ጓድ በረከት ስምኦን ከጀርባ ሆኖ ያዘጋጀውን የአዲስ አመት አቀባበል የድርጊት መርሃ ግብር ተመለከትኩት። የተከታታይ ቀናት ስያሜም ” የፍቅር ቀን”፣ ” የአንድነት ቀን”፣ ” የመከባበር ቀን”፣ ” የአገር ፍቅር ቀን”፣ ” የሰላም ቀን”፣ ” የኢትዮጵያ ቀን” …ወዘተ በሚል መሰየሙን ተመለኩ ። ሁሉም ቀናት የራሳቸው መሪ ቃል ቢኖራቸውም የአጠቃላዩ ማዕከላዊ መፈክር ” መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው!” ይላል። አባባሉ ከታዋቂው የአመራር ሳይንስ ፀሐፊ jim Collins ” Good to Great!” በሚል ከፃፈው መጽሐፍ የተኮረጀ ይመስላል ። እንዲህ አይነት ጥሩ ነገሮችን ከውስጥ ስሜት መነሻ ተደርጐ ቢዘጋጅ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባል። ዝርዝር ተግባራቱም በኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጐት ላይ የተመሰረተ ቢሆን አገዛዙ ለለውጥ መዘጋጀቱን እንደ መነሻ መውሰድ ይቻል ነበር። በምኞት እና ነበር ቀረ እንጂ!
ስለዚህ እኔም እንደ አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ተቆጣሪ በዝግጅቱ አይነት እና ዝርዝር ተግባራቱ ላይ ቢጨመሩ በማለት የሚከተሉትን ለማቅረብ አስቤያለሁ። ይሄን ማመልከቻ የማቀርበው አቶ በረከት በዚህ የፕሮፐጋንዳ እቅዱ ላይ ቢያካትተው በማለት ነው።
አንደኛ: ” የይቅርታና ብሔራዊ እርቅ ቀን”(ጳግሜ 1 )
በዚህ ቀን ላለፋት ሩብ ክፍለዘመን ህውሓት ለፈፀመው ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ፣ ህዝቡን በዘርና በሐይማኖት የከፋፈለበትን ተግባራት አምርሮ የሚኮንንበትና በኢትዮጵያን ህዝብ እግር ስር እየወደቀ ይቅርታ የሚጠይቅበት ይሆናል። ወደ ዝርዝር ተግባራቱ ስንገባ ደግሞ በቀናት ውስጥ ለሁሉም የፓለቲካ ድርጅቶች ፣ ሲቪክ እና ሙያ ማህበራት የብሔራዊ እርቅ ጥሪ ያደርጋል። መቼም ” የተጣላ የለም!” የሚለው የአቶ መለስ መከራከሪያ ከሰውየው ጋር አብሮ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ መጣሉን የሚከራከር የለም ።
ሁለት: “የፓለቲካ እስረኞች የመፍታት ቀን” ( ጳግሜ 2)
በዚህ ቀን አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ፕሮፌሰር መራራ፣ በቀለ ገርባ፣ አንዱአለም አራጌ፣ ቱዋት ፓል ጨምሮ ሁሉንም የፓለቲካ እስረኞች ህውሓት ለፈፀመባቸው በደል ይቅርታ ጠይቆ የሚፈታበት ይሆናል። የዚሁ እለት አቶ አባይ ፀሐዬ እና የደህንነት ሃላፊው አቶ ጌታቸው የፀረ ሽብርተኝነቱን ፣ በረከት ስምኦን ሚዲያና NGO አዋጁን፣ እያቃጠሉ በቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ይታያሉ። ወልደሥላሴ ( አባይ ነብሲ) ፓርላማው እና የክልል ምክርቤቶች መበተናቸውን ይፋ ያደርጋል። የዘውጌ ተኮር የፓለቲካ አደረጃጀቶች መፍረሳቸውን ያውጃል። እስከዛሬ ለደረሱት ግፎች መታሰቢያ እንዲሆን ” ማእከላዊ እስር ቤት” ወደ ሙዚየም መቀየሩን ደብረፂዮን በፀፀት ውስጥ ሆኖ ይናገራል። አዜብ መስፍን ኤፈርትን ጨምሮ የሕውሐት ንብረት የሆኑት ፋብሪካዎች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መንግስት እንዲወርሳቸው ማመልከቻ ለሐይለማርያም ታስገባለች። ሐይለማርያም ማመልከቻው እንደደረሰው በአንድ ሰአት ውስጥ ለስብሃት ነጋ ለውሳኔ ያቀርባል። ስብሃት በይቅርታ ውስጥ ሆኖ ውሳኔውን ያፀድቃል።
ሶስት: “የኢትዮጵያ ቀን” ( ከጷግሜ 3 እስከ ጷግሜ 05 እኩለ ለሊት)
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይች አገር የጋራ አገር መሆንዋን እንደሚረዳና ” ኢትዮጲያዊነት” በተባለ ጥልቅ የአገር እሴት ዙሪያ እንዲሰባሰብ የሐይማኖት አባቶችና አገር ሽማግሌዎች ጥሪ ያቀርባሉ ። በኢትዮጵያ ህልውና ተጋድሎ ውስጥ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ይዘከራሉ። ኢትዬጲያዊነትን የሚያንፀባርቁ ሙዚቃዎች ፣ ኤግዚብሽኖች፣ ኮንሰርቶች በነፃ ይዘጋጃሉ።
@ዘ- ሀበሻ
No comments:
Post a Comment