Saturday, August 29, 2015

ኦሮሚያን እንገነጥላለን የሚለው ጥያቄ ታላቋ ኢትዮጵያን ለመሰረተው የኦሮሞ ህዝብ ስድብ ነው - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46258#sthash.St8bLsFf.dpuf

ማስታወሻ፡- ቀጥሎ የምታነቡትን ጽሑፍ በፍቃዱ ኃይሉ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ለአንባቢያን እንዲደርስለት ለነገረ ኢትዮጵያ የላከው ነው፡፡ ኦሮምኛውን ቀደም ብለን የለቀቅን ሲሆን አማርኛውን ደግሞ እንሆ!
Guddaa saalpaa fariddi guniddaan dhessa

በፍቃዱ ኃይሉ (ከቂሊንጦ እስር ቤት)
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ተሰብስበው ወሰኑ፡፡ ኃያላኑ መንግስታት የየድርሻቸውን ሲወስዱ የኢትዮጵያን አካባቢዎች ለመውረር የሞከረው የጣሊያን መንግስት ነበር፡፡ አውሮፓውያን ወራሪዎች ‹‹ዓላማችን አፍሪካውያንን ከእንቅልፋቸው ቀስቅሶ ማሰልጠን ነው›› ቢሉም እየዋሹ ነበር፡፡ ዋነኛ ዓላማቸው የአፍሪካን ሀብት ለፋብሪካዎቻቸው ጥሬ ዕቃ ማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም እግረ መንገዳቸውን አፍሪካውያንን ሀይማኖታቸውን እያስለወጡ ከራሳቸው ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ቋንቋ፣ ወግ እና ልማዶችን በማጥናት ዘመናዊ በሚሉት በራሳቸው ቋንቋ፣ ወግ እና ልማድ ይተኩታል፡፡ አፍሪካውያንን ማሰልጠን የሚሉት ይህንን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከቅኝ ግዛት በኋላ ብዙ አፍሪካውያን የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል እና ስርዓት ሙሉ ለሙሉ አጥተው በአውሮፓውያን ገዥዎቻቸው ባህል እና ስርዓት እየተዳደሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን በአንጻሩ ይህንን ወረራ በኅብረት መመከት በመቻሏ ምንም እንኳን ከአውሮፓ ተጽዕኖ ባትተርፍም የተለየ (የራሷን) ባህል እና ወጎችን እንደያዘች አለች፡፡
(ጋዜጠኛ በፈቃዱ ኃይሉ)
(ጋዜጠኛ በፈቃዱ ኃይሉ)
ኢትዮጵያ የአውሮፓ ወራሪዎችን መመከት የቻለችው ህዝቦቿ በመተባበራቸው ነው፡፡ የጣልያን ሰራዊት አድዋ ላይ ድል ካደረጉት የጦር መሪዎች መካከል ባልቻ ሳፎ (በፈረስ ስማቸው አባ ነፍሶ) ሳይጠቀሱ የማይታለፉ የኦሮሞ ልጅ ናቸው፡፡ ከምንም ተነስተው የጦር ሚንስትር እስከመሆን የደረሱት ሀብተጊዎርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) ለዚህ ደረጃ የበቁት በአድዋ ባሳዩት ጀግንነት እና መለኝነት ነበር፡፡ እርሳቸውም የኦሮሞ ልጅ ናቸው፡፡ ጣልያን ድል ሆኖ መመለሱ ቆጭቶት ከ40 አመታት በኋላ ሲመለስም ወረራውን በመመከት ረገድ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ኦሮሞዎች ተሰልፈው ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል የማይዘነጉት እነ ገረሱ ዱኪ እና ጃጋማ ኬሎ ይገኙበታል፡፡ ጀግናው ጃጋማ ኬሎ ፍቀረማርቆስ ደስታ በጻፈላቸው ታሪካቸው ውስጥ ‹‹ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው›› ሲሉ ነግረውታል፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ በብዛት ትልቁ ኢትዮጵያዊ ብሄረሰብ ነው፡፡ የኦሮሞ ታሪክ ከተጻፈው በላይ ትልቅ ነው፡፡ የኦሮሞ ጎሳዎች ይተዳደሩበት የነበረው የገዳ ስርዓት ዴሞክራሲ ለኦሮሞ ህዝብ ባህሉ ነው ያስብላል፡፡ በኦሮሞ ባህል የሰዎች አደረጃጀት የበላይና የበታች የሚለው ብዙም ተቀባይነት የለውም፡፡ በየትኛውም የገዳ ስርዓት የስልጣን እርከን ላይ ያለን ሰው የትኛውም ተራ ሰው መተቸት እንዲችል የኦሮሞ ባህል ይፈቅድለታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ባህል የህዝብ መሪዎች ከህዝብ ትችት እንዳያመልጡ የሚያደርግ ስለሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ፣ ምንም እንኳን የብዛቱን ያህል ተጠቃሚ ባይሆንም የኦሮሞ ልጆች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የስልጣን ተቀናቃኝ ሆነው አልፈዋል፡፡ አንዳንድ ባለታሪኮች ‹ዘመነ መሳፍንት› የሚሉት የኢትዮጵያ ክፍለ ታሪክ በየጁ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያ የተመራችበት ዘመን ነው ይላሉ፡፡ ያኔ መናገሻ የነበረችው ጎንደር ከተማ የስራ ቋንቋዋ ኦሮምኛ ሆኖ ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ንግስናውን ያገኙት የአማራ እና የትግሬ ገዢዎች ከኦሮሞ ጦረኞች ጋር ተስማምቶ ለማደር በጋብቻ መተሳሰርን መርጠዋል፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ ልባቸው እስኪጠፋ ያፈቅሯት የነበረችው ሚስታቸው የወሎው ኦሮሞ ራስ አሊ ልጅ ተዋበች ነበረች፡፡ አጤ ምኒልክ ያገቡት ‹‹የኢትዮጵያ ብርሃን››
የምትባለውን ዜደኛ የየጁ ኦሮሞ ሴት ጣይቱ ብጡልን ነበር፡፡ …ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን በቀጥታ ባልገዙበት ዘመን በተዘዋዋሪ አዝዘውባታል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንዳለመታደል ሆኖ ህዝቡ ተመችቶት አልኖረም፡፡ የኦሮሞ ህዝብም የዚሁ ገፈት ቀማሽ ነበር፡፡ መሪዎች በተገላበጡ ቁጥር ለራሳቸው ሲሉ ድሃውን ገበሬ ሲያንገላቱ ኖረዋል፡፡ ነገስታቱ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከጎናቸው ያልተሰለፈውን ሁሉ በኃይል ያጠቁ ነበር፡፡ ገበሬው ያመረተውን ቆርሶ የማካፈል ግዴታ ነበረበት፡፡ ግብር የበዛባቸው ገበሬዎች ከመማረራቸው የተነሳ የእህል ክምራቸውን የንጉስ ወታደሮች ሊወስዱባቸው ሲመጡ እህሉ ላይ እሳት ለኩሰውበት ይሸሹ ነበር፡፡ ነገስታት በመጡ፣ ነገስታት በሄዱ ቁጥር ድሃው ህዝብ እረፍት ሳያገኝ ኖሯል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከጥቂቶቹ የስልጣን ተቀናቃኞች በስተቀር ቀሪው ያሳለፈው ታሪክ የፈተና ነበር፡፡ ሆኖም ግን ጭቆናው ዴሞክራሲያዊ (ህዝባዊ) ያልሆኑ መንግስታት ባሉበት ቦታ ሁሉ ብዙሃኑ ላይ የሚጫን ቀንበር ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ በታሪኩ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ከደቡብ ወደ ሰሜን በመስፋፋት ያልሰፈረበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም፡፡ ከሁሉም ህዝብ ጋር ተቀላቅሏል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የራሱን ባህልና ቋንቋ ሲያወርስ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ከተስፋፋባቸው አካባቢዎቹ የቀድሞዎችን ነዋሪዎች ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ሀይማኖት ወርሷል፡፡ ‹‹ግማሽ ሲዳማ››፣ ‹‹ግማሽ ጉራጌ›› የሲዳማንና የጉራጌን ባህል የወረሱ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ የወሎ ኦሮሞዎች አማርኛ ቋንቋ እና እስልምና ሀይማኖት ወርሰዋል፡፡ ራያ እና አዘቦዎች ትግርኛ ቋንቋና ክርስትናን ወርሰዋል፡፡ … በዚህ መንገድ ኦሮሞዎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተሳስረዋል፡፡ ሶሾሎጂስቱ ዶናልድ ሌቪን የኦሮሞዎች እንዲህ ከሌሎች የመዋሃድ ችሎታ ትልቋን ኢትዮጵያ ፈጥሯል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝቦች አሁንም ከገዥው ጭቆና አልተላቀቁም፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ትላንቷ ኢትዮጵያ የመብት ጥያቄ ያነሱ ልጆች በኃይል ይጨፈለቃሉ፡፡ ይህንን ጭቆና ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በየራሳቸው መንገድ እየታገሉት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተባበረ ክንድ መታገል ባለመቻላቸው ጭቆናው ሊቆም አልቻለም፡፡ ብዙ የኦሮሞ ልጆች መፍትሄው የኦሮሚያ መገንጠል እንደሆነ ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ ኦነግ በቀድሞው ብርታቱ ባይኖርም መንፈሱ አለ፡፡ ብዙዎች የኦነግ መንፈስ የሚሉት ይህንን ‹‹እንገነጠላለን›› የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ብዙዎች የተሰውለት፣ ብዙዎች የታሰሩለት፣ ብዙዎች የተሰደዱለት ጥያቄ ይሄው ቢሆንም እስካሁን ለውጥ አላመጣም፡፡ በእኔ እምነት ጥያቄው ለውጥ ያላመጣው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ ትልቋን ኢትዮጵያ የመሰረተው የኢትዮጵያ ግንድ (የኦሮሞ ህዝብ) እንደቅርንጫፍ እገነጠላለሁ ማለቱ ነበር፡፡ ሁለተኛ ጠላታችን የሆነውን ጭቆና ማሸነፍ የምንችለው በመተባበር እንጂ በመለያየት ባለመሆኑ ነው፡፡
የጣልያን ወረራን ያሸነፍነው በተባበረ ክንዳችን እንጂ በተነጣጠለ ኃይል አይደለም፡፡ አሜሪካ ዓለምን የምትመራው ክፍለ ሀገሮቿ ተባብረው አንድነት ስለቆሙ ነው፡፡ አውሮፓውያን የአውሮፓ ህብረትን የመሰረቱት የአሜሪካን ኃያልነት በህብረት ለመቋቋም ነው፡፡ አፍሪካም ወደ ህብረት እየሄደች ነው፡፡ በህብረታችን ታሪካዊ ጠላታችን ጭቆናን ማሸነፍ ይቻላል፡፡ መገነጣጠል ግን ይብሱን ያደክመን ይሆናል እንጂ አይበጀንም፡፡ የኤርትራ መገንጠል ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት አላስገኘም፡፡ የደቡብ ሱዳን መገንጠል ለደቡብ ሱዳናውያን ሰላም አላመጣላቸውም፡፡ የሶማሊያ አንድ ብሄር መሆንና አንድ ሀይማኖት መከተል ከመበጣበጥ አላዳናቸውም፡፡ መዋጋት ያለብን ጭቆናን እንጂ ህብረታችንን አይደለም፡፡
ኦሮሚያን እንገነጥላለን የሚለው ጥያቄ ታላቋ ኢትዮጵያን ለመሰረተው የኦሮሞ ህዝብ ስድብ ነው፡፡ ሽንፈት ነው፡፡ ትግሉ መሆን ያለበት ጠንካራና ነጻ ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ ነው፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለዚህ ዓላማ (ሌሎች ፖለቲከኞች ባይመቿቸው እንኳ) የዴሞክራሲ ባህላቸውን ተጠቅመው ሊታገሉት ይገባል እንጂ የገነቧትን ትልቋን ኢትዮጵያ ጥለው እንገነጠላለን ማለት የለባቸውም እላለሁ፡፡ የታላቅነት ምስጢሩ ህብረት እንጂ ነጠላነት አይደለም፡፡ በህብረት እናሸንፋለን!
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46258#sthash.St8bLsFf.dpuf

No comments:

Post a Comment