በዘረኝነትና በጥላቻ መርዝ ተወልዶ ያደገው ሕወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በመዘልዘልና የጋራ እሴቶችን በመበጣጠስ ማታለልና ማጭበርበርን ከጠመንጃ ጋር አዳቅሎ ዋና የመግዣ ስልት በማድረግ የዜጎችን እውቀትና ችሎታ ለግላቸውና ለሐገራቸው እድገት አስተዋፅዖ እንዳያደርግ አፍኖ ይዞ ሐገራችን አሁን ለምትገኝበት ምስቅልቅል ዳርጓታል፡፡ አገዛዙ ተንከባክቦ ያሳደገው የዘረኝነትና የጥላቻ ዘንዶ ራሱን እየበላው ወደ ሞት አፋፍ አድርሶታል፡፡ ከዚህ ጣዕረ-ሞት ለመዳንና ትንፋሽ ለማግኘት ሲልየተፈጥሮ ባሕርይው ያልሆነውን እና በገዥዎቹ አንደበትም ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ሲያጣጥሉትና ሲያንቋሽሹት የኖሩትን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ታላቅነትን፣ መከባበርን በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመስበክ በኢትዮጵያዉያን ልብ ውስጥ ቦታ ለማግኘት በመቧጨር ላይ ይገኛል፡፡
አገዛዙ በውስጥ ችግር በመዘፈቁና ባለፉት ዓመታት ለተነሱ ዋና ዋና የፖለቲካ ጥቄዎች መልስ መስጠት ባለመቻሉ በሕዝብ መስዋዕትነትና በራሱም በውስጥ መዳከም ምንም ነገር ማድረግ የማይችልበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ በመድረሱ በድንጋጤና በመረበሽ በተፈጥሮ ባሕሪው ሊያደርጋቸው የማይቻለውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣እርቅን፣ ታላቅነትን፣ በኢትዮጵያ አሰፍናለሁ የሚል አዲስ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በመክፈት ሕዝብን ለማጭበርበር በመወራጨት ላይ ይገኛል፡፡
ባለፉት ዓመታት ለሐገር ህልውና መሰረት የሆኑት አንድነት፣ እኩልነትና ፍትህ በሐገራችን እውን እንዲሆን የጠየቁ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ገድሏል፣ በጅምላ አስሯል፣ አፈናቅሏል፣ አሳዷል፡፡ ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት በዜጎቻችን ላይ የፈፀመ አገዛዝ ግፍ የፈፀሙ በሕግ ተጠያቂ ሳይሆኑ፣ ሕዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ፣ በግፍ እስር የሚማቅቁ ሳይፈቱና በእስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የጨፈለቀ አገዛዝ ዛሬ ላይ ከመሬት ተነስቶ ፍቅርና ሰላምን እየሰበከ አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ እያለን ነው፡፡
የአገዛዙ አረመኔያዊ ተግባር ማለትም እናት ልጇን ገድሎና አስከሬኑ ላይ አስቀምጦ የሚስለቅስ የእናቶች ቀን አከብራለሁ ይለናል፡፡ በጠራራ ፀሐይ ወጣቶችን በጥይት በመፍጀት አረጋውያንን ያለጧሪ አስቀርቶ የአረጋውያንን ቀን አከብራለሁ ይለናል፡፡ ሐሳባቸውን በመግለፃቸውና ስለኢትዮጵያውነት በመቆርቆራቸው ብቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የስቃይ ማማ በሆኑ አደገኛ እስር ቤቶች እያማቀቀ ስለ አርቅና መቻቻል ላስተምራችሁ ይለናል፡፡ በዜጎች መካካል ጥላቻና የዘረኝነት መርዝ እየረጨ ልዩነትን የአገዛዝ መሰረት አድርጎ ዜጎች እርስ በእርሳቸው በጥርጣሬና በፍርሃት እንዲተያዩ ካደገረገ በኋላ ስለአንድነትና መከባበር ላስተምራችሁ ይለናል፡፡ ዕውቀትና አዋቂዎችን አዋርዶ ትምህርትን ለማህበራዊ ሽግሽግ የሚያገለግል ተራ ሸቀጥ አድርጎ እና የንባብና የጥናት ቦታዎች የአደንዛዥ ዕፅ መሸጫነት ካዋለ በኋላ የንባብ ቀን አከብራለሁ ይለናል፡፡ ኢትዮጵያውያን እምቅ ችሎታቸውን ለሐገራቸው ጥቅም እንዳያውሉ በጠመንጃ አፍኖ በመግዛትና ሐገራችንን የእውቀትና የሐሳብ ድሃ አድርጎ የካድሬና የአድር ባዮች መፈንጫ ካደረገ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ ከፍታ ሊነግረን ይፈልጋል፡፡ ይህ የማጭበርበርና የማደናገር ተግባር የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅና በቁስሉ ላይ ጨው መነስነስ ነው፡፡
ከላይ የጠቅስናቸው ከአገዛዙ ማርጀትና ምንም ነገር ለማስፈፀም አቅም እያጣ ከመሄድ የተነሳ የተፈጠሩ የማስመሰያና የማታለያ ዲስኩሮች ከሕወሃት/ኢሕአዴግ የተፈጥሮ ባሕርይ ጋር የሚቃረኑ ስለሆኑ ከተባሉት የፕሮፓጋንዳ ቀናት በኋላ በተግባር አይኖሩም፡፡ የስልጣን መሰረቱ ጥላቻና በልዩነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ እርቅን፣ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ከተቀበለና በተግባር የፖሊሲው አካል አድርጎ ከሰራበት አገዛዙን ስለሚያጠፉት ተፈፃሚነት የላቸውም፡፡ ስለሆነም የሕወሃት ኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ ለማስቀየስና ጊዜ ለመግዛት ስለሆነ ከዚህ ማደንዘዣና ማደናገሪያ ምንም ሳንጠብቅ ትግላችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሐገራችን በአሁኑ ሰዓት ካለችበት ውስብስብ ችግር ለመውጣት አርቆ አስተዋይና ለሞት የማያሳሱ፣ እንደ ጧፍ ነደው የብልፅግናና የእድገትን መንገድ የሚያሳዩ ባለ ራዕይና የነገ ሰዎች ያስፈልጓታል፡፡ ይህንን የተከበረ ሐገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የደም መስዋዕትነት በመክፈል የተግባር ምሳሌ ሆነው አሳይተውናል፡፡ ይህ የደም ዋጋ ለፍሬ እንዲበቃ እኛ አትዮጵያዊያን ካለፉት ተሞክሮዎቻችን በመማመር የዘረኝነትና የጥላቻ ሰንኮፍ የሆነውን ሕወሐት/ኢህአዴግ በመንቀል የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲያብብ በአዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ ትግላችንን አጠናክረን ለመቀጠል ቃል እንድንገባ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment