–በመቶ ሚሊዮን ብሮች ተጠርጥረዋል
በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት
ሁለት ወራት ሲፈለጉ የቆዩት የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
አቶ ወንድሙ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በፌዴራልና በኦሮሚያ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ጥምረት ነው፡፡ በሁለቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የተዋቀረው ግብረ ኃይል ተጠርጣሪውን ግለሰብ ነሐሴ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ምድብ ችሎት በማቅረብ፣ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የ11 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አቶ ወንድሙ የተጠረጠሩት የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅትና ከዚያ በኋላም የኦሮሚያ ክልል ብድርና ቁጠባ ተቋም ምክትል ኃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ጊዜያት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ገንዘብ በመመዝበር የሙስና ወንጀል ነው፡፡
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር፣ ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ፣ አቶ ወንድሙ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና በቁጥጥር ሥር ሊወሉ የቻሉት መንግሥት ማግኘት የነበረበትን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አሳጥተዋል በሚል ምክንያት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ከክልሉና ከፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ አቶ ወንድሙ ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት፣ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበት ግብርና ታክስ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች የሰበሰቡትን ቫት ሆን ብለው ለመንግሥት ገቢ እንዳይሆን በማድረግና ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡ ግለሰቡ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ማግኘት ያለባቸውን ገቢ አሳጥተዋል ተብለው ስለተጠረጠሩ ሁለቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በትብብር መሥራት መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪውን ግለሰብ ለፍርድ ለማቅረብ በሚሞከርበት ወቅት ተጠርጣሪው በመሰወራቸው ከሁለት ወራት ፍለጋ በኋላ በአዳማ ከተማ መያዛቸው ታውቋል፡፡
አቶ ወንድሙ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም ከፍተኛ ንብረት ማካበታቸው ምርመራ እንዲደረግባቸው መንስዔ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለሁለቱም የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጥቆማዎች ደርሰዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በሻሸመኔና በምሥራቅ ሐረርጌ ቦርዶዴ አካባቢ የሚገኙ የጫት ኬላዎች ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢ ለግል ጥቅም ሲያውሉ ቆይተዋል የሚል ጥርጣሬ መኖሩን፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖቹ መረጃ ያመለክታል፡፡
አቶ ወንድሙ የሥራ ጊዜውን ባጠናቀቀው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል ነበሩ፡፡ ኦሕዴድ አቶ ወንድሙን በ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ዕጩ አድርጎ እንዳላቀረባቸው ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት አቶ ወንድሙ ያለመከሰስ መብት የሌላቸው በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው ተገልጿል፡፡
አቶ ወንድሙ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ምክትል ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ቆይተው፣ ከ30 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ሕገወጥ ግዥ ተጠርጥረው ከወራት በፊት ከምክትል ኃላፊነታቸው መነሳታቸው ታውቋል፡፡
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/9512#sthash.z2e3fnq4.dpuf
No comments:
Post a Comment