ቀበሮና ኖርዌይ !
=========
=========
ዛሬ አንድ ዳግብላደ የተባለ የኖርዌይ ጋዜጣ ያወጣው ታሪክ አስደመመኝ ፡፡ ነገሩም ስላስገረመኝ ኖርዌጅያንኛ ለማይችሉ ወገኖቼ ባስነብባቸው ምን ያህል እኛና ምዕራባውያኑ በአንዲት ፕላኔት ላይ ብንኖርም ምን ያህል እንደተራራቅን ያሳያል የሚል እምነት ስላደረብኝ ነው ይህን ታሪክ ላቋድሳችሁ የፈለግሁት ፡፡
አምባገነን ገዥዎቻችን ሁልግዜ የሰው ልጅ መብት ነጻነትን በሚጠየቁበት ጊዜ « ዲሞክራሲ ሂደት ነው ! በሂደት እንሻሻላለን ይሏችኋል » እንደ ምዕራብውያኑ ሱፍ ልብስ ለብሰው ፥ ክራቫት አንጠልጥለው ፥ በውድ አውቶሞቢል በሞተረኛ ታጅበው መሄድን እና ያማረ ቤተመንግሥት ውስጥ መኖርን እንደስልጣኔ ከቆጠሩት ፣ ህዝባቸው ለሚጠይቃቸው ነጻነት ግን ዲሞክራሲ ሂደት ስለሆነ በሂደት ሁሉም ነገር ይሟላልሃል አሁን ግን ገና ነህ ማለት ምን እንደሆነ አይገባኝም ፡፡ መጀመርያ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር ዲሞክራሲው ማደግ የነበረበት ፡፡ ከዚያ ወደ ህዝብ ማውረዱ ይቀል ነበር ፡፡
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ላምራ ፡፡ ኧስት መርካ በሚባል አንድ ገጠራማ የኖርዌይ አውራጃ ውስጥ የቀበሮ መንጋ ፈልቶ ፣ የአካባቢውን በግ ፥ ውሻ እንዲሁም ህጻናትን ሁሉ ሳይቀር እየተተናኮለ ቢያስቸግር ፣ የአካባቢው ህዝብ አቤት እያለ ወደ መንግሥት ይጮሃል ፡፡ ያለ መንግሥት ፈቃድ ምንም ቀበሮው የአካባቢውን ህዝብ እየተተናኮለ ቢያስቸግር ንክች ማድረግ አይቻልም ፡፡ ጭራሽ ባለፈው ሳምንት የአውሬ መብትን አስከትሎ የአገሪቱ ቴሌቭዥን የአንድ ሰአት ስርጭትን ያካሂዳል ፡፡
ይህን ፊልም የተመለከተው የአካባቢው ህዝብ ግን ሞረሽ ጠራ ፡፡ በአንድ ጊዜ 120 ሰዎች ተሰባስበው በቴሌብዥኑ ድርጅት ላይ ክስ መሰረቱ ፡፡ ኧንደውም ተቃዋሚው ህዝብ እየተበራከተ በመምጣቱ የቴሌቭዥኑ ዋና የስራ ኃላፊ የመጣበትን ተቃውሞ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ማርች 5 ቀን በጉዳዩ ላይ ለመምከርና የህዝቡን አቤቱታ ፍጻሜ ለማድረስ ፣ የፊልሙን ዶክሜንተሪ አዘጋጅ ፥ እንዲሁም በንስሳ መብት ዙርያ ክህሎቱ ያላቸውን ምሁራኖች ፥ በቀበሮ ዝርያ ላይ ጥናት ያደረጉ ሳይንቲስቶችን ፥ እና ያካባቢውን ህዝብና በግ አርቢ ገበሬዎችን ያካተተ ምክክር ሊያደርግ ቀጠሮ ይዟል ፡፡
ወደ አገራችን አሰብኩ ፡፡ ጂሃዳዊ አራካትን ፥ አኬልዳማን ፥ በዞን ዘጠኝ ጦማርያን ላይ የተሠራውን ፊልም ፣ በስክንድር ፥ በሃብታሙ ፥ በአንዷለም ፥ በበቀለ ገርባ ፥ በሸዋነስ ወዘተ ላይ እነ ሽመልስ ከማልና ፥ ሬድዋን ሁሴን ያሠሩትንና ያስተላለፉትን ፊልም አስታወስኩ ፡፡ ዳኝነት በሌለበት ፥ እንደፈለጋቸው የሚነዱት ህዝቤ አሳዘነኝ ፡፡ ዲሞክራሲ ሂደት ነው የሚሉት ምጸትም የበለጠ እንድበግን አደረገኝ ፡፡ ዲሞክራሲና ስልጣኔ ገባን የሚሉት የቤተ መንግሥት ገዥዎቻችን መቸ ነው ለነርሱ የገባቸውን ዲሞክራሲ ወደ ህዝቡ የሚያወርዱት ? የሰው ልጅ ከሆንን ህግን እንደፈረንጁ የማንጠቀምበት ለምንድነው ? ይህ መመጻደቅ አይደለም ነጻ ተቋም ካለ በነጩ ዓለም የሰራው ህግ አፍሪካም ይሠራል ፡፡ ምን ይደንቃል ! ነጻ ነው በተባለ የምርጫ ቦርድ በቅርቡ የተወስደውን የህገ አራዊት ውሳኔ አይተን የለ ! ይቺ ዲሞክራሲ ሂደት ነው የምትል ምጸት ከጥቁሩ ህዝብ ላይ መች ይሆን የምትፋቀው ? የፈረንጅ ቀበሮ ያገኘውን መብት በአርያ ስላሴ የተፈጠረው ሰው መብቱን የተገፈፈባት ኢትዮጵያ እስከመቼ በዚህ ትቀጥል ይሆን ?
No comments:
Post a Comment