Thursday, August 13, 2015

የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመጨረሻ መጽሃፍ – መጽሃፍ ቅዱሱን ተነጠቀ!!

eskinder2ዳዊት ከበደ ወየሳ እንደዘገበው) ሃሳቡን በጽሁፍ ስላቀረበ “አሸባሪ” ተብሎ 18 አመት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ በእስር ቤት ውስጥ በከፍተኛ ጫና እየደረሰበት መሆኑ ተገለጸ። ምንም ነገር ማንበብም ሆነ መጻፍ ተከልክሏል። በአንድ ለሊት እስከሶስት ግዜ ክፍሉ እየመጡ፤ ከእንቅልፉ በመቀስቀስ ፍተሻ ያደርጉበታል።
ይህ ሁሉ የሚደረገው ደግሞ ከህግ እና ህገ መንግስቱ ተጻራሪ በሆነ መንገድ ነው። ለምሳሌ – በህገ መንግስቱ አንቀጽ 21 ላይ፤ “የህግ እስረኛ መብት ሊጠበቅ ይገባል።” ይላል። አንድ ታሳሪ ሰብአዊ ክብሩም መጠበቅ እንዳለበት ይዘረዝራል። ይህ ብቻ አይደለም። በዚሁ አንቀጽ ቁጥር 2 ላይ “ማንኛውም እስረኛ ከሚቀርበው ሰው ጋር መገናኘት ይችላል” ይልና መብቱን በዝርዝር ሲገለጽ- ከትዳር ጓደኛው፣ ከቅርብ ዘመዶች፣ ጓደኞች ከሃይማኖት አማካሪው፣ ከሃኪሙ እና ከህግ አማካሪው ጋር የመገናኘት መብት እንዳለው ብቻ ሳይሆን፤ ስለጾም እና ጸሎት ለመማከር ቢፈልግ የሃይማኖት አባት ማነጋገር እንደሚችል ተደንግጓል። በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ግን ራሳቸውን ከህገ መንግስቱ በላይ ያደረጉ የወህኒ ቤቱ አዛዦች ሰብአዊ መብቱን የሚጋፉ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ሲፈጽሙበት ቆይተዋል። ይህም በጨለማ ቤት ውስጥ ከማሰር ጀምሮ ቤተሰብ እና ጓደኞቹ እንዳይጠይቁት እስከማድረግ ድረስ ይዘልቃል። በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ገብረወልድ የተባለ ደህንነት በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ተመድቦበት፤ በቁም እንዲሰቃይ እያደረገው ነው። በቀን እና በለሊት በማንኛውም ግዜ ጋዜጠኛ እስክንድር ወደታሰረበት ክፍል በመግባት ያዋክበዋል፤ የሚጠቀምበትንም ቁሳቁስ ይወስድበታል። ለምሳሌ – እስረኞች እዚያው ከሚሰሩትና ገዝተው ከሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች መካከል እዚያው ግቢ ውስጥ የሚሰራው መቀመጫ አንዱ ነው። ይህን መቀመጫ ከጋዜጠኛ እስክንድር ክፍል ውስጥ ወስደውበታል። እንዲህ ያለ ተራ ተግባር ነው እየተፈጸመ ያለው። ከእስር ቤት አካባቢ የደረሰን መረጃ እንደሚያስረዳው፤ መቀመጫ ወንበሩን ከጋዜጠኛው ላይ ከወሰዱበት በኋላ፤ በእስር ክፍሉ ውስጥ የሚገኘውን ባልዲ ገልብጦ፤ እንደወንበር ይጠቀምበታል። “ይህን ዘገባ ሲመለከቱ ደግሞ፤ ይህቺኑ ባልዲ ሊወስዱበት ይችላሉ” ብለውናል ዘገባውን ያደረሱልን ግለሰቦች። ይህን እንደምሳሌ ገለጽን እንጂ፤ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ከዚህ በላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲደርስበት ነበር፤ አሁንም እየደረሰበት ነው። በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት መጽሃፍ ወይም ወረቀት እንዲኖረው አይፈቀድለትም። ባለፈው ሳምንት ክፍሉን የበረበረው ገብረወልድ ሲያስጠነቅቀው፤ “እስክሪብቶ እንኳን ይዘህ እንዳይህ አልፈልግም።” ሲል ነበር የዛተበት። ሌላው ቀርቶ እስክንድር ያነበው የነበረውን የመጨረሻ መጽሃፍ – መጽሃፍ ቅዱሱን ጭር ወስደውበታል። ይህን መጽሃፍ ቅዱስ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል የሰጠችው ነበር። ከምንም ነገር በላይ ግን ከአምላኩ ጋር የሚገናኝበት፤ በጸሎት ግዜ የማይለየውን መጽሃፍ ቅዱስ የወሰዱበት የጋዜጠኛውን ቅስም ጭምር ለመስበር ቢሆንም፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ግን አሁንም በመንፈሰ ጠንካራነት ከሚታወቁት እስረኞች መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ የአለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችን ትቀበላለች። ሆኖም በጋዜጠኛ እስክንድር ላይ የሚደርሰው ግፍ ግን የሰው ልጅ ሊሸከመው የሚከብድ ነው። ትላንት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን መብት መከበር ይቆረቆር እና ይጽፍ የነበረው ጋዜጠኛ ህክምና ጭምር ተከልክሎ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይቅርታ ጠይቆ እንዲወጣ ተጠይቆ ፈቃደኛ ባለመሆኑጥርስ ተነክሶበታል። እንደኢትዮጵያ አለም አቀፉን የሰብአዊ መብት አያያዝ የፈረሙ አገሮች የእስረኞችን ሰብአዊ ክብር ይጠብቃሉ። እስረኞች እንደየሃይማኖታቸው መጽሃፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርአን እንዳያነቡም ሆነ እንዳይኖራቸው አይከለከሉም፤ በኢትዮጵያ ግን እየሆነ ያለው ከዚህ በተቃራኒ ነው። (በዚህ አጋጣሚ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች – የጋዜጠኛው መጽሃፍ ቅዱስ እንዲመለስለት ጠቅላይ ሚንስትሩን እንዲጠይቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን) በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በታሰረበት ክፍል ውስጥ፤ እሱን ጨምሮ አምስት እስረኞች አሉ። ከነሱም ውስጥ “መንግስትን በሃይል ወይም በመፈንቅለ መንግስት ለመገልበጥ ሙከራ አድርጋችኋል” ተብለው ሞት የተፈረደባቸው ጌታቸው ብርሌ እና መላኩ ተፈራ፤ ከመኢዴፓ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) እና በከፍተኛ ሙስና የታሰረው የጉምሩኩ ገብረዋህድ አብረው ነው የታሰሩት። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከታሰረ በኋላ፤ ሃብት እና ንብረቱን – ገንዘብ እና ቤቱን ሳይቀር መንግስት አግዶበታል። የወላጆቹን ንብረት እንዳይሰበብ ሆኗል። በሚሊዮን ይቆጠር የነበረውን እና እናቱ በባንክ አካውንታቸው ያስቀመጡት ገንዘብ ከፍርድ ቤት እግድ ውጪ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል። እናቱ በህይወት በነበሩበት ወቅት፤ ክሊንካቸውን እንዲዘጉ ከተደረጉ በኋላ ንብረታቸውን አዘርፍታል። አራት ኪሎ የሚገኘው ቤታቸው ተወስዶባቸው ሆቴል ውስጥ ነበር የሚኖሩት። በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ፤ የእስር ብቻ ሳይሆን የግል መኖሪያ ቤቱ እና ንብረቱ ጭምር እግድ ወጥቶበታል። ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን ከሁለት አመት በፊት፤ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጠው፤ “እኛ ሁላችን እናልፋለን። ልጄ ናፍቆት እክንድር አድጎ፤ አንድ ቀን ንብረታችንን ያስመልሰዋል።” የሚል ምላሽ ለፍርድ ቤቱ መስጠቱ ይታወሳል። ከዚህ በታች ያወጣነው ለፍርድ ቤቱ የተጠየቀው የእግድ ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው፤ 1ኛ ንፋስ ስልክ ላፍቶ የሚገኘው G+2 መኖሪያ ቤት፤ ከእናቱ በውርስ ያገኘው የካ ወረዳ የሚገኘው ትልቅ ቪላ ቤት እንዲሁም ልጁን ናፍቆት እስክንድርን ትምህርት ቤት ያመላልሱበት የነበረው አቶዝ መኪና በባለቤቱ በወ/ሮ ሰርካለም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ደብዳቤው ገልጾ፤ በመንግስት እንዲወረስ ጥያቄ ቀርቧል። - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45838#sthash.JCh0S9yg.dpuf

No comments:

Post a Comment