ከመድፍ ድምጽ ያየለ፣ ጽናትን፣ እምነትንና ጥንካሬን የሚያሳይ ታላቅ ድምጽ በመዲናችን ተሰማ። ማንም ቀስቃሽ ከሚያደርገው ጥሪ በላይ የክተት አዋጅ የመሰለ የእምነት ቃል ፈጽሞ ሊሆን ይችላል ተብሎ ከማይጠበቅበት አቅጣጫ ተሰማ! አዎ ለፍልሚያው ቆርጫለሁ እናንተን ከመንበረ ሥልጣኑ ለማንሳት በኔ አቅም ያለውን ሁሉ ለማድረግ ጉዞ ጀምሬአለሁ። በአካል ከስፍራው አልደረስኩም እንጂ በመንፈስ ሸፍቻለሁ ይህንን አምናለሁ ግን ግን ፈጽሞ ጥፋተኛ አይደለሁም! አሁንም ባለሁበት ሁኔታና ካለሁበት ለመታገል ከቶውንም ወደሗላ አልልም!
በእርግጥም ከነጎድጓድ ያየለ ከመድፍ ድምጽ አስርሺህ ጊዜ የበለጠ ሃያል ድምጽ በ‘አንበርካኪዎቹ’ ማማ ላ
ይ በ‘አስጎንባሾቹ’ መድረክ ላይ ተሰማ። ኢትዮጵያ ያልታደለ ሕዝብ የሚኖርባት ግን የታደለች ሀገር ናት። አፈርና ውሀዋ የሰራው ዜጋዋ ከአየሩ ጋር አብሮ ከሚተነፍሰው የነፃነት መንፈስ ጋር ተዳምሮ ከዘመን ዘመን በኩራት እንዲረማመድ ሆኖ የተሰራ ነው። ለዚህም ነበር የጥቁር አፍሪካ ፈርጥ ለነፃነት ፈላጊዎች የመንፈስ ምርኩዝ ተብሎ የሚጠራው። ግና የእናት ሆድ ዥጉርጉር እንዲሉ ባርነትን የተከተቡ፣ ጥላቻ የተጠናወታቸው በአእምሮ ድህነት የሚሰቃዩ ከዚችው ኢትዮጵያ የተፈጠሩ የሰው አረሞች ቁልቁል ደፍቀው እምነትና ነፃነቱን ክፉኛ ፈትነውታል። አወቅን ባይ የትምክህት ባሮች እንቅፋት እየሆኑት በጠላት ወጥመድ ውስጥም እየጣሉት ከችግር ወደመከራ ከበረዶ ወደ እሳት የሚገላበጥበትን ገሃነማዊ ህይወት እንዲመራ አድርገውታል። የትግራይ ጎጠኞች ተስፋውን ያሟጠጠ እንዳሻን የምናደርገው ፈሪ ሕዝብ ፈጥረናል በሚሉበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አለንልሽ የሚሏት ለክብሯ ለነፃነቷ ሊሞቱላት የቆርጡ ጀግኖች ወደ ትግል ሜዳ ሲተሙ፣ በያሉበት ስንደቅዓላማዋን ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ ለተመለከተ ግን እውነትም የታደለች አገር! እንዲል ያስገድደዋል።
ይህ ያበቃለት የመሰለው የራሱ ወገኖች ደካማና ፈሪ አድርገው የሚስሉት ሕዝብ ጀግንነትና ቆራጥነት በደሙ ውስጥ መመላለሱን የሚያረጋግጥና ያለነፃነት ከመኖር ማናቸውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ግን ዕለት በዕለት እያስመሰከረ ነው። በየአደባባዩ፣ በየጉድባውና ሰርጣ ሰርጡ ጣዕረሞት ከመሰሉት የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች ጋር ለመፋለም መቁረጣቸውን የሰማ ሁሉ ተስፋ በውስጡ እያበበች ነው። በርገር በሊታዎቹ ቂጣ ለመብላት የተዘጋጀ ስነልቦና እንዳላቸው አስመስክረዋል። ስሜታቸው ብቻ ሳይሆን አጥንታቸው የሟሟ የሚመስል በወያኔ እስር ውስጥ ተጠፍረው ያሉ ከአሳሪዎቻቸው ገዝፈውና ታላቅ ሆነው ደካሞቹን ቁልቁል ሲመለከቱ ማየትም ያለውን እምቅ ሃይል አመላካች ነው። የርዕዮት ብዕር ወረቀት ማድማቱን ማየት ስሜት የሚያሞቅ ነው። እነ አብርሃ ደስታ ቁም ነገር ሊከትቡ ወደ ትልቁ እስር ቤት መመለሳቸው እነ ሃብታሙ ‘እመነኝ!’ ሲሉ እንደገና ልንሰማ መሆኑን ማሰብ ደስ ያሰኛል።
በሌላ ወገን ወያኔ የተማመነበት ሰራዊት ኢትዮጵያዊነቱ በልጦበት እየከዳ ነው። መሳርያውንም ወደ አገር አፍራሽ ጎጠኞች እንደሚያዞር ምልክቶቹ ሁሉ እየታዩ ነው። ስማቸውን ያልሰማን ማንነታቸውን ያላወቅን ለጊዜው ማወቅም የማይገባን በርካታ ጀግኖች በዚህ የትግል መስመር ገብተው ለፍልሚያ ስለመዘጋጀታቸው ከቶወንም ጥርጣሬ የለንም። የሰላም በር ሲዘጋ የፍልሚያ መስኮቶች ይበረገዳሉና በየአቅጣጫው መነሳሳትን ማየታችንም ለዚሁ ነው። ከተሞች ሁሉ የትግል አምባ ወደመሆንና ጎጠኞችንና የሀገር ጠላቶችን በህግም በትጥቅም ቢሆን ለመፋለም ዝግጁነታቸውን እያረጋገጡ ነው። ፍርሃት ያራዳቸው የወያኔ ጉልተኞች ብር በሻንጣ ይዞ መሮጥ መጀመራቸውም የዚሁ አይነተኛ የውድቀት ምልክት ነው።
ወደ ጀመርኩት ርዕስ ልመለስና የነብርሃኑ ተክለያሬድን ዜና እንደሰማሁ ኢካድፍ የለጠፈውን ምስል ተመለከትኩ ሰውነት የሚወር ስሜት ተሰማኝ በወጣቶች ያለኝ ጽኑ እምነት ታደሰ። ኢየሩሳሌምን በስስት ዐይን ተመለከትኩ፣ የጀግና ክብር የሚገባት የጣይቱ ልጅ በሰላሙም ጎዳና ሁሉን ችላ በፅናት የሄደችበት ጀግናዬ ናት። ሽንታም እያሉ ለሚሳደቡት እንደኛ ለመሆን የጫካውን መንገድ ሞክሩ ለሚሉና ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ወግተው በፈረንጅና በተጃጃሉ ኢትዮጵያውያን ትከሻ ስልጣን ላይ የወጡትን እብሪተኞች ለመፋለም ጉዞውን የጀመሩትን ጀግኖች አንኳን እኔ ጠላትም እንዲያደንቃቸውና እንዲያከብራቸው ግድ ይለዋል። መድረኩን አገኙ ቃላቸውን ሰጡ። ቃላቸው ግን ድፍን የኢትዮጵያ ወጣቶችን የሚያስሸፍት እንዲሆን ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም።
ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው፣ ዳሴ ካሳሁን ክብር ለናንተ ይሁን። ካሰባችሁበት ያልደረሳችሁ መስሏችህ ከሆነ አትሳሳቱ ማናችንም ከምናሰበው በላይ ግዳጃችሁን ተወጥታችሗል። መድረስ ብቻ አይደለም አልፋችሁ ሄዳችሗል። ከጠላት ምሽግ ገብቶ የጨበጣ ውጊያ ከመግጠም በላይ የእምነት ቃላችሁ ስራውን ሰርቷል። በዚህ በርካቶች አንገት በደፉበት ሰዐት፣ በርካቶች በሌሎች ትከሻ መሸጋገርን በሚሹበት ጊዜ እናንተ ድልድይም መስዋዕትም ሆናችሁ ለታሪክ የሚተርፍ ገድል ፈጽማችሗል። አዎ ጥፋተኛ ሳትሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግኖቹ ናችሁና ደስ ይበላችሁ። ፈለጋችሁን የሚከተሉ በረሃ የሚዘልቁም ሆነ ባሉበት ሆነው በተጠንቀቅ የሚጠብቁ በርካቶችን በማነሳሳታችሁ ክብር ለእናንተ ይሁን።
ኢትዮጵያ በነፃነትና በክብር ለዘለዐለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment