዛዝ ዘመን በአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰው በደል ዘርፈ ብዙ ነው። መሬቱ ተዘርፏል፤ ማንነቱ ተደፍሯል፤ በገዛ አገሩ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ዜጋ እንዲሆን ክብሩ ተዋርዷል። አማራን እርስ በርሱ በማጣላት እንዲዳከም ብዙ ተዶልቷል፤ እየተዶለተም ነው። በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት የዚህ ሁሉ በደል ማብቂያ ቁልፍ መፍትሄ ህወሓትን ከኢትዮጵያ የፓለቲካ ስልጣን ማስወገድ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ወንበር ላይ እስካለ ድረስ ማናቸውም ዓይነት መብቶች አይከበሩም። በህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የስብዕናና የዜግነት መብትን መጠየቅ በሽብርተኝነት የሚያስከስስ ወንጀል ነው። በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ሥር ሆነን መብትን ለማስከበር የምናደርገው ትግል የትም አያደርሰንም፤ ያለን መፍትሄ አገዛዙን ማስወገድ ነው። በዚህም ምክንያት መብቶቻችንን ለማስከበር ተገደን ወደ ጦርነት ገብተናል። ድል እስከምናደርግ ድረስ የሚቆም አይደለም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ የማውጣት ኃላፊነት የወደቀው በአማራ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊያን ሁሉ ላይ ነው። ስለሆነም አገዛዙን ለማስወገድ የሚደረገው ተጋድሎ ከአማራ ውጭ ወደሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲስፋፋ አርበኞች ግንቦት 7 ጠንክሮ ይሠራል። መላዋ ኢትዮጵያ ነፃ ካልወጣች አንድ አካባቢ ብቻ ተለይቶ ነፃ ሊወጣ አይችልም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በታጋይ ወላጆች፣ አያቶች፣ አጎቶች፣ ባለቤቶችና ሕፃናት ልጆች ላይ ፋሺስታዊ ጥቃት ማድረስ እየበረከተ መጥቷል። የበርካታ ታጋዮች ሕፃናት ልጆች ተደብደበዋል፣ ታስረዋል፣ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ከብቶቻቸው ተግዘዋል። በአርበኛ ታጋይ ቤተሰቦች ላይ የበቀል እርምጃ በሚወስዱ የሥርዓቱ አገልጋዮች ላይ ምህረት የለሽ አፀፋ የሚሰጥ መሆኑን በደል ፈፃሚዎች እንዲገነዘቡ አርበኞች ግንቦት 7 በጥብቅ ያሳስባል። አርበኞች ግንቦት 7 እንዲህ ዓይነት እጅግ ኃላቀር የሆነ የበቀል ሥርዓት ፈፃሚዎችን ከመቅጣት እንደማይመለስ እንዲያውቁት በአጽንዖት ያስገነዝባል።
ባለፉት ዓመታት ሞቅ ደመቅ ሲል የቆየው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በተደራጀና በተጠናከረ መንገድ እንደገና እንዲቀሰቀስ የማደራጀት፣ የማስተባበርና በግንባር ቀደም የመምራት ተግባር እንዲያከናውኑ አርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎቹን ያሳስባል። ከእንግዲህ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽ ተደጋግፈው እንዲሄዱ ይደረጋል።
ዛሬ እያንዳንንዱ ኢትዮጵያዊ ጎራውን እንዲለይ የሚጠየቅበት ወቅት ላይ ተደርሷል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ውሳኔውን ራሱ መስጠት አለበት። ምርጫው ሁለት ነው። አንደኛው አማራጭ ከበዳዮች፣ ዘራፊዎች፣ ገዳዮች ከሆኑት ህወሓት እና እሱ የፈጠራቸው ድርጅቶች ጎን መቆም ነው። ሁለተኛው አማራጭ ሕዝብን ለስልጣን ባለቤትነት ለማብቃት መስዋትነት እየከፈሉ ካሉት አርበኞች ግንቦት 7 እና አጋሮቹ ጎን መቆም ነው። ሦስተኛ አማራጭ የለም።
በዚህም ምክንያት በግል ተነሳሽነት ጭምር የተሰባሰባችሁ ወገኖች በድርጅት በመታቀፍ ውጤት ለሚያመጣ የጋራ ትግል ኃይላችሁን አስተባብሩ። የተናጠል ትግል እምንመኘው ግብ እንደማያደርሰን ተገንዝበናል። ስለሆነም መተባበር ብቻ ሳይሆን በድርጅት ታቅፎ መታገልን ባህል እናድርገው። በጋራ ትግል አምባገነኑን የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝን አስወግደን የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እናድርግ።
አንድነት ኃይል ነው !!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!
No comments:
Post a Comment