Friday, September 1, 2017

የኦብነግ ከፍተኛ አመራር ለህወሃት መንግስት ተላልፈው መሰጠታቸውን ተከትሎ በሶማሊያ ሶስት ከተሞች ተቃውሞ ተቀሰቀሰ (ኢሳት ዜና–ነሐሴ 26/2009)

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ከፍተኛ አመራር ለህወሃት መንግስት ተላልፈው መሰጠታቸውን ተከትሎ በሶማሊያ ዛሬ በሶስት ከተሞች ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ።
የኦብነግ አመራር አባል አብዱልከሪም ሼህ ሙሴ ተላልፈው የተሰጡት በዚህ ሳምንት ውስጥ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እንደተወሰዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህን በመቃወም ህዝቡ ዛሬ በሞቃዲሾ፣ ኪስማዩና በዶብሌይ ሰልፍ መውጣቱ ታውቋል።
የሶማሊያ በርካታ መገናኛ ብዙሃንም ድርጊቱን በማውገዝ እየቀሰቀሱ ሲሆን በኬኒያ ናይሮቢ የሚኖሩ ሶማሊያውያንም በሶማሊያ አምባሳደር ላይ ድንጋይ በመወርወር ቁጣቸውን መግለጻቸው ተሰምቷል።
በሌላ በኩል ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ተላለፈው የተሰጡትን የኦብነግ አመራር አባል ግንባሩን በመክዳት እጃቸውን ሰጥተዋል የሚል ፕሮፖጋንዳ እያዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።
ለላለፉት ሶስት አመታት ነዋሪነታቸውን በሞቃዲሾ አድርገው የቆዩትንና አብዱከሪም ሼህ ሙሴ ባለፈው ሳምንት ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ችግር ወደ ሶማሊያ ማእከላዊ ግዛት ጋልሙዲግ መሔዳቸውንና በጋልካዩ ከተማ በአካባቢው የጸጥታ ሃይል መያዛቸውን የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው።
አብዱልከሪም ሼህ ሙሴ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የወታደራዊ ክንፍ አንድ አመራር እንደነበሩ የተጠቀሰው ግንባሩ ዓለም ዓቀፍ ህግን በመጣስ የሶማሊያ መንግስት ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ገዢ ቡድን አሳልፎ መስጠቱ ዋጋ ያስከፍለዋል ማለቱም የሚታወስ ነው።
ዛሬ ከሶማሊያ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የአብዱልከሪም ሼህ ሙሴ ተላልፎ መሰጠት የህዝቡን ቁጣ ቀስቅሷል።
ቀድሞውኑ በህወሀት የሚመራው መንግስት በሰላም አስከባሪ ስም በሶማሊያ ምድር መገኘቱን አጥብቀው የሚያወግዙት ሶማሊያውያን በአንጻራዊ መመዘኛ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው መንግስታቸው ‘’ሼህ ሙሴን እንዴት ለጠላት አሳልፎ ይሰጣል’’ በሚል በሶስት ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ መውጣታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በርዕሰ ከተማዋ ሞቃዲሾ፣ በሁለተኛዋ ትልቋ የወደብ ከተማ ኪስማዩ እንዲሁም በዶብሌይ አደባባይ በመውጣት መንግስታቸውን ያወገዙት ሶማሊያውያን፡ በተለይ ሁለቱን መሪዎቻቸውን በድርጊታቸው የኮነኑ ሲሆን በህወሀት የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በአስቸኳይ ሀገራቸውን ለቆ እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት እንደገለጹት የዛሬው የሶማሊያውያን ተቃውሞ ለሶማሊያ መንግስት ድንጋጤን ፈጥሯል።
እንደ ኦብነግ ቃል አቀባይና በአንዳንድ በሶማሊያ ጉዳይ ዘገባ ይዘው በሚወጡ የዜና ምንጮች እንደተገለጸው የአብዱልከሪም ሼህ ሙሴ ተላልፎ መሰጠት ለሶማሊያ መንግስት ያልተጠበቀ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ አድርጓል።
በአሁኑ ጊዜ በመስራቅ አፍሪካ ላይ በማተኮር በሶማሊኛ ቋንቋ ዜናዎችን የሚያቀርቡና ከሶማሊያ የሚተላለፉ መገናኛ ብዙሃንም በመንግስት በኩል የተወሰደን ርምጃ በማውገዝ ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጆችና ሶማሊያውያን በያሉበት ሀገራት ከወዲሁ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ዛሬ በኬኒያ ናይሮቢ በሶማሊያ አምባሳደር ላይ ጥቃት የተሰነዘረ ሲሆን የሶማሊያ ወጣቶች አምባሳደሩ በተሳፈሩበት ተሽከርካሪ ላይ ድንጋይ በመወርወር መስታወቱን መሰባበራቸውም ተመልክቷል።
በህዝቡ ተቃውሞ የተደናገጡት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አሳልፈው ለሰጡት የህወሀት መንግስት ስልክ መደወላቸው የተሰማ ሲሆን ተመልሰው ወደ ሞቃዲሾ እንዲመጡ መጠየቃቸውን የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ ሀሰን ገልጸዋል።
የሶማሊያ ህዝብ በህወሀት የሚመራው ጦር በሀገራቸው መኖሩን አጥብቀው እንደሚቃወሙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ለተለያዩ ቡድኖች መሳሪያ ከማቀበል አንስቶ በግልጽ ጣልቃ በመግባት የሀገሪቱ ሰላም ርቆ እንዲቀር በማድረግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው የህወሀት መንግስት ነው የሚለው ግንዛቤ በሶማሊያውያን ዘንድ በሰፊው ይሰማል።
ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ጥቅሙ ምን እንደሆነ በግልጽ ሳይታወቅ ላልፉት 10 ዓመታት በሶማሊያ ምድር የቆየው በህውሀት የሚመራው ጦር የደፈረሰውን ሰላም ይበልጥ እንዲደፈርስ ከማድረግ ያለፈ አስተዋጽኦ እንደሌለው ገንዘብ ከሚሰጡት የምዕራብ ሀገራት ጭምር የሚሰማ ወቀሳ ሆኗል።
የህወሀት ጄነራሎች ሀብት የሚያሸሹበት በመሳሪያ ንግድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰበስቡበት ቀጠና መሆኑን የሚገልጹ ሪፖርቶች በየጊዜው በመውጣት ላይ ናቸው።

ትርጉም ለጠፋበት ለዚህ ዘመቻ ከ10ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ልጆች በሶማሊያ ምድር የተገደሉ ሲሆን ለቤተሰቦቻቸው ሳይነገር አሁን ድረስ መቆየቱ በህዝብ ዘንድ ጥያቄ ፈጥሯል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተጠይቀው ይሄ አይመለከታችሁም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል ከሶማሊያ መንግስት ተላልፈው የተሰጡትን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ አመራር አባል ላይ ፕሮፖጋንዳ ለመስራት የህውሀት መንግስት እየተዘጋጀ መሆኑም ተሰምቷል።
አብዱልከሪም ሼህ ሁሴን ከኦብነግ በመክዳት በሰላም ሰርተው ለመኖር በመወሰን እጃቸውን ሰጥተዋል የሚል ዜናና ዝግጅት ተሰናድቶ ህወሀት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን ሊተላለፉ እንደሚችሉ የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment