ከዊሃ እስከ ኦምሃጀር – አንድ ሰሞን ከአርበኞች ጋር (ኤፍሬም ማዴቦ)
ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። አዎ! ማተቡን ላጠበቀና በአምላኩ ለሚታመን በእርግጥ ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። ሰዉ ነኝና እንደ ፈጣሪ ቃሌ ሁሉ እዉነት ነዉ ብዬ አለተፈጥሮዬ አላብጥም። ግን ሰዉ ብሆንም ፈጣሪዬን የምፈራ ሰዉ ነኝና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስል ልቦናዬ እያወቀዉ እንደነ ጋሼ እንደልቡ ዉሸት ደርድሬ ለአንባቢ የማቀርብበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ቀጥሎ የማስነብባችሁ እያንዳንዱ ቃል እንደ ዳያስፖራ ተረተኞች የምተርተዉ ‘ሰዉ ሰዉ’ የማይሸተት ተረት ሳይሆን ኢትዮጵያ ድንበር ላይ በየግንባሩ የተሰለፉትንና በስልጠና ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አርበኞች ስጎበኝ በአይኔ ያየሁትንና በጆሮዬ የሰማሁትን ቃል ነዉ።
እንደፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ረቡዕ ኦጎስት 5 ቀን ከሌሊቱ 9 ሰዐት የተሳፈርኩበት አዉሮፕላን አስመራ አለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ አይኔ ላይ ዉል ዉል እያለ ልቤን የሰቀለዉ የሚጠብቀኝ የትግል ዉጣ ዉረድ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ በ22 አመቴ ስራ የጀመርኩባት ዉቧ የአስመራ ከተማ ምን ትመስል ይሆን የሚል የሀሳብ ዉጣ ዉረድ ነበር። ሆኖም አካልም መንፈስም እየከዳ ምንም ነገር ማሰብ አይቻልምና ወደ ግዜያዊ ማረፊያ ቦታዬ እንደወሰዱኝ ለሁለት ቀን ከግማሽ የተጠራቀመ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ።
ረቡዕ ከቀኑ አንድ ሰዐት አካባቢ “እባክህ ተነሳና ምሳ እንብላ” የሚል የሁለት ሰዎች ድምጽ ተራ በተራ ጆሮዬ ዉስጥ ገባና እንቅልፌን ሰለበዉ. . . መነሳት ባልፈልግም በልቤ ትግሉ ተጀመረ አልኩና ከተጋደምኩበት ቀና አልኩ። ፊት ለፊቴ ቆመዉ ተነስ እያሉ የሚጨቀጭቁኝ የትግል ጓደኞቼ ነአምን ዘለቀና ብርሀኑ ነጋ ነበሩ። ምሳ ላይ ተቀምጠን እነሱ የሚያወሩት ወደ ኤርትራ በረሃዎች ሰለሚደረገዉ ጉዞ ሲሆን እኔ ደግሞ በወጣትነቴ ስለማዉቃት የአስመራ ከተማ ነበር። አስመራን ትቼ ከነሱ ጋር እንደነሱ ማሰብ ሞከርኩ . . . አሁንም አሁንም ሞከርኩና ሲያቅተኝ ተዉኩት። በተለይ ምሳ የበላንበት ካራቨል ሬስቶራንት ዉስጥ በወጣትነቴ ብዙ ትዝታዎች ነበሩኝና ጭራሽ ምግቡን ትቼ በምናብ ወደ ወጣትነቴ ሽምጥ ጋለብኩ። ባር ኡጎ፤ ባር ቱኔል፤ ባር ፀአዳ ፈርስ፤ ባር እምባባና የባቢሎን ጋጋታ እንዳለ ፊቴ ላይ እየመጡ ተደቀኑ። ቀና ስል ነአምንና ብርሀኑ . . . አትበላም እንዴ አሉኝ። ወደ ኋላ ሽምጥ ያስጋለበኝን ፈረሴን ልጓም ያዝ አደረኩና ካሁን በኋላ ወደፊት ብቻ ብዬ ከሁለቱ ጓደኞቼ ጋር በአካልም በመንፈስም ተቀላቀልኩ።
የአስመራ ከረን መንገድ ከተነጠፈ አስፋልት ዉጭ ሌላ ምንም አይቶ ለማያዉቅ ለእንደኔ አይነቱ የዳያስፖራ ‘በለስ’ ቀርቶ ደጋግሞ የተጓዘበትንም ሰዉ ልብ ይሰልባል። አስመራን ይዞ፤ አዲአቤቶንና እምባደርሆን ይዞ በአዲተከለዛን፤ በኢላበርዕድ፤ በከረንና በሀጋዝ አድርጎ አቆርደት ድረስ የሚዘልቀዉ መንገድ የአለም ተራራዎች ስብሰባ ተጠራርተዉ ወደየመጡበት ላለመመለስ ተማምለዉ የመሸጉበት ቦታ ይመስላል። አንዱን ተራራ ሽቅብ ወጥተንና ቁልቁል ወርደን እፎይ ብለን ሳንጨርስ ሌላዉ ከተፍ ይላል። በስተቀኛችን ያለዉን ተራራ አይተን ወይ ጉድ ስንል በግራችን ያለዉ ድንቄም ጉድ እያለ ያሾፍብናል። እልፍ ስንል ተራራ፤ ከዚያም ተራራ፤ተራራ፤ ተራራ ብቻ ነዉ። ፊት ለፊቴ የማያቸዉ ተራራዎች ተፈጥሮ የቆለለዉ የዲንጋይ ክምር ሳይሆን አዋቂ በዉኃ ልክ እየጠረበ የደረደረዉ ሾጣጣ ኃዉልት ይመስላሉ። አንኳን ለሰዉ ልጅ ለገደሉ ንጉስ ለዝንጀሮም አይመቹም። ባጠቃላይ የአስመራ አቆርደትን መንገድ ሲመለከቱት እንደ አጥር ከተሰለፉት ተራራዎች ባሻገር አገር ያለ አይመስልም። አላማና ጽናት ላለዉ ሰዉ ግን ከተራራዉ ወዲያ አገር ከአገርም ወዲያ ሌላ. . . ሌላ ወያኔ የቀማን አገር አለ።
አላማ የሌለዉ፤ ሆዱ ያልቆረጠ፤ ፈሪ፤ ወኔ የከዳዉና አይኑን ተራራዎቹ ላይ ብቻ ያሳረፈ ሰዉ ከአስመራ ተነስቶ በከረን በኩል አቆርደትን አቋርጦ የጀግኖቹ መንደር ሀሬና የሚደርስ አይመስለዉም። ለዚህ ነዉ ሁሉን የሚችል እግዚአብሄር አይዞህ ብሎ የላከዉ የብሉይ ኪዳኑ ነቢዩ ኤልያስ ኤልዛቤልን ፈርቶ እንደሸሸ ሁሉ የኛም ዘመን ጋዜጠኛ ነን ባዮች፤ ዘፋኞችና አርበኛ ነን ባይ የሀሰት ነቢያት ገና ከረን ሳይደርሱ ተራራዉን እየፈሩ በኤርትራ በኩል ምንም ነገር መስራት አይቻልም እያሉ እንደ ግመል ሽንት የኋሊት የሚጓዙት። ድንቄም ጋዜጠኛ! ጋዜጠኛ ታሪክ ሸራርፎ በሰጠዉ ግዜ እየኖረ ያየዉንና የሰማዉን ለትዉልድ እያስተላለፈ ለራሱ የማይኖር ልዩ ፍጡር ነዉ። የኛዎቹ “ጋዜጠኛ” ነን ባዮች ግን እራሳቸዉ ለራሳቸዉ በሰጡት ግዜ እየኖሩ የራሳቸዉን ግሳንግስ የፈጠራ ታሪክ የሚነግሩን ከህያዉ በታችና ከሙታን በላይ ባለዉ ባዶ ቦታ የሚኖሩ ባዶዎች ናቸዉ። አምላክ በምህረቱ ወደ ላይ ይሳባቸዉና ከህያዋን ጋር ይቀላቅላቸዉ።
ምድረ የወሬ ቋቶች ይግባችሁ! የኢትዮጵያ ህዝብ ዉኃ ዉኃ የሚያሰኝ የእሳት ጉድጓድ ዉስጥ ነዉ ያለዉ፤እሱ ከጉድጓዱ ባስቸኳይ መዉጣት እንጂ እንደናንተ በኤርትራ በኩል ከሆነ ይቅርብኝ ብሎ የሚጃጃልበት ግዜዉም ትዕግስቱም የለዉም። ለነገሩ እነዚህ የወሬ አርበኞች ተራራ ወጥተዉ፤ በረሃ አቋርጠዉና ወንዝ ተሻግረዉ ከወያኔ ጋር ሳንጃ ሊማዘዙ ቀርቶ የገዛ ልጆቻቸውን የልደት ኬክ ደፍረዉ በቢላዋ የማይቆርጡ የ”ዳዉን ታዉን” ቅምጦልች ናቸዉና ከነወሬያቸዉ እዚያዉ “ዳዉን ታወን” ብንተዋቸዉ የሚበጅ ይመስለኛል። አይደል?
ወሬና ስራ ለየቅል ናቸዉ፤ ለወሬ የሚያስፈልገዉ ሹል አፍ ብቻ ነዉ። ለስራ ግን አፍ፤ እጅ፤ አግር፤ አይን፤ ጆሮና የሚያስብ አዕምሮ ያስፈልጋል። ወረኛና ለስራ ያልተፈጠረ ሰዉ የተራራዉ ከፍታ እየታየዉ “በዚህ በኩል እንዴት ተደርጎ” እያለ የወሬ ቱማታዉን መደርደር ይጀምራል። የሚሰራ ሰዉ ግን ግቡ ከተራራዉ ባሻገር ከተከዜ ማዶ ነዉና ተራራዉን ሽቅብ ወጥቶና ከጠመዝማዛዉ መንገድ ጋር እኩል ተጠማዝዞ ወዳለመዉ ግብ ይጓዛል። አንባቢ ሆይ! ሠራተኛ በለኝ አትበለኝ እሱ ያንተ ጉዳይ ነዉ፤ መዳረሻዬ ከተከዜና ከመረብ ወንዞች ባሻገር መሆኑንና አላማዬም ፍትህና ነጻነት መሆኑን ግን እኔዉ እራሴ አብጠርጥሬ ልነግርህ እችላለሁ። የምወደዉን አንድ ልጄንና ጥሩ ስራዬን ደህና ሁኑ ብዬ በረሃ የገባሁት እናት አገሬ ዉስጥ ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ አብበዉ ለማየት ነዉ እንጂ የኤርትራ በረሃና ተራራ ናፍቆኝ አይደለም። የናፈቀኝ ተራራና በረሃ ቢሆን ኖሮ አሪዞናና ኮሎራዶ ይቀርቡኝ ነበር።
ዉቧን የአቆርደት ከተማና ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ያሰሩትን ግዙፍ መስጊድ በስተቀኝ እያየን ወደ ባሬንቱ ስናመራ ያ ከአስመራ ጀምሮ የተከተለን የተራራ መንጋ ፀሐይ እንደገላመጠዉ በረዶ እየሟሸሸ ሄዶ ገና ሀይኮታ ሳንደርስ ሜዳ ሆኖ አረፈዉ። የበረሃዉ ሙቀት እንዳለ ቢሆንም ባሬንቱ ስንደረስ የሚነፍሰዉ ቀዝቃዛ አየር ሙቀቱን አለዝቦታል። ባሬንቱን ለቅቀን ወደ ተሰነይ ስናመራ መሬቱ ሜዳ፤ ሰማዩ ደመናማ፤ አየሩ ነፋሻማ እየሆነ ይመጣል። ትናንሽ ልጆች እዚህም እዚያም ይዘልላሉ፤ ትራክተሩ ያርሳል፤ ግረደሩ ይዳምጣል፤ እንደኔ አይነቱ ጠመዝማዛዉ መንገድ ቀልቡን የሰለበዉና ፀሐዩ ያቀለጠዉ ምስኪን ደግሞ ወላዲት አምላክ ምን በደልኩሽ እያለ ያምጣል። ባሬንቱ ያኔ እኔ ሳዉቃት የጋሽና ሰቲት አዉራጃ ዋና ከተማ ነበረች፤ ዛሬ ከሃያ ስምንት አመት በኋላ ያየኋት ባሬንቱ ግን ከፍተኛ የንግድና የእርሻ እንቅስቃሴ ይታይባታል፤ ዉብትም ስፋቷም በእጥፍ ጨምሯል ፤ደግሞም የዛሬዋ ባሬንቱ የጋሽ ባርካ ዞን ዋና ከተማ ናት።
ከባሬንቱ ወደ ተሰነይ ሲወጣ ግራና ቀኝ አዉራጎዳናዉን ይዞ ኢትዮጵያና ሱዳን ጠረፍ ድረስ የተንጣለለዉ መሬት የኤርትራ የእህል መቀነት ነዉ። አካባቢዉ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ይታይበታል። የኤርትራን ልማትና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ማየት የፈለገ ሰዉ ከአስመራና ከሌሎች ትላልቅ ከተማዎች ወጥቶ ገጠር መግባት አለበት። ግድቡ፤ እርሻዉ፤ የጤና ተቋሙና ሌላም ሌላ የመሠረተ ልማት ምልክቶች በጉልህ የሚታዩት ገጠሪቱ ኤርትራ ዉስጥ ነዉ።
ከተሰነይ ወጥተን ጥቂት እንደተጓዝን መኪናችን አስፋልቱን ለቅቃ ኮረኮንቹ መንገድ ዉስጥ ገብታ ስትንገጫገጭ ከእንቅልፌ ነቃሁና እንደመንጠራራት ብዬ . . . ደረስን እንዴ አልኩ … የመኪናችንን ሾፌር። ገና ነዉ ትንሽ ይቀራል አሉ ወደኋላ ዞር ብለዉ። እንዳዉ ለነገሩ ነዉ እንጂ ሰዉዬዉ ዬት እንሄዳለን፤ መቼ አንሄዳለን ወይም መቼ እንመለሳለን ለሚሉ ጥያቄዎች በፍጹም መልስ አይሰጡም። ወያኔ የማይሰማን ሁሉንም ነገር ሆዳችን ዉስጥ ከያዝነዉ ብቻ ነዉ የሚል ፈሊጥ አላቸዉ። ዋናዉን መንገድ ለቅቀን ኮረኮንቹን ከተያያዝነዉ በግምት ከ20 ደቂቃ በኋላ አርበኞች መንደር ቁጥር አንድ ደርስን። ዘፈኑ፤ ጭፈራዉ፤ ሆታዉና ዕልልታዉ ቀለጠ። አርበኛዉ ጠመንጃዉን እንደታቀፈ እየዘለለና እየፎከረ እንኳን ደህና መጣህልን እያለ መሪዉ ላይ ተጠቀለለ። “የወያኔ ዘረኞችና አንዳንድ ተላላዎች አንተንና ጓዶችህን ትኩስ ሀምበርገር እየበላችሁ ወጣቱን በረሃ ዉስጥ ታስጨርሳላችሁ” እያሉ አርበኛዉንና መሪዉን ለመለያየት ብዙ ጥረዋል። እናንተ ግን የሞቀ ኑሯችሁን ትታችሁ ታግላችሁ ልታታግሉን በረሃዉ ድረስ መጥታችሁ ተቀላቅላችሁናል . . . እሴይ የኢትዮጵያ አምላክ! . . . ወያኔ የተሸነፈዉ ዛሬ ነዉ እየለ አርበኛዉ በሆታና በዕልልታ ከዉስጥ የመነጨ ደስታዉን ገልጸ። ብቻ ምን አለፋችሁ ጀግኖቹን ያሉበት ቦታ ድረስ ልናይ ሄደን የጀግና አቀባበል ተደረገልን። እንደ አንድ ታጋይ ድል አፋፍ ላይ ልድረስ አልድረስ አላዉቅም፤ ማሸነፋችንን ግን አረጋገጥኩ።
የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዉን እንዳቀፈ ሰላም ሊለኝ ሲመጣ ትኩር ብዬ አየሁት። ወጣት ነዉ፤ ጽናቱና ቁርጠኝነቱ ፊቱ ላይ ይነበባል። በፈገግታ የታጀበዉ የዋህ ፊቱ ልጅነቱን በአዋጅ ይናገራል። ዕድሜዉ ከሃያ አይበልጥም። ተቃቅፈን ሰላም ስንባባል እጅብ እጅብ ብሎ የተጎነጎነ ፀጉሩን በእጄ እያሻሸሁ “እቺን ነገር ታበድረኛለህ” አልኩት ፀጉር እየከዳዉ ያስቸገረኝን እራሴን እያሳየሁት። ችግር የለም አለኝ። “ችግር የለም” በአርበኞቹ ሠፈር የተለመደ አባባል ነዉ። የበረሃዉ ንዳድ፤ የዉኃዉ ጥማት፤ የምግብ ችግር፤ ክብደት ተሸክሞ ተራራዉን ሽቅብ መዉጣትና ባጠቃላይ ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን ማስወገድ ለአርበኛዉ ችግር አይደለም። አርበኛዉ ለእንደነዚሀ አይነት ችግሮች ተዘጋጅቶ ስለመጣ እንደችግር አይመለከታቸዉም።
ድንኳን ዉስጥ ገብተን ቁጭ እንዳልን . . . . እዚህ አካባቢ ችግራቸሁ ምንድነዉ አልኩት። ይምጡ አለኝና ከድንኳኑ ይዞኝ ወጥቶ ገዢ መሬት ይዘዉ የመሸጉትን የተለያዩ ካምፖች አሳየኝና የእያንዳንዳቸዉን ስም ነገረኝ። ሁላችንም የመጣነዉ ከኢትዮጵያ ነዉ፤ ሁላችንም የምንታገለዉ ወያኔን ነዉ፤ ደግሞም የሁላችንም ጥያቄ ፍትህ፤ ነጻነትት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ ነዉ. . . .. ግን አንድ ላይ አንታገልም። እስከመቼ ነዉ የአንድ አገር አርበኞች ከአገራችን ወጥተን፤ የተለያየ ድንኳን ተክለን፤ በተናጠል የጋራ ጠላታችንን የምንዋጋዉ? እባካችሁ ገላግሉን ብሎኝ ቀና ሲል አይኑ ካይኔ ገጠመ። በአፉ ከነገረኝ በአይኑ የነገረኝ በለጠብኝ። እንዲህ አይነቱን ብስለት የተሞላዉ ንግግር የሰማሁት ከልጄ ብዙም ከማይበልጥ ኢትዮጵያዊ ወጣት መሆኑ ሲሰማኝ እራሴን ታዘብኩት፤ ኢትዮጵያዊነቴን ግን ከወደድኩት በላይ ወደድኩት። አዎ አሁንም አሁንም አትዮጵያዊነቴን ከነችግሩ ወደድኩት። ደግሞስ ዬኔ ስራ ችግር መፍታት ነዉ እንጂ የአገሬ ችግር ፊቴ ላይ በተደቀነ ቁጥር ኢትዮጵያዊነቴን ጥያቄ ዉስጥ ማስገባት አይደለም።በነገራችን ላይ በተናጠል የሚደረገዉ ትግል አያዋጣምና “እባካችሁ አንድ አድርጉን” የሚለዉ ጥያቄ የአንድ አርበኛ ጥያቄ ሳይሆን በየሄድኩበት ካምፕ፤ ግምባርና ምሽግ ዉስጥ ከአብዛኛዉ አርበኛ አፍ የሚወጣ ጥያቄ ነዉ።
ቀኝ እጄን ወጣቱ አርበኛ ግራ ትከሻ ላይ አሳረፍኩና በሌባ ጣቴ በርቀት የሚታዩትን ካምፖች እያሳየሁት… አንዱጋ መሄድ እንችላለን አልኩት። አይ ጋሼ አሁን መሽቷል አለኝ። ሰዐቱ ገና ከቀኑ 9 ሰዐት ቢሆንም ሰፈሩ የአርበኞች ስለሆነ በነሱ ህግ መተዳደር አለብኝ ብዬ እሺ አልኩት። አይዞት እናንተ አስተባብራችሁ አንድ አድርጉን እንጂ ሌላ ሌላዉ ችግር የለዉም አለኝ። እኔም እንደ ወጣቱ አርበኛ በድፍረት “ችግር የለም” ለማለት ባልደፍርም . . . አይዞህ ትብብርን በተመለከተ በቅርብ ግዜ ሁላችንንም የሚያስደስት ዜና አብረን እንሰማለን አልኩት። ፈገግ አለና እሱን ከጨረሳችሁልን ሌላዉን ለኛ ተዉት አለኝና ይዞኝ ወደ ድንኳኑ ገባ።
ሐሙስ ነኃሴ 13 ቀን ጎህ ሳይቀድ ከእንቅልፌ ተነሳሁና ትንሽ ዞር ዞር ብዬ አልጋዬ ላይ ተመልሼ መጽሐፌን ማንበብ ጀመርኩ። ሁለት ምዕራፍ ጨርሼ ሦስተኛዉን ልጀምር ስል ከሩቁ ቡና ቡና ሸተተኝ። ቀና ብዬ ስመለከት ፍረወይኒ የቆላችዉን ቡና እስከነማንከሽከሻዉ ተሸክማ ልታስሸትተኝ ስትመጣ አየኋት፤ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ቁርስ ደረሰ እንዴ ብዬ ማንከሽከሺያዉ ላይ የሚንቦገቦገዉን ጭስ በእጄ ደጋግሜ ወደ አፍንጫዬ ሳብኩት። ‘ኡወ ቁርሲ ደሪሱ’ ብላ ፍረወይኒ የተቆላዉን ቡና ይዛ ወደ መጣችበት ተመለሰች።
ከጧቱ አንድ ሰዐት ከመሆኑ በፊት ቁርስ ተበልቶ አለቀና ሁላችንም ወደየተመደብንበት መኪና እንድንገባ ተነገረን። የሚጸዳዳዉ ተጸዳድቶ ሲጋራ የሚያጤሰዉም ሲጋራዉን ለምጦ ጉዞ ተጀመረ። ዬት እንደምንሄድ ወይም ለምን እንደምንሄድ የጠየቀም የተናገረም አልነበረም። . . . ዋ! ትንፍንሽ ብትሉ የተባለ ይመስል ሁሉም አፉን ዘግቶ ወደማያዉቀዉ ቦታ ጉዞዉን ቀጠለ። አንድ ሰዐት ያክል እንደተጓዝን . . . “እነዚያ ቤቶች ይታዩሃል” የሚል ድምጽ መኪናዉ ዉስጥ የሰፈነዉን የዝምታ ጽላሎት ሰበረዉ።አዎ ይታየኛል . . . ምን የምትባል ከተማ ናት ብዬ ቀና ስል ትልቅ ወንዝ አየሁ፤ ግን ወንዙንም ከተማዉንም ስለማላዉቃቸዉ ምንም አልተሰማኝም። እንድያዉም ፀሐይ ያጋለዉን ሰዉነቴን ለማቀዝቀዝ ወደ ወንዙ እንሂድ አልኳቸዉ። “ይቅርብህ እንደቀዘቀዝክ ትቀራለህ” አለኝ ከአጃቢያችን አንዱ።
ከተማዉ ኦምሀጀር፤ ወንዙ ተከዜ፤ ከወንዙ ባሻገር የሚታየዉ ከተማ ደግሞ ሁመራ መሆኑ ሲነገረኝ . . . የምን ወንዝ መዉረድ እዚያዉ ቀዝቅዤ ቀረሁ። አደራ ቦቅቧቃ እንዳትሉኝ . . . አልፈራሁም አልደነገጥኩም። በእርግጥ እንኳን እንደዚያ ቀርቤዉ ከሩቅ ከባህር ማዶም ጠልፎ ሊወስደኝ የሚፈልግ ሰላቢ የነገሰበትን ምድር ሳላዉቀዉ እንደዚያ በድንገት መቅረቤ ትንሽም ቢሆን አሳስቦኛል። ይልቅ እንደዚያ ያፈዘዘኝና ገና ወንዙ ዉስጥ ሳልገባ ያቀዘቀዘኝ እናት አገሬን ኢትዮጵያን በ25 አመት ለመጀመሪያ ግዜ ማየት መቻሌ ወይም የእናት ኢትዮጵያ ናፍቆት ነዉ። ለነገሩ አገርም ሰዉም የሚናፍቀዉ ርቀዉ ሲሄዱ ነዉ። ዬኔ ናፍቆት ግን ልዩ ጭራሽ ልዩ ነዉ። አጠገቧ ቆሜ አገሬ ናፈቀችኝ። አዎ! መግቢያዬ ቀረበ መሰለኝ ኢትዮጵያ ስቀርባት ይበልጥ ናፈቀችኝ።
በቃ አንሂድ አለ ይዞን የመጣዉ የበላይ መኮንን . . . አዎ እንሂድ እንጂ ከዚህ በላይ መቆየት ለወያኔ ካልሆነ ለሌላ ለማንም አይበጅም አሉ ሌላዉ በዕድሜ ጠና ያሉ የበላይ መኮንን። እኚህ ሰዉ የወያኔ ስም ሲነሳ ደማቸዉ ይፈላል ፤ እሳቸዉ እራሳቸዉ እንደ ዳዊት ሲደጋግሙት ግን ምንም አይሰማቸዉም። ከሰዐት በኋላ ረፋዱ ላይ ሁላችንም ወደየመኪናችን ገብተን ኦምሀጀርን ለቅቀን ወደ ጀግኖቹ አገር ወደ ሀሬና አቀናን። ሀሬና አርበኞች ግንቦት 7ን፤የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄን፤ የአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን፤ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ድርጅትንና ደምህትን ወላድ ማህፀንዋ ዉስጥ አምቃ የያዘች እርጉዝ ምድር ናት። እርግጠኛ ነኝ በቅርቡ ትወልዳለች።
የአስመራ ምፅዋ መንገድ እንደ ጥምጥም እየተጠመጠመ እየቀናና እየጠመመ ለረጂም ሰዐት የሚዘልቅ ያዋቂንም የልጅንም ቀልብ የሚሰልብ ሰላቢ መንገድ ነዉ። እግዚኦ . . . የከረን መንገድ በስንት መልኩ! ከአስመራ ምፅዋ መሄድ ማለት ከ2500 ሜትር ተራራ ላይ ቁልቁል ወርዶ ባህር ወለል መድረስ ማለት ነዉ። ትንፋሼን ቋጥሬ በቀኜ ገደሉን በግራዬ ተራራዉን እያየሁ ለሰዐታት ቁልቁለቱን ከተያያዝኩት በኋላ የቋጠርኩትን ትንፋሽ አዉጥቼ እፎይ ማለት የጀመርኩት ማይ አጣል ስደርስ ነዉ። ከማይ አጣል በኋላ ምፅዋ ድረስ መንገዱ ሜዳ ነዉ።
ምፅዋ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ሆዴን ባር ባር አለዉ። የደስታ ይሁን የሀዘን ወይም የሲቃ አላዉቅም ብቻ ልቤ ሌላ ሌላዉን ሰዉነቴን ትቶ ደረቴ ዉስጥ ብቻዉን ይዘላል። “ዉስጥ እጄን ይበላኛል” ምን ሊያሳየኝ ይሆን . . . ይል ነበር የልጅነት ጓደኛዬ። ምነዉ እኔም እንደሱ ሆኜ ዉስጥ እጄን በበላኝ . . . ልቤ ደረቴን ጥሶ የሚወጣ እሰኪመስል ድረስ ደረቴ ዉስጥ ከሚዘል። አይፎኔን አወጣሁና ግራና ቀኙን አይኔ ያረፈበትን ቦታ ሁሉ ፎቶ አነሳሁ። ቦታዉ ዶጋሌ ይባላል. . . አዎ! ዶጋሌ . . . ጀግናዉ ራስ አሉላ 500 የጣሊያን ወታደሮችን ዶጋ አመድ ያደረጉበት የድል ቦታ። ለካስ ልቤ አለምክንያት አልዘለለም! ጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ዉስጥ የአምስት መቶዎቹ አደባባይ የሚባል ቦታ አለ (ፒያዛ ዴ ቺንኮ ቼንቶ)። እመኑኝ እኛም አገር አይቀርም! ባንዳ ባንዳዉንና ልክ ልኩ ሲነገረዉ ደንግጦ የሞተዉን ምናምንቴ ሁሉ ትተን ሞተዉ ህይወት የሆኑልንን የትናንትናና የዛሬ ጀግኖቻችንን እናስታዉሳለን።
ምፅዋ ሁለት ቀን ብቻ ነዉ ያደርኩት – ቅዳሜና እሁድን። በጦርነቱ የፈራረሱ ህንጻዎች አሁንም አልፎ አልፎ ይታያሉ፤ ያም ሆኖ ምፅዋ ዉብ ከተማ ናት፤ ደግሞም አያሌ አዳዲስ ህንጻዎች ተሰርተዉባታል። የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጠ/መምሪያ የነበረዉ ማዕከል ግን በጦርነቱ እንደፈረሰ ነዉ፤ ያየዉም የነካዉም ያለ አይመስልም።
እሁድ ነኃሴ 16 ቀን ከምፅዋ ተነስተን 45 ደቂቃ ከነዳን በኋላ ዊሃ ደርስን። ዊሃ ሌላዉ የአርበኞች መንደር ነዉ። ዊሃ ያለዉ አርበኛ እንዴት እንደተቀበልን ለመግለጽ አማርኛ ቋንቋ እንደገና “ሀ” ብዬ መጀመር የሚኖርብኝ ይመስለኛል። በዚያ የወፍ ማረፊያ በሌለበትና በየሴኮንዱ ዉኃ ዉኃ በሚያሰኝበት ንዳድ ዉስጥ ወታደራዊ ሥልጠና መዉሰድ ቀርቶ አንድ ሜትር መራመድም እጅግ በጣም ይከብዳል። እንግዲህ ይታያችሁ የኛዎቹ ጀግኖች እንደዚህ የምድር ሲኦል በመሰለ ቦታ ነዉ ወገኖቻቸዉን ከወያኔ መንጋጋ ነፃ ለማዉጣት እልህ አስጨራሽ የሆነ ወታደራዊ ሥልጠና የሚወስዱት። እኔም የኢትዮጵያን ህዝብ ከወያኔ ዘረኞች ለማላቀቅ እንደወያኔ 17 አመት ጫካ ለጫካ መንፏቀቅ እንደሌለብን ቁልጭ ብሎ የታየኝ ዊሃ ሄጄ እነዚህን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ስመለከት ነዉ።
No comments:
Post a Comment