ለነጻነት በሚደርገው ትግል ኢትዮጵያውያን በአቅማቸውና በሙያቸው አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ጥሪ አቀረበ።
በአራት ድርጅቶች በቅርቡ የተመሰረተው ሃገራዊ ንቅናቄ በዋሽንግተን ዲሲ ከኢትዮጵያን ጋር ባካሄደው ውይይት በሀገሪቱ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መሰረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ፣ እና የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በጋራ የመሰረቱት የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ዕሁድ የካቲት 26, 2009 በዋሽንግተን ዲሲ በደብዳቤ ጥሪ ከተደረገላቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረገው ውይይት በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያን አንድነትና በህዝባዊ ዕምቢተኝነት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል። በትግሉ ውስጥ ሴቶች ስለሚኖርባቸው ተሳትፎም ተወስቷል።
“የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ” በሚል ጥርት ያለ ስያሜ ስንነሳ በቅንነት ኢትዮጵያውያንን ቀርበን ማወያየት፣ ማነሳሳትና፣ ማሳተፍ ከቻልን፣ በዚሁ ንቅናቄ አማካኝነት የምንወስዳቸው ዕርምጃዎችን ሙሉ ውጤታማ ልንሆን የማንችልበት ምክንያት የለም የሚል ሙሉ ዕምነት ይዘን ነው በሚል መድረክን የከፈቱት የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ በመወከል ዝግጅቱን ያስተባበሩት አቶ ዘውዴ ጉደታ ሲሆኑ፣ ከእርሳቸው የመግቢያ ንግግር በኋላ የአባል ፓርቲ ተወካዮች አጭር ንግግር አድርገዋል።
ከአርበኞች ግንቦት 7 አቶ ነዓምን ዘለቀ፣ ከሲዳማ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አቶ በቀለ ዋዩ እንዲሁም ከአፋር ህዝብ ፓርቲ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ እና ከኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አቶ ሌንጮ ባቲ በየተራ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄን በተመለከተ በሰጡት አጭር መግለጫ የተጀመረው ውይይት ሙሉ ቀን የፈጀ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚል ርዕስ ገለጻ ያደረጉት ተጋብዘው የተገኙት አርኪዖሎጂስቱ ዶ/ር ዮሃንስ ዘለቀ፣ ኢትዮጵያን በአለም ላይ ቀደምት መንግስታት ካለባቸው ሃገራት አንዷ መሆኗንና ህዝቧ የሰው ዘር ምንጭነት አስታውሰው፣ ለ 2ሺ 500 ዓመታት ባልተቋረጠ፣ በ50 እና 30 አመታት በሚያገረሽ ጦርነት ማለፏን ወደኋላ እንደጎተታት ዘርዝርዋል።
የሴቶች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በመዘርዘር በዕለቱ ጽሁፍ የቀረበው ፋሲካ ወልደሰንበት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ከንግስት እሌኒ ጀምሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉል ሚና እንደነበራቸው በማስታወስ ከዘመኑ ጋር እያደገ መሄድ የሚገባት ቢሆንም፣ ደካማ ሆኖ መቀጠሉን ዘርዝረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን በመዳሰስ በኢትዮጵያ የነበሩትም በማስታወስ መድረኩ ጽሁፍ ያቀረቡ አቶ ኮነ ፍሰሃ በህዝባዊ ዕምቢተኝነት ውስጥ ጀግኖች መሪዎች እንዲሁም አክቲቪስቶች የሚኖራቸውን ሚና ዘርዝረዋል።
የህዝባዊ ንቅናቄ አስሩ ህግጋት በሚል ርዕስ ገለጻ ያደረጉትን በተሳታፊዎች መካከል የተደረገውንም ውይይን የመሩት ዶ/ር ጌብ ሃምዳ ሰፊ ገልጻ አድርገዋል። የዕለቱ ፕሮግራም ከተደመደመ ህዝባዊ ስብሰባዎች በተለይ ተሳታፊዎች ጭምር በቡድን እየተከፋፈሉ ሃሳብ የተለዋወጡበትና ይህንንም ሃሳባቸው በጋራ የመከሩበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። በሃገሬው አቆጣጠር ጠዋት 9 ሰዓት ላይ ጀምሮ ማታ 6 ሰዓት የተጠናቀቀው ውይይት ያሳረጉት የንቅናቄው ስ/አስፈጻሚ ሊቀመንበር ዶ/ር ዲማ ነገዎ ናቸው።
No comments:
Post a Comment