Saturday, March 4, 2017

‹‹ስለ እኔ አታልቅሱ!›› by MulukenTesfaw


Image may contain: 1 personየሚፈግ እሳት፤ የማይጠፋ ፋና! አርበኛ ሰማዕት ጎቤ መልኬ (ከ1958 – 2009 ዓ/ም)
ምን ብየ እንደምጀምር አላውቅም፤ ግን እኛ ‹‹ዋዋ›› እያልን ለምንጠራው አባታችን
ቤተሰቦቹ ደግሞ ‹ጃውይ› እያሉ በፍቅር ለሚጠሩት የዘመናችን ታላቅ ሰማዕት የ51
ዓመቱ ጎቤ መልኬ መናገር አለበኝ፡፡ አዎ! ማክሰኞ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም
ከሕይወቴ እኩይ ቀኖች በቅድሚያ እመድባታለሁ፤ ተደጋግሞ የተደወለ የስልክ ጥሪ
ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ፤ ከስልኩ የሰማሁት ነገር መንቃቴን መልሼ እንድጠራጠር አደረገኝ፤
ምናለ በሕልሜ በሆነ አልኩ!
የአንዳንድ ሰዎች የወገን ፍቅር ይገርመኛል! ሀብትና ንብረት ግድ የማይሰጣቸው ጥቂት
ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሕይወታቸውን ለወገን አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎች ግን ጥቂቶች
ናቸው፡፡ ለእኔ አርበኛው ጎቤ መልኬ እንደዚያ ነው፡፡
ጃውይ ጎቤ መልኬ! የሚፈግ እሳት የማይጠፋ ፋና!
ትውልዱ እንዲህ ነው፡፡ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት በጠገዴ ወረዳ አዴት ቊስቋም ከአባቱ
አቶ መልኬ ተገኘ ከናቱ ይሳለም ደምለው በ1958 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ለዋዋ ሕይወት
አልጋ በአልጋ አልነበረችም፡፡ አባቱን በለጋ እድሜው በሞት ተነጠቀ፤ የቤተሰብ ኃላፊነት
ገና በ17 ዓመቱ ተጣለበት፤ ግን ኃላፊነቱን የማይወጣ ዋልጌ አልነበረም፤ በድፍን
አርማጭሆና ጠገዴ ስሙ የገነነ ገበሬ ሲሆን ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ጃውይ ፈጣን ንቁ
የወገን ያገር መከታ ሁኖ አደገ፡፡ መንጠሩነን መንጥሮ ዳጉሳ ከጅሆላ እያመረተ
ከቤተሰብ አልፎ በሰኔ በሐምሌ ድፍን ጠገዴ ከእነርሱ ቤት ሲበላ ሲጠጣ ስሙ
ከአጽናፍ አጽፍ ገነነ፡፡
በግብርናው ወደር የሌለው አራሽ አደፋራሽ ሆነ፤ ላሙ ቦራ ቦራ፣ በሬው ዛጎላ፣ እቦሳው
ሶራ፣ ፍየሉ ወያይ፣ ማንም ደራሽ የሌለው ስለመሆኑ ዋሕብቴ ጀጀቢት በርሃ ይመስክር!
ዋዋ ጎቤ ላገር መከታ ልበሙሉ ዘመን ባመጣው ቴክኖለጅ ቀዳሚ ተራማጅ ብቻም
ሳይሆን ተፈላሳሚ ነበር፤ ሳይማር ያወቀ የወንዶች ወንድ፣ ካልነኩት የማይነካ አንበሳ
ነበር፡፡ በሌላ በኩል ጃውይ የተጣላ አስታራቂ፣ የተገፋ ጠያቂ፣ የታሰረ አስፈች፣ የተራበ
መጋቢ፣ አግዳሚው አላፊው ዘወትር እንደ አብርሃም ቤት ቤቱ ከእግዳ የማይለየው
ጃውይ ጎቤ ነበር፡፡ ጃውይ በአገሩ ሰው እጅግ የተወደደ ወደር የሌለውም ጀግና ነበር፤
በሃይማኖቱ እና በአገሩ ቀልድ የማያውቅ ወደፊት እጅ ወደኋላ የማይል ጀግናዎች
መካከል ሰው ቢፈለግ ጎቤ መልኬ ቅድሚ ስሙ አለ፡፡
ጃውይ ማለት ልቡ የማይደነግጥ ደፋር ለወዳጁ ማር ለጠላቱ ኮሶ ነው፤ ዋሽ ከሆነ
ድፍን አርማጭሆና ወልቃይት ጠገዴ ይመስክር፡፡ ተቆጥቶ ካያችሁት እንደአንበሳ
ያስፈራል፤ ሲጫወት ሲስቅ ደግሞ ርግብ የዋኅ ነሰው ነበር፡፡
በንግዱ በኩል የተዋጣለት ነጋዴም ነበር፡፡ አርማጭሆ ሳንጃ ከተማ መካከል አላፊው
አግዳሚው ድራፍት ከወይን ከፍየል ቁርጥ ጋር የሚያወራርድበት ሆቴል ነበረው፡፡
አርማጭሆ ጠገዴ የሚገናኝበት መስከረም ሲጠባ የሰባ ሰንጋ አርዶ የሚዘክርበት
ጠላው በገምቦ የሚወርድበት ጥሎሹ ተዘርግቶ ቄስ ከመለኩሴ ዲያቆን ተሞሃይ
የሚዘምርበት፣ የጃውይ ማጀቱ ወልወሉ የሚትረፈረፍበት አብልቶ አጥቶ ውሎ
የሚያድርበት ጃውይ ቤቱ የእነአብርሃም የሳራ ዘመን ያለን የሚመስልበት ነበር፡፡ ይህን
ሁሉ ለሰው ሲነግሩት ተረት ይመስል ይሆናል፤ ግን ከአርማጭሆ ሰው በላይ ምስክር
የሚሆን የለም፡፡
ዘመናዊ ትምህርት ቤት አልገባም፤ ግን አስተሳሰቡ ዩንቨርሲቲ ገብተው ዲግሪ በጥሰው
ከወጡ ሰዎች በላይ ነው፤ ከማንም በፊት መኪና ገዝቶ ራሱ ያሽከረክርም ነበር፡፡
የነበረው የፍየል ቁጥር በትክክል አይታወቅም፤ ሦስት ያክል መኪናዎችና የባለብዙ
ሚሊዮን ብር ባለንብረትም ነበር፡፡ ግን ይህ ሁሉ ለዋዋ ከወገን ፍቅር በላይ
አልበለጠበትም፡፡
አርበኛ ጎቤ እንዴት የወያኔ መንግሥት ላይ ነፍጥ ሊያነሳ ቻለ?
የዋዋ እና የወያኔ ጠብ አሁን የተጀመረ አይደለም፤ ከ1983 ዓ.ም በፊትም ይቀድማል፡፡
ወያኔዎች ገና ሥልጣን ሳይዙ በወልቃይትና በጠገዴ አካባቢ በዐማሮች ላይ
የሚያደርሱት ጥፋት ያሳስበው ነበር፡፡ አስቦም ዝም አላለም፡፡ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ
የወያኔ መንግሥት ክልሎችን ሲያዋቅር የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ወደ ትግራይ
መከለልን ተቃውሞ ከወንድሞቹ ጋር ነፍጥ አንስቶ ነበር፡፡ በጊዜው በመረጃ እጥረት
ሌላው የዐማራ ሕዝብ በአካባቢው የሚሆነውን ባለመዋቁ ምክንያት እንቅስቃሴው ያን
ያክል ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡
ጃውይ ጎቤ መልኬ ከወያኔ ጋር እርቅ ሰላም የሚባል ነገር ኖሮት አያውቅም፤
በ2006/7 በወያኔዎች የማስፋት እቅድ ግጨው አካባቢን አልፈው ለመያዝ ባደረጉት
ጦርነት እነ ጎቤ መልኬ ተሳታፊ ብቻም ሳይሆን የጦርነቱ መሪዎች ነበሩ፡፡ አቶ ዓባይ
ወልዱ የክልላቸውን የፖሊስ አባላት እስካ አፍንጫቸው አስታጥቀው ሲቪል አልብሰው
ነበር ወደ ግጨው የላኳቸው፡፡ የወንዶች ቁና ጎቤ መልኬ ከአርማጭሆና ከጠገዴ
ወጣቶች ጋር በመሆን ነበር ከነትጥቃቸው በጫካዎች ውስጥ አመድ ያደረጋቸው፡፡
ወያኔዎች ቀንዳቸውን ተብለው ፖሊሶቹም በጫካዎች ውስጥ ረግፈው ነው እቅዳቸው
የተኮላሸው፡፡
የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ብሔርተኛነት የማንነጥ ጥያቄ እዚህ እንዲደርስ ከታገሉት
ሰዎች መካከልም ቅድሚያ ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል ጎቤ አለ፡፡ በሕግ አግባብ
እንዲያልቅ የሚችለውን አደረገ፤ ወያኔ ግን በኃይል ሊደፍቀው ፈለገ፡፡
ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ/ም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ እነ አታላይን፣ እነ ጌታቸው
አደመን እና ሌሎች የኮሚቴ አባላት ወያኔ ሲያፍን ጎንደር ከተማን ያጨናነቀው የጎቤ
ጦር ነበር፡፡ ከብልኮ እስከ አውቶ ፓርኮ ድረስ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የጎቤ ጦር
ተሰልፎ ሲመለከቱት አጼ ኃይለ ሥላሴ ከስደት መልስ ቤተ መንግሥት ሲገቡ የነበረውን
ግርማ ሞገስ የተላበሰ ትርኢት ይመስል ነበር፡፡ በዚህ ቀን ጎቤ አንድ ትልቅ ንግግር
አደረገ፡፡ ‹‹ብአዴን የሕወሓትን የበላይነት ጥሎ ለሕዝብ ከቆመ መልካም፤ ካልሆነ ግን
እኛ የምናደርገውን እናውቃለን›› አለ ጎቤ፡፡
ለቃሉ ሟቹ ጎቤ የተናገረውን በተግባር ነው ያሳየው፡፡ ጎቤ ከዚያን ቀን በኋላ
በአርማጭሆና በቆላ ወገራ ያደረጋቸው የጦር ሜዳ ውሎዎች በሌላ ክፍል
እመለስባቸዋለሁ፡፡
እንግዲህ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም በጠዋት የዚህ ጀግና መስዋት መሆን ነበር
የሰማሁት፡፡ እንደሰማሁ ዝም አላልኩም፤ ደጋግሜ ከወንድሞቼ ጋር ተነጋገርንበት፡፡
ጀግናው ሞቷል፤ ግን ደግሞ ጀግናው አለ፡፡ ማክሰኞ ዕለት ብቻ እስከ አንድ ሺህ
የሚደርስ ጎቤን በተመለከተ በሕይወት ስለመኖሩ እንደነግራቸው ጠየቁኝ፡፡ ምን ብየ
ልመልስላቸው? ወንዱ ሞተ ልበል?
ዋዋ እኮ በአካሉ የሞተው ገና ያን ሁሉ ሀብት ንብረት ጥሎ ጫካ የገባ ዕለት ነው፤ ግን
ጀግንነቱ እንደ ዓድዋ ጀግኖች በዘመን ሁሉ ሲታወስ እንደሚኖር ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶች
ስለሞቱ ብዙ ጻፉ፤ ብዙም አለቀሱ፡፡ ዋዋን አሁን አግኝቼ ብጠይቀው ‹‹ስለ እኔ
አታልቅሱ›› እንደሚለኝ አልጠራጠርም፡፡ የእርሱ ፍቅር እኮ ሕይወትን አሳልፎ እስከ
መስጠት ነው፡፡
የጎቤ ታላቅነት በጀግንነቱ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ የአንድ መሪ ታላቅነት የሚለካው
ተተኪ መፍጠር ሲችል ነው፡፡ በዚህ ጎቤ የሚታማ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ብቻ
አይደለም፤ ብዙ ጎቤዎች ተፈጥረዋል፡፡
በመጨረሻም በጎቤ የቅርብ ዘመድ ናትናኤል ሞላ የተገጠመ የሚከተለውን ግጥም
በማስከተል ለጊዜው ጽሑፌን ልጨርስ፡፡
ወልቃይት ጠገዴ የሚወለደው፡
ጪልቋና አርማጪሆ የሚወለደው
ያባ ደፋር ልጅ አገር ያወቀው!
ያባደፋር ልጅ ጃዊ ሚሉት!
ባለ መኪና ባለ ጥገት፡
ትውልዱ አመራ ትውልዱ አዴት፡፡
አረ ዋዋየን የነካው ማነው?
ያገሬ ኩራት መመኪያችን ነው!
ታንክ መትረጊሥ የማይበግረው፡
ባንዳ ወያኔ ፈርቶት ሚኖረው፡
ላገር ነፃነት ጫካ የሄደው!
ያለ ነፃነት ሀብት ምን አለው?
ቆራጡ ጀግና ዋዋ ነው ያለው!
ምኑን አውርቸ ምኑን ልተወው፡
ድንበር ጠባቂ ያገር ኩራት ነው!
የከብቱን ብዛት ያየ ይናገር!
የበጉን ብዛት ያየ ይናገር!
የመኪናውን ያየ ይናገር!
የጠገዴው ወንድ የናጅሬ ዘር
ይቅርብኝ ብሎ ገባ ወደዱር፡፡
ሊሠርቅ አይደለም ሊቀማ አይደለም!
የነ ሥጦታው የናይቶ ወንድም!
መልመጥመጥና መፍራት አይወድም!
(ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው የአርበኛ ሰማዕት ጎቤ መልኬ የቅርብ ዘመድ ናትናኤል ሞላ
በሰጠን መረጃ መሠረት ነው፤ እናመሰግናለ፡፡ የጎቤን የጦር ሜዳ ጀብዱዎች በቀጣይ
እናቀርባለን)፡፡

No comments:

Post a Comment