አቻምየለህ ታምሩ
የራሱ የኑሮ መመሪያ እምነት [ideology] የሌለው ያሁኑ የኢትዮጵያ ወጣት «ምሁር»፤ አገራችን በዚህ ወቅት የደረሰችበትን «ደረጃ» ሲገመግም፥ ወያኔ በቴሌቨዥን ኑሯችንን በማይመስሉ የስኬት አሃዞች አጅቦ የሚያሳየንን የወያኔ ዘመን ኢትዮጵያና የቀድሞ ስርዓቶች ኢትዮጵያን ውድድር እንደ እውቀት በመውሰድ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የክፍለ-ዘመኑን ታላቅ እመርታ ያስመዘገበችና መቼም ልትደረስበት በማትችለው የልማት ምህዋር ውስጥ እንደገባች በወያኔ የሚደሰኮረውን ፕሮፓጋንዳ እንዳለ ተቀብሎ ሲያበቃ መሰረታዊ ችግሮቿን ያልፈታችን አገር ልክ እንደ ተሰፋ ምድር አግዝፎ ይመለከታታል።
በእኔ እምነት ከላይ የቀረበው የአሁኑ የኢትዮጵያ ወጣት «ምሁር» የአገሩን ሁኔታ የሚረዳበት ሸውራራ አተያይ የሚመነጨው፣ አቃለልከው ካላላችሁኝ፣ የሰው ዘሮችን ከሚያጠቁት ከችግር፣ ከበሽታና ከድንቁርና በታች ከሆነ የኑሮ ደረጃ ነፃ ስላልወጣ፣ በትምህርትና በልዩልዩ ልቀቶች ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የጭራነት ደረጃ በሺዎች እጥፍ ልትደርስበት የሚገባትን ከፍተኛ የልማት ትሩፋትና የላቀ የጥበብ ስራ፣ ከሰብዓዊ ተግባር የላቀ መስሎ እንዲታየው ሆኖ ስለተቀረጸ ነው።
የወደፊቷን ኢትዮጵያን ሳስባት ተስፋየ የሚጨልመው ሸውራራ እይታ ባላቸው ሆዳም የወያኔ ደጋፊ ወጣት «ምሁራን» ብቻ አይደለም፤ ወያኔን በማይደግፈው «ምሁር» ላይም ጭምር ነው። የወያኔዋ ኢትዮጵያ በወያኔ አገላጋይነት በወለደችው ችግር የተነሳ፣ ወያኔን የማይደግፈው ወጣት «ምሁር» sworn enemies እስኪመስል ድረስ በጎሳ ተከፋፍሎ በአይነ ቁራኛ እየተያየ ተቀራርቦ ለመነጋገር ፍላጎት አለማሳየቱ፤ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ከአሁኗ ኢትዮጵያ የተሻለ እንድትሆን ለማድረግ የተጀመረም ጥረት አለመኖሩና አሁን ያለው ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ መጪው ጊዜም ይህንን ለማድረግ ሰፊ እድል እንደሌለ ስረዳ ሀዘኔ ይበዛል።
ወያኔን የማይደግፈው የዘመኑ ወጣት «ምሁር»፣ ለኔ እንደሚታየኝ የህይዎት ጉዞ አስተሳሰቡ እንደሚከተለው ይመስለኛል። ጫፍና ጫፍ ያለው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የመክፈት ተግባር ብዙም አያሳስበውም። ታሪክ ፖለቲካው ሆኗል። ይሄ ትውልድ በፖለቲካ ታሪክ መስራት ሳይሆን ታሪክን የፖለቲካው መሳሪያ ማድረግን የህይወት ጥሪው አድርጎታል። ከለዘብተኛው መካከል ደግሞ በሽታን፣ ችግርን፣ ድንቁርናን፣ ፈላጭ ቆራጭና አፋኝ ገዢዎች ባገሩ መፈጠርን በተፈጥሮ ኃይል የሚደርሱ ጉዳቶች ወይንም ከእ/ሔር እንደታዘዙ መጥፎ እድሎችና መቅሰፋቶች ብቻ አድርጎ የሚያየው ቁጥሩ የትየለሌ ነው። በዚህም የተነሳ እነዚህን ችግሮች በበረታ ትግሉ የሚያሸንፋቸው፤ በጥንካሬው የሚቀርፋቸው አይመስሉትም።
ባጠቃላይ ግን ሃብትን፣ ጤንነትን፣ ምቾትን፣ ዕውቀትን፣ እንደ ጋንዲ፣ ኔሕሩ፣ አብርሃም ሊንከን፣ ኡመር አልሐጣብ፣ ሙስጠፋ ከማል አታቱርክና የመሳሰሉ መሪዎች ያሏቸው ህዝቦች፤ እድገትና ሌሎችን ነገሮች ደግሞ ለተለዩ ምርጥ ሰዎች ብቻ ከፈጣሪ እንደተሰጡ በረከቶች አድረጎ በመቀበል፤ ደንቆሮ በድንቁርና፣ ድሓ በድህነቱ፣ በሽተኛ በደዌው፣ አምባገነን የሚረግጠው በእስር፣ በእንግልትና በአፈና ረክቶ ከሞተ በኃላ የሚሄድበትን ዓለም ብቻ የሚጠባበቅ የሚመስለው የዘመኑ ያገራችን ወጣት «ምሁር» ቁጥሩ ቀላል የማይባል ነው።
ይህ የ21ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ሁሉን ነገር ለምን እንዲህ ሆነ ተብሎ ገዢዎች የሚጠየቁበት፤ የሚጎነተሉበትና ምኞቱን ካላሟሉለትም የሚወገዱበት ጊዜ ነው ብሎ ከልብ የመነጨ እምነት መያዝና ማራመድ እምብዛም በዚህ ዘመን ያገራችን ወጣት «ምሁር» ዘንድ አይስተዋልበትም። እኔ እንዴውም አንዳንድ ጊዜ ሳስብ፤ ወያኔዎች በመልካም ሰውነት የሚያምኑ ሆነው፣ «በዚህ ዘመን ሁሉን ነገር ለምን እንዲህ ሆነ? ብሎ እኛን መጠየቅ በሰውነትህ የማይነኩ መብቶችህ ናቸውና ውሰድና ተጠቀምባቸው» ብለው ቢሰጡትም የዚህ ዘመኑ ወጣት «ምሁር» አምኖ የሚቀበል አይመስለኝም።
ወያኔዎችም ከላይ ያቀረብኩትን አይነት ወጣት «ምሁር» ሲፈጥሩ የሚታያቸው ነገር ኢትዮጵያን የሚረከባት እንደዚያ አይነት ትውልድ መሆኑ ወይንም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ማህበራዊ ኑሮ ሰላም የሌለበት መሆኗ አይደለም፤ እነሱ የሚታያቸው የዚህ ዘመን ወጣት «ምሁር» እና እሱ እያፈራው ያለው ከጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ በላይ የማያነበው አንድ ትውልድ መፈጠሩ ቢያንስ የግፍ ዘመናቸውን በአንድ ትውልድ ለማራዘም እንደሚያስችል አቅም አድርገው ነው።
የምዕራብ አገራት መንግስታት ግን፣ የሚተካቸውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ባጠቃላይ፣ ጊዜና አካባቢ ከሚያመጣቸው ችግሮች ጋር እንዳይጋጭ በማሰብ ዛሬውኑ መንገዱን በመጥረግ፣ የዛሬውም ተግባራቸው የወደፊቱን አገር ተረካቢ ትውልድ ህይዎት እንዳያውክ ራሳቸውን በማረም ላይ ናቸው። እኛ ግን ተጨንቆ ለማሰብ ልብና ጊዜ የለንም። እኛና ምዕራቡ አለም ተለያይተናል። በአንድ ፕላኔት አብረን ብንኖርም እነሱ ዘመኑን ከጊዜው ቀድሞው እየደረሱበት ነው ለኛ ግን ዘመኑ ወደኋላ እየሄደ ነው!
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/9995#sthash.ZnQY6rin.dpuf
No comments:
Post a Comment