Tuesday, March 28, 2017

የወጣት ማስተዋል እና የአምባሳደር ሀለቃ ፀጋይ ሙግት





ማስተዋል ጥላሁን በእስራኤል ነው የሚኖረው። ሰሞኑን ሀብታሙ አያሌው በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛው ክፍለ ጊዜ ላይ ቀርቦ በእስር ቤት ውስጥ በእሱና በሌሎች ታሳሪዎች ላይ ስለሚፈጸመው ግፍ ሲናገር ውስጡ በከፍተኛ ቁጣና ንዴት የተሞላው ማስተዋል፤ ቀጥታ ቴላቪቭ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመሄድ በጽህፈት ቤቱ በር ላይ ተሰቅሎ የነበረውን ባለኮከቡን ባንዲራ አውርዶ በማቃጠል ነው ከቁጣው ለመብረድ የሞከረው።
ይህን የተመለከቱት ቀደም ሲል የትግራይ ክልል ርዕሰ ብሔር፣ ከዚያም የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጸጥታና ደህንነት አማካሪ የነበሩት አዲሱ የእስራኤል አምባሳደር ሀለቃ ፀጋይ በርሃ በእስራኤል ፍርድ ቤት ማስተዋል ላይ ክስ ይመሰርታሉ። “የደህንነት ስጋት አለብኝ”በማለትም ለፍርድ ቤቱ አቤት ይላሉ።ከዚያም ፍርድ ቤቱ ማስተዋልን ለምን ድርጊቱን እንደፈጸመ ሲጠይቀው ምክንያቱን ይናገራል።
ግራና ቀኙን ያደመጠው የእስራኤሉ ፍርድ ቤት በመጨረሻም ወጣት ማስተዋልን በነጻ አሰናብቶታል።
ሃለቃ ፀጋይም “የደህንነቴንስ ጉዳይ?” በማለት ደጋግመው አቤት በማለታቸውም ማስተዋል ከኤምባሲው እስከ 500 ሜትር ባለው ርቀት እንዳይጠጋ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አካቷል።
“ቀጥ ብላችሁ ዐያችሁን” ብለው በጥይት ግንባር ግንባርን ሲቀሉና ሲያስቀሉ፣ እንዲሁም ከላይ ሆነው በሚያሽከረክሯቸው ፍርድ ቤቶች በንጹሀን ላይ እንደፈለጉ በትዕዛዝ ሲያስፈርዱ የቆዩ አምባገነኖች ፤ተዘልፈውም፣ ተዋርደውም ፍትሕ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲህ ሲያዩ እንዴት ደስ ይላል!
ጋዜጠኛ ደረጀ ሀ/ወል

No comments:

Post a Comment