Friday, March 10, 2017

አርበኞች ግንቦት 7 በሰሜን ጎንደር ጥቃት ፈጽሞ እስረኞችን አስለቀቀ


የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሃይሎች በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ ችንፋዝ በገና ሲናሪክ ከተማ ሰርገው በመግባት በፈጸሙት ጥቃት እስረኞችን አስለቀቁ።
ታጋዮቹ ትናንት የካቲት 30: 2009 አም ምሽት ከ4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት በከተማ ባሉ የመንግስት ታጣቂዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች ገድለዋል።
የተወሰኑ የከተማዋ ታጣቂዎች ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጋዮች ድጋፍ በመስጠት በህወሃት ኢህአዴግ ወታድሮች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ከፊሎችም የአርበኞች ግንቦት 7 ሃይሎችን ተቀላቅለዋል።
በዚሁ ጥቃት የተደናገጠው የህወሃት/ኢህአዲግ ጦር ተጨማሪ ወታደሮች በ5 ኦራል መኪኖች ወደ ከተማዋ በማስገባቱ ውጊያው ተፋፍሞ እንደነበረ ምንጮቻችን ገልጸዋል። አርበኞችም ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደመጡበት መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነጋዴ ባህር በተባለው አካባቢና በህወሃት/ኢህአዴግ ቀይ ዞን ተብሎ በተሰየመ ቦታ በአንድ ነዳጅ ጭኖ ከሱዳን በመጓዝ ላይ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። በዚሁ ጥቃት መነሻነትም ከ50 በላይ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ነጋዴ ባህር ላይ ቆመው እንንደሚገኙ የኢሳት ምንጮች አስታውቀዋል። ጉዳዩ ያስጨነቃቸው የህወሃት የመከላከላ የጦር አባላት ጀኔራል ሲሳይ በተባሉ አዛዥ ተመርተው ወደ አካባቢው ማምራታቸው ተነግሯል።
ጄኔራሉ በጸጥታ ስጋት ነጋዴ ባህር ላይ የቆሙት 50 ነዳጅ የጫኑ መኪኖች ጉዞ እንዲጀምሩ ትዕዛዝ ቢሰጡም ሹፌሮቹ ፈቃደኛ አለመሆናቸን ለማወቅ ተችሏል። በዚሁ ምክንያት ጀኔራሉ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አንፈልግም በሚል ሹፌሮቹ ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲያንቀሳቅሱ በማስገደድ ላይ መሆናቸውን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment