Saturday, February 28, 2015

የመስዋእትነት ትርጉም !አድዋ የእፍሪካ ድል 1888

የመስዋእትነት ትርጉም !
ጣይቱ , ምቾታችንን ትተን ለዚህ ሃገር መሞት ክብራችን ነው ስትል ... ምንሊክ የጣልያንን የጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውል አልቀበለም ብሎ ክተት ሲያውጅ ... ቀላል ውሳኔ አልነበረም ... ከዘመናዊው ወራሪ ጋር ጦርነት መግጠም ሃይሉን እንደሚያዳክመው , ስልጣኑንም አደጋ ላይ እንደሚጥልበት ሳያውቀው ቀርቶም አይደለም :: ግን በልቡ ስለ ኢትዮጵያ ጠንካራ እምነት ነበረው , በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ነበረው .. በሃገሩ ልጆች ጠንካራ እምነት ነበረው .. እነሱም ቀርተው አላሳፈሩትም .. በሃገር ጉዳይ ላይ አንድነት እንጂ ኩርፍያ አልነበረም ::
እንደ አንዳንድ ጥቁር ንጉሶች ሃገሩን ለጣልያን ተስማምቶ በእጅ አዙር እያስገዛ , እያስዘረፈ እኮ ..ንግስናው ሳይነካበት ተደላድሎ መኖር ይችል ነበር .. እንደዛም አይደለ እንዴ ብዙዎቹ ጥቁር አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በገዛ የጎሳ መሪዎቻቸው እና ንጉሶቻቸው የተከዱት?
ወስዋእትነት ምንድነው ? ሰዎች መስዋእትነት ሲከፍሉ , በልባቸው የሚይዙት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ አይደለም .. የራሳቸውን ምቾትም አይደለም :: መስዋእትነት ክቡርነቱ የሚገለፀው ከራሳቸው ከከፈሉትም በላይ ለሌሎችም ሲባል በመሆኑ ነው ::
ይህ ሃገር ብዙ መስዋእትነቶች እንደተከፈለበት ታሪክ ይነግረናል.. ከነዚህ ውስጥ ዓድዋ ለኔ ከፍ ከፍ ብሎ ይታየኛል :: አባቶቻችን ስለ ጎጣቸው ሳይሆን ስለሃገር ሲሉ .. በመካከላቸው የነበሩ የስልጣን ፉክክር እና ግጭቶች ሳይከፋፍላቸው .. ስለ ኢትዮጵያ ሲሉ ደማቸውን አፍሠዋል .. በባዶ እግራቸው .. ባልጠገበ ሆዳቸው .. እምቢ ብለው ከቅኝ ገዢ ተናንቀው ድል አድርገዋል !
አባቶቻቻን .. እነዛ ደማቸውን ለክብራችን ያፈሰሱ , ዘመናዊ ትጥቅ ሳይሆን ቆራጥ ልብ የታጠቁ አባቶቻችን እንዴት አይከበሩም ? .. እነሱ በከፈሉት መስዋእትነት ላይ ነው ዛሬ ከነማንነታችን የቆምነው ... አሁን እኛ ሃገሬ , ክልሌ እያልን የምንመፃደቅበትን የሰጡን እኮ እንሱ ተባብረው አብረው በመቆም አፅንተው ነው ::
አሁንም , ወደፊትም ምንም አይነት ችግር , ጭቆና ቢደርስብን የነሱ ጥፋት አይደለም:: ዛሬ አለብኝ ለምትለው ችግር ባወረሱን የነፃነት መንፈስ አንተ ደግሞ በተራህ መስዋእትነት ከፍለህ ነፃነትህን ያዛት .. በያዝከው ጥላቻና ወሬ ሳይሆን እንደነሱ በፍቅር እና ወኔ ተሞልተህ ለመጪው ትውልድ ምሳሌ የሚሆን ጀግንነት አሳይ እና ቤዛ ሁን !
የዛሬ ነፃነት ማጣትህ ተጠያቂው ... ራስህ ነህ ! ራስሽ ነሽ !
የባንዳ , የፈሪ እና ከሃዲ የልጅ ልጅም ከሆንክ , እሱ ከሆነም ልብህ የሚያውቀውን የጀግኖቹን አባቶቻችንን መስዋእትነት እንዳታከብር የተናነቀህ , አትጨነቅ ... ጀግኖቹ የሞቱት ለኛ ብቻ ሳይሆን ላንተም ለባንዳው የልጅ ልጅ ነው :: ዛሬ አንተ የነጭ ባርያ ከሆኑ , በማንነታቸው ከሚሳቀቁ በራስ መተማመናቸው የተሸረሸረ ቤተሰቦች የተገኘህ ማንንት ቢስ ከመሆን ታድገውሃል ..
ዛሬም አንተ አጣሁት የምትለውን ነፃነት .. ድጋሚ አባቶች ከሞት ተነስተው .. ድጋሚ መስዋእትነት ከፍለው ድጋሚ ሞተው እንዲሰጡህ ነው መሻትህ ? ታድያ ምንድነው ወቀሳህ ? .. ጀግኖችን አፍህን ከፍተህ መውቀስ ጀግንነት መስሎህ ነው ? ,, የነሱን የጀግንነት እና ቆራጥነት ሽርፍራፊ ያህል እንኳን በውስጥህ የሌለህ .. አንት ምስጋና ቢስ !
ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ !
የተሰጠን ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት !
ምስጋና ለነሱ ለዓድዋ ጀግኖች
ለዛሬ ነፃነት ላበቁን ወገኖች !
በኩራት , በክብር , በደስታ , በፍቅር
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን !

No comments:

Post a Comment