መሳይ መኮንን
ዛሬ ለኢሳት የደረሰው ጥብቅ መረጃ 11ዓመታትን ወደ ኋላ በትዝታ ወሰደኝ:: ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዋናው ጸሀፊ ቢሮ አፈትልኮ የወጣው መረጃ እንደሚያጋልጠው ለሰላም አስከባሪ 11 ሺህ የኢትዮጵያ ሰራዊት የሚከፈለው ደምወዝ ከ90 በመቶ በላይ የህወሀት ካዝና ውስጥ የሚገባ ነው:: በወር 13 ሚሊዮን ዶላር(500 ሚሊዮን ብር ገደማ) የወታደሩ ገንዘብ ህወሀቶች ይቀራመቱታል:: ይህን ጉዳይ የመንግስታቱ ድርጅት የሚያውቀው ይመስለኛል:: ለዚህም እኔ የተሳተፍኩበትን የሰላም አስከባሪ ዘመቻ አጋጣሚ በአስረጂነት ማሳየት እችላለሁ::
እኤአ በ2003-2004 በመንግስታቱ ድርጅት የበላይነት: በአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚነት ከተላከው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ጋር ወደ ቡሩንዲ ሄጄ ነበር:: ወደ 18 የምንሆን አስተርጓሚዎች ከ8 ወር እስከ 1 ዓመት ቆይተናል:: ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ:: ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የተፈጸመውን የህወሀቶችን ለከት ያጣ ስግብግብነትን ላጫውታችሁ::
በዘመቻው በUN ደረጃ ወርሃዊ ደምወዝ ከ1000 ዶላር ያላነሰ: የመስክ ክፍያ በቀን 60 ዶላር: የበዓል ክፍያ በአንድ በዓል 1000 ዶላር: የላብ መተኪያ: …..በጣም ብዙ ዓይነት ክፍያዎች ነበሩት:: አብዛኛው የሰላም አስከባሪ ሰራዊት አባላት በተስፋ ነበር ወደ ቡሩንዲ የተጓዘው:: እዚያ እንደደረስን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኑ:: ቃል የተገባው: በውል የታሰረው( የሚገርመው የውሉን 3 ኮፒዎች አንሰጥም ብለው እዚያው መከላከያ ግቢ ቀርቷል:: መንግስትን አምነን ነው የተጓዝነው) ክፍያ የለም:: በወር 40 ዶላር ለኪስ እየተሰጠን: ምግብና መጠጥ በአላሙዲን እየቀረበልን: እየበላንና እየጠጣን መኖር ብቻ ሆነ:: ከኢትዮጵያ ሌላ የደቡብ አፍሪካና ሞዛምቢክ የሰላም አስከባሪ ሃይሎችም ለተመሳሳይ ዘመቻ ቡሩንዲ ገብተዋል:: ለእነሱ የሚገባቸው ክፍያና ጥቅማጥቅም ሀገራቸው በባንክ አካውንታቸው የሚገባላቸው ይህንንም የሚያረጋግጥ ደረሰኝ በየወሩ እንደሚደርሳቸው በነበረን ቅርበት ተረዳን:: እኛ ግን ምንም የለም:: ስንጠይቅ ኢትዮጵያ ይጠራቀምላችኋል የሚል መልስ ከማስፈራሪያ ጋር ይሰጠናል::
በእኛና በሌሎቹ ለተመሳሳይ ዘመቻ በመጡ ሀገራት የሰላም አስከባሪው ዘመቻ አባላት መሃል ያለው የኑሮ ሁኔታ የሰማይና የምድርን ያህል የሚራራቅ ነበር:: በህወሀት ስግብግብነት የተነሳ በጣም በሚያሳፍር የኑሮ ገጽታ መቀለጂያ ሆንን:: በሰራዊቱ ውስጥ ቅሬታው ስር ሰደደ:: ተስፋው ጨለመ:: በወር 40 ዶላር እየወረወሩ እዚያ ይጠራቀምላችኋል በምትል ከቃል ያለፈ በደረሰኝ ያልተረጋገጠች ተስፋ ብቻ ይዘን በብስጭት ገፋን:: በመሃል ሲብስብን አስተርጓሚዎች ተነጋግረን ቡጁምቡራ በሚገኝ የUN ጽ/ቤት አቤቱታ ልናቀርብ ሄድን:: የተሰጠን ምላሽ ተስፋችንን ይበልጥ ገደለው:: “ስለ እናንተ የተፈራረምነው ከመንግስታችሁ ጋር በመሆኑ አይመለከተንም:: መንግስታችሁን ጠይቁ::” የሚል ወሽመጥ የሚቆርጥ ምላች ተሰጠን::
በመሃሉ መለስ ዜናዊና ሳሞራ የኑስ ሊጎበኙን ቡጁምቡራ መጡ:: ሳሞራ ሰብስቦን ችግር ካለ ንገሩኝ አለ:: ሰራዊቱ የክፍያው ነገር ሲያንገበግበው ስለከረመ ሳሞራን ሲያገኝው በየተራ እየተነሳ ጠየቀው:: ሳሞራ ጀት ሆነ:: ባለጌ አፍ እንዳለው ያረጋገጥኩት የዚያን ዕለት ነው:: የኢትዮጵያን የችግር መዓት ሲዘረዝር: መዓት ሲያወራ ቆየና ” ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም:: የሌሎችን እያያችሁ እንደነሱ እንሁን ማለት አደጋ አለው:: እዚህ ገንዘብ ምንም አያደርግላችሁም:: በብር ኢትዮጵያ እየተጠራቀመላችሁ ነው:: ለሸርሙጣ ፈልጋችሁ ከሆነ ኢትዮጵያ ስትመለሱ ትደርሱበታላችሁ…..” እያለ ወረደብን::
ሰራዊቱ ቅስሙ ተሰበረ:: ብዙ የምንሰራው ስራ አለ:: ትምህርት ቤት እንገነባለን:: ….እያለ ተንዘባዘበ:: የዚያን ዕለት ሌሊት ከአምቦ የመጣ የሰራዊቱ አባል በታጠቀው መሳሪያ ራሱን አጠፋ:: ባርቆበት ነው የሚል ሪፖርት እንድናዘጋጅ በህወሀት የጦር አዛዦች መመሪያ ተሰጥቶን የውሸት ሪፖርት አዘጋጅተን ለUN ተላከ:: ይህ የሆነበትም ራሱን ካጠፋ UN ካሳ አይከፍልም:: እርግጠኛ ነኝ በዚህ የተገኘውን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር ህወሀቶች ኪስ ገብቷል::
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ እየተጠራቀመላችሁ ነው እየተባለ ስንሸነገል የከረምንበትን ገንዘብ ሊሰጡን ተዘጋጁ:: ለአንድ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱ አባል በትንሹ ከ250ሺህ ብር በላይ ወይም በወቅቱ ምንዛሪ 10ሺህ ዶላር መከፈል ነበረበት:: በጣም የሚያሳፍር የሚያስደነግጥ ነገር ነበር የጠበቀን:: እንደ ቆይታ ጊዜ ከ15ሺህ እስከ 25ሺህ የኢትዮጵያ ብር ሰጥተው አሰናበቱን:: ከእያንዳንዳችን ከ200ሺህ ብር በላይ ህወሀቶች ተቀራመቱት:: …በሌላ ጊዜ በስፋት እመለስበታለሁ::
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46076#sthash.D4kyf1U4.dpuf
No comments:
Post a Comment