በኢትዮጵያ ተከሰተ ስለተባለው ረሃብ በማህበራዊ ሚዲያና በኢንተርኔት ላይ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል። አብዛኞቹ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን (ቢቢሲ፣ ዘጋርዲያን፣ አልጀዚራ፣ ኒውስ 24) በኢትዮጵያ ውስጥ በዝናብ እጥረት ሳቢያ በተከሰተ ድርቅ የተጎጂዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን እንደደረሰ፣ እነዚሁን በረሃብ የተጎዱ ወገኖች ለመመገብ ለምግብና ለእህል ግዢ ተጨማሪ ከ320 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ሲዘግቡ ከርመዋል።
ለዝናብ እጥረት መንስኤውም የኤል ኒኖ የአየር መዛባት እንደሆነ በእነኚህ የመገናኛ ብዙሃን ተነግሯል፣ እየተነገረም ይገኛል። ችግሩ የከፋ እንደሆነና የዝናብ እጥረቱ አዝርዕትን ከማቅጨጭ አልፎ አድርቋል። በእነዚሁ ዝናብ-አጠር የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነዋሪዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፣ በምግብ ንጥረነገር ማነስ የተጎዱ ህፃናትና አዋቂዎች እንዳሉ የመስክ ጥናቶች ይፋ አድርገዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ዘንድሮ ምዕራብ አርሲን ጨምሮ ትርፍ አምራች የሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎችም ጭምር የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ። የውሃና የግጦሽ መመንመን ተከትሎ የአርብቶ/ አርሶ አደሮችን ከብቶች ቁጥር በሞት ምክንያት በእጅጉ እንዲቀንሱ አድርጓል፣ በመሆኑም አስቸኳይ አልሚ ምግብ በዚህ አመት ከሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ከእጥፍ በላይ [ከየካቲት 2007 (49%) እስከ ግንቦት 2007 (97%)] አድጓል። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ጊዜያዊ ሃላፊ “የበልግ ዝናብ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜትሮሎጂ ድርጀት ከተነበየው በተቃራኒው ለአጭር ብቻ ነው የዘነበው” ብለዋል።
ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ስንመጣ ደግሞ የተመጣጠነ እድገት በአገሪቷ ያለ ይመስል፣ “ኢኮኖሚያችን በ 11% አድጓል፣ ድህነት ታሪክ ሆኗል፣ በቀን ሶስት ጊዜ ለመብላት በቅተናል” የሚሉ መሰረት የሌላቸው አሉባልታዎችን በፊስቡክ ካድሬዎች ሲያናፍስ የቆየ ቢሆንም እውነት ተደብቃ አትቀርምና ይኸው የድርቁ መከሰት ሰሞኑን ገሃድ ሆኖ ወጥቷል። ሕወሃት/ ኢህአዴግ ድርቅ መኖሩን ሲያስተባብል ለረጅም ወራት የቆየ ቢሆንም በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ድርቅ መኖሩን ያጋለጠ አንድ መረጃ ወጥቷል። አንድ ግለሰብ ከአዲስ አበባ አፋር ሰመራ በሚወስደው መንገድ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ በድርቁ የሞቱ የቤት እንስሳትን ቪድዮ ቀርጾ በፊስቡክ በመልቀቁ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እየተነጋገሩበት ይገኛሉ። መረጃው የህወሃት ኢህአዴግን ውሸት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር። ከዚያ በኋላም ድርቅ የለም እያለ ሲክድ የቆየው የህወሃት ወያኔ መንግስትም ይህንን አውነታ እያቅማማም ቢሆን ወደማመኑ ደረጃ ደርሷል።
ከዚህ ጋር ተይይዞ በቅርቡ የምግብ እጥረት ይኖራል በሚል ግምት አለም አቀፍ ሚዲያዎች በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጡ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስትም አንዴ “ድርቅ በኢትዮጵያ የለም” ሲል ሌላ ጊዜ “በ አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ አለ ረሃብ ግን የለም” የሚል ውሃ የማይቋጥር አሰልቺ መከራከሪያ በተደጋጋሚ አቅርቧል። ችግሮች መኖራቸውን አምኖ እርምጃ አለመውሰድ የህወሃት ኢህአዴግ ባህርይ ይህ ነው። ኢህአዴግ ማለት ችግሮቹ አፍጥጠው በገሃድ እየታዩ ሽምጥጥ አድርጎ መካድን የተካነ ቡድን ነው።
ከዚህ ሁሉ “አለ!፣ የለም!” ንትርክ ድርቁ መከሰቱን በአለም አቀፍ ሚዲያና በማህበራዊ ድህረገጾች ከተነገረም በኋላም ቢሆን ኢህአዴግ “ድርቁና ረሃቡ ከአቅሜ በላይ አይደለም” የሚል አዲስ የመከራከሪያ ስልት ይዞ ብቅ ብሏል። ህወሃት/ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ “ከቁጥጥራችን ውጭ አይደለም የውጭ አርዳታም አያስፈልገንም” የሚል ሰንካላ መከላከያ በማቅረብ አንባቢውን፣ ተመልካቹንና፣ አድማጩን ለማደናገር ሞክሯል። መቼም ይህች አገርና ህዝቦቿ እውነት የማይናገሩና ለችግሮቿ መፍትሄ የማይሰጡ ጨካኝ መሪዎችን በተለያዩ ጊዜያት አስተናግዳለች። ኢትዮጵያ አርሶአደሮች በዝናብ እጥረት የተነሳ አዝመራ ሲበላሽባቸውና ሲራቡ፣ የአርብቶአደሮች የቀንድና የቁም ከብቶቹ በድርቁ ምክንያት ሲያልቁ፣ አይዟችሁ ብሎ ድጋፍ የሚሰጥ ሳይሆን፣ ምንም አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረ አድርጎ በማሰብ ለህዝቡ አገልግሎት ከማበርከት ይልቅ ለግል ጥቅምና ዝና የሚጨነቁ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደአሸን የፈሉባት አገር ሆናለች። በቅርቡ በተከሰተው ድርቅና ረሃብ አቶ ሬድዋን ሁሴን እና አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሁነኛ ተዋናዮች ሆነው መድረኩን ተቆጣጥረውት ነበር።
ከድርቅ ጋር በተያያዘ የጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ሬድዋን ሁሴን “የከብቶች መሞት የተከሰተው ባለቤቶቹ ለከብቶቻቸው በጊዜው ውሃ ስላላጠጧቸው ነው” የሚል አላጋጭ መልስ ለመገናኛ ብዙሃን በመስጠት በድርቁ በተጠቃው ህዝብ ላይ ተሳልቀዋል። ይህ ንግግራቸው የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት የአስተሳሰብ ደረጃቸው ምን ያክል የዘቀጠ እንደሆነ ያሳየ ክስተት ነው። አቶ ሬድዋን የባዮሎጂ መምህር ናቸው። እናም የአርብቶ አደሩን የከብት አያያዝና አረባብ ባህል በደምብ የተረዱ አልመሰለኝም። እንዲያውም ለእርሳቸው የአርብቶ አደር ህይወት እጅግ ውስብስብ መሆኑን የተረዱት አይመስልም። አርብቶ አደር የቁምና የቀንድ ከብቶች እንዲሁም በግና ፍየሎችን ለረጅም ዘመናት [ያለሳይንሳዊ ድጋፍ] ሲያረባ የኖረ ህዝብ ነው። አቶ ሬድዋን ያልተረዱት ጉዳይ የአሁኑ የቤት እንስሳት በጅምላ መሞት ውሃ ማጠጣት ወይም አለማጠጣት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ነው። እኛ እስከምናውቀው ድረስ አርብቶ አደሩ ሆነ አርሶ አደሩ ከራሱ አስበልጦ ለቤት እንስሳት እንክብካቤ የደርጋል። የቤት እንስሳት ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች ህይወት ናቸው። የእኛ ህዝብ ከህይወቱ ጋር የተቆራኙ እንስሳትን አይደለም በቸልተኝነት ውሃ ባለማጠጣት እንዲሞቱ ማድረግ ይቅርና፣ አርዶ ለመብላት እንኳን በጣም የሚቸገር ህዝብ ነው። ለዚያም ነው እንስሳቱ እየሞቱ ምንም ምርጫ ስለሌለው ዝም ብሎ እያየ ያለው። አቶ ሬድዋን ደግሞ ያልመለሱት ጥያቄ ቸልተኛ ሆነው ውሃ ሳያጠጡ የቀሩት ስንት አርሶ/አርብቶ አደሮች ናቸው? የሚለው ነው። እዉነት ሁሉም አርብቶአደር ውሃ ባለበት አካባቢ እንስሳቱን አልወሰደም? ውሃ አላጠጣም? ወይስ አቶ ሬድዋን የተለመደ ህወሃታዊ አነጋገር ማንጸባረቃቸው ነው? የጊዜ ጉዳይ ነው። ይህ ሃላፊነት የጎደለው አነጋገር የኋላ ኋላ አቶ ሬድዋንን ዋጋ ያስከፍላቸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አምባሳደሮችንንና ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን ሰብስበው ባናገሩበት ወቅት ድርቁን በጣም አቅልለው አይተውታል። የእርሳቸው ንግግር ሃላፊነት የጎደለው ነው። እሳቸው ህወሃት ባዘጋጀላቸው አልጋ እየተኙ የቤተመንግስት ምግብ እየበሉ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መብላት ያልቻለን አርሶ/አርብቶ አደርን ችግር ለማጣጣል መሞከራቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። እሳቸው አንድ ቀን እራት ሳይበሉ ቢያድሩ ረሃብ ምን ያክል የሚያንገበግብ መሆኑን የሚያውቁት አይመስለኝም። ይባስ ብለውም አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ድርቁን ራሳችን መቋቋም እንችል እንደሆነ ዳር ላይ ሆነው እያዩን ነው የሚል አሁንም ሃላፊነት የጎደለው ንግግር ሲናገሩ በተሌቪዥን አየኋቸው። ባይዋሹ ጥሩ ነበር፣ ውሸት አንድ አገር እመራለሁ ከሚል ጠቅላይ ሚኒስትር አይጠበቅም። እናም ጉዳዩ እርሳቸው እንዳሉት ሳይሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ 320 ሚሊዮን በላይ የሚጠጋ ገንዘብ ከእርዳታ ለጋሽ አገሮች እየፈለገ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። የአቶ ሃይለማሪያም መንግስት መደበ የተባለው ገንዘብ ግን 33 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ታዲያ ተቆርቋሪው ማነው? እኔ እስከሚገባኝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተቆርቋሪና ደራሽ የውጭ የእርዳታ ድርጅቶችና መንግስታት እንጂ ድርቁንና ረሃቡን የደበቁትና የካዱት ሃይለማሪያም እና እሳቸው የሚመሩት መንግስት አይደለም። ታየኝ እኮ በ 33 ሚሊዮን ዶላር ድርቁንና ረሃቡን ሲከላከሉ!
አቶ ሃይለማሪያ እንደዋሹን የድርቁና ረሃብ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በምግብ እጥረት የሚሰቃየው ሰው ቁጥር በ 55% በመጨመር ከ2.9 ሚሊዮን አሻቅቦ ወደ 4.5 ሚልዮን ከመድረሱም ባሻገር የእርዳታ ፈላጊው ቁጥር እስከ ሚያዚያ 2008 አሁን ካለው አህዝ ቢጨምር እንጂ እንደማይቀንስ መገለጹ ነው። አቶ ሃይለማሪያ በንግግራቸው ወቅት ትዝብት ላይ የጣላቸው ሌላው ነገር፣ ዕርዳታ ለጋሽ ድርጅቶችና አገራት እንደ ኢህአዴግ ሃላፊነት የጎደላቸው አድርገው መናገራቸው ነው። ለዘመናት በምግብ እጥረት የሚሰቃየውን ህዝብ ሃላፊነት ወስደው ህይወቱን እያተረፉት ያሉትን ለጋሽ ድርጀቶች በምን ሂሳብ ነው ህወሃት/ ኢህአዴግን አምነው “ትወጡት እንደሆነ ዳር ላይ እናያለን” የሚሉት? እርዳታ ድርጅቶቹ በሰብአዊ ድርጊታቸው ከወያኔ ጋር ማወዳደር የሚቻል አይሆንም። ምዕራብያውያን ህወሃት በሰው ህይወት ላይ የሚሰራውን ድራማ አብረው አይተውኑም። አቶ ሃይለማሪያም ይህንን ንግግር ሲናገሩ “በምዕራብያውያን መንግስታት ተዓማኒነት አለን” ለማለት የተናገሯት ቀልድ እንደሆነች ይገባናል። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ይህንን ሲናገሩ በእውነት ለጋሽ ድርጅቶች አማርኛ አይሰሙም ብለው አስበው ይሆን? ከሰሙኝ ይታዘቡኝ ይሆናል አይሉም? የ 320 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በተመለከተ የ ዩኒሴፍ ተወካይና ጊዜያዊ ሃላፊ ሚስ ሜሊሶፕ “ለጋሽ ድርጅቶች ቸር መሆን አለባቸው፣ የተፈጠረውን ቀውስ በእነሱ በተለመደ ድጋፍ እንሸፍናለን” በማለት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል። ይህም ኢህአዴግ ኖረ አልኖረ ምዕራብያውያን አገሮች በድርቁ ለተጎዳው ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ ዕርዳታ መስጠታቸውን ለአፍታም ቢሆን የማያቋርጡ አጋር መሆናቸውን ያሳዩበት ቃል ኪዳን ነው። ምዕራብያውያን ዕርዳታ ለጋሽ ድርጅቶችና አገራት ኢህአዴግን ሳይጠይቁ የራሳቸውን መርሃግብር አውጥተው በድርቅ የተጎዱ ተረጂዎችን ወደፊትም ይታደጓቸዋል። አቶ ሃይለማሪያም ያላወቁት ግን 100% በህዝብ ድምፅ ተመረጥኩ ያለው ኢህአዴግ ድርቅና ረሃብን ከመመከት አኳያ ምንም ተጨባጭ ሚና አለመጫወቱን ነው።
አቶ ሃይለማሪያም ሌላ የተጣረሰ መረጃ የወያኔ አምባሳደሮችና እና ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን በሰበሰቡበት ወቅት ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት በምግብ እጥረት የተነሳ ለከፋ ሁኔታ ተዳርገው በማቆያ ጣቢያ እንዲመገቡ የተደረጉ ህጻናት የሉም ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ያወጣው መረጃ ደግሞ እሳቸው ካሉት በተቃራኒው ነው። እንደ ተመድ (UN) መረጃ ከሆነ በምግብ የተጎዱ የህጻናት ቁጥር በቅርቡ በ 14.4 ፐርሰንት በማደግ 302,605 ደርሷል። ታዲያ ለአቶ ሃይለማሪያም በምግብ የተጎዱ ህጻናት እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ ሳይመልሱ ፌዝ በመሰለ ንግግራቸው አምባሳደሮችን ሸኘተዋቸዋል። አቶ ሃይለማሪያ ደሳለኝ በምግብ እጥረት መጎዳት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እንኳን ሳያገናዝቡ የህወሃት ኢህአዴግ የውሸት ቅርሻት ተፍተውብናል። 14 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተራቡበት አገር ምንም አዲስ ነገር እንዳልተከሰተ በማውራት የህወሃት ባለስልጣናትን ስኬት ብቻ መዘርዘራቸው ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል። ከንግግራቸው የተረዳነው ሃይለማሪያም በራሳቸው የሚያስቡ ሳይሆኑ ከመጋረጃ ጀርባ በተቀመጡ መሪዎቻቸው በሩቅ መቆጣጠሪያ (ረሞት ኮንትሮል) የሚንቀሳቀሱ ግለሰብ ናቸው።
እኔን እያሳሰበኝ ያለው የወደፊቱ የአገራችን ሁኔታ ነው። መቼ ነው ሃላፊነት የሚወስድ መንግስት የሚኖረን? የረሃቡ ጉዳይ እስከመቼ ይሆን በመንግስት ባለስልጣናት በዝምታ የሚታለፈው? ህዝባችን ሲራብ ለምን ዝም ይባላል? ድርቅ ሲከሰት የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት ትዝብት ላይ የሚጥል ነገር ለምን በአደባባይ ይናገራሉ? መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለአገር ውስጥ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ችግሩ ሲከሰት ለምን ይፋ አያደርግም? በአገራችን የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ፣ ማህበራዊና፣ ፖለቲካዊ ችግሮች የምንሰማው ከምዕራባውያን አገራት ወይም የአለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ባለስልጣናት ነው። ታዲያ የእኛ አለቆች ምንድነው የሚሰሩት? ምንስ እያደረጉ ነው ያሉት? ተመረጥን ያሉት አገርንና ወገንን ለመጥቀም መስሎኝ? በችግር ጊዜ ጥሪ ሊያሰሙ መስሎኝ? እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች የሚመልስልኝ ሁነኛ ሰው አጣሁ። ምን አልባትም እንደተለመደው የውጭ አገር ባለስልጣናት መልሱን አንድ ቀን ሊመልሱልኝ ይችሉ ይሆናል።
ከላይ እንደተገለጸው አሁን ያሉት የህወሃት/ ኢህአዴግ አምባገነኖች ለራሳቸው ስልጣንና ክብር ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ደንታ የሌላቸው ናቸው። ኢትዮጵያም የልመና እና እርዳታ ተምሳሌት ሆና እንድትቀጥል ህዝቡን ማስተባበር ያልቻሉ ራስ ወዳዶች ናቸው። እኛም እነዚህን ሃፍረተቢስ ዋሾዎችን መሪዎቻችን ናቸው ብለን ዝም ብለን መቀመጣችን ይገርማል። እስካሁን የሰሩት ጥፋት እንዳለ ሆኖ፣ ለእነዚህ ሰዎች በአንድነት ውሸት በቃችሁ ልንላቸው ይገልባል። ስልጣን ላይ በምርጫ [እነሱ እንደሚሉት] ይሁን በጉልበት [አለም እንደሚያውቀው] የተቀመጡት ህዝብን ሊያገለግሉት እንጂ ሊያፌዙበት አይደለም። በመሆኑም እነዚህ ግለሰቦች ማፌዝ አቁመው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ወገኖቻችንን በረሃብና በድርቅ አስጨርሰን ዝም የምንልበት ምክንያት አይታየኝም።
No comments:
Post a Comment