መንግስት ከ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ላይ እጁን ያንሳ
❖ ‹‹ … ሁለተኛው ዙር የእሬቻ በዓል ሥነ ሥርዐት በዝቋላ ተራራ እና በአከባቢው ይከበራል ፡፡›› – የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ
❖ ‹‹ … የእሬቻ በዓል በዝቋላ ገዳም እንደሚካሄድ በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም ፡፡ ›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
❖ ‹‹ …ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት በተገለጸበት የመንግሥት ብዙኃን መገናኛ ማረሚያ እንዲተላለፍ መደረግ አለበት ፡፡ ›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
❖ ‹‹ … ከጥንት ጀምሮ የዝቋላ ተራራ እና የጠበል ሐይቁ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ይዞታነት የታወቀ ነው ፡፡ ይህን እውነታ ወደ ጎን በመተውና የገዳሙን ሕጋዊ ባለቤትነት በመናቅ በማን አለብኝነት መንፈስ የተላለፈው ውሳኔ እኛንበእጅጉ አሳዝኖናል ፤ከፍተኛ የሆነ ሥጋትንም አጭሮብናል ፡፡ ›› ማኅበረ መነኮሳት
❖ ‹‹ … የእሬቻ በዓል በታሪካዊው ገዳም ላይ እንደሚካሄድ በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ በመተላለፉ በገዳማውያኑና በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዩች ዘንድ ቅሬታን አስከትሏል ፡፡ ›› ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
❖ ‹‹ … ይኽን ችግር በተደጋጋሚ ጊዜ ለቀድሞው ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና ለመንግሥት አካላት ያመለክትን ቢሆንም ለችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ እስከ አሁን ባለመሰጠቱ ለእንደዚህ ዐይነት ችግር ሊዳርገን ችሏል፡፡››ማኅበረ መነኮሳት
❖ ‹‹ … የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ግንቦት 23 ቀን 2004 ዓ.ምየገዳሙን አስተዳደር ደብረ ዘይት ድረስ ስብሰባ በመጥራት አስፈራርቷል ፡፡ ›› ማኅበረ መነኮሳት
❖ ‹‹ … ነገ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ ከአሁኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን ፡፡ ›› ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
❖ ‹‹ … እናንት እኛ ቦታ ድረስ መጣችሁ እንጂ እኛ እናንተ ጋር አልመጣንም ፤ሀገራችንን ለቃችሁ ውጡ ፤ገዳሙ የነፍጠኛ ሃይማኖት እንጂ ለኦሮሞው ምኑ ነው ? ቦታው የእኛው እስከሆነ ድረስ አይደለም ሐውልት ማቆም ውሻ እንሰዋበታለን ፡፡ ››
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ
❖ ‹‹ … የዞኑ መስተዳደር ተወካዩች እና የጸጥታ ቢሮ ሓላፊዎቸ በተገኙበት የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ሓላፊዎች ኢትዮጵያዊነታችንን እና ወንድማማችነታችንን በሚገድልና ጫና ባለበት ሁኔታ በገዳሙ ጠበል እና ታቦት ማክበሪያ ስፍራ ሐውልት እንደሚያቆሙ በዛቻ አሳውቀውናል ፡፡ ›› ማኅበረ መነኮሳት
❖ ‹‹ …ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነት ሲሉ ለብዙ ዓመታት የተጋደሉበት ቦታ ፣ ስማቸውና ታሪካቸው ተሸሮ ሌላ ሐውልት ሲተከል በዝምታ ለማየት አቅሙ የለንም ፡፡ … ገዳማችን ታፍሮና ተከብሮ ለእኛም ለማኅበረ መነኮሳቱም አስተማማኝ የሆነ ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ እንዲደረግልን እንጠይቃለን ፡፡ ››
ማኅበረ መነኮሳት
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ከክልሉ የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ጋራ በመቀናጀት በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የጠበል ስፍራ ከሕግ አግባብ ውጭ ‹‹ መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም የበዓለ እሬቻን እና የሐውልት ተከላ ሥነ ሥርዐት አከናውናለሁ›› ማለቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ፣ ከምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ፣ ከገዳሙ አስተዳደር ጽ/ቤት ፣ ከማኅበረ መነኮሳቱና ከምእመናን ተቃውሞ ገጠመው ፡፡
በአድራሻ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳደር ለአቶ ሙክታር ከድር በቁጥር 151/370/2007 ፣በቀን 25/5/2007 ዓ.ም ተጽፎ፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፤ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በኢትዮጵያ ካሉት ጥንታውያንና ታሪካውያን ገዳማት አንዱ መሆኑን አውስቶ፤ሕገ መንግሥቱን በመተላለፍ እና አዎንታዊ የሴኩላሪዝም መርሕን በመደፍጠጥ፣ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውና በትምህርታቸው ለሀገርና ለወገን ስላማዊ መረጋጋትን እያስገኙ ያሉ መነኮሳትና በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝበ ክርስቲያኖችን ለማስቆጣት፤ የእሬቻን በዓል ሥነ ሥርዐት በዝቋላ ገዳም እንደሚካሄድ የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ የሰጡትን መግለጫ ተቃውሟል ፡፡
በታላቁ በዝቋላ ገዳም‹‹የእሬቻን በዓልን አከብራለሁ›› ተብሎ የተሰጠው መግለጫ ተገቢ አለመሆኑን የገለጠው የቅዱስነታቸው ደብዳቤ፤ ‹‹ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት በተገለጸበት የመንግሥት ብዙኃን መገናኛ ማረሚያ እንዲያስደርጉ›› ሲል የክልሉ ርእሰ መስተዳደር የሆኑትን አቶ ሙክታር ከድርን አሳስቧል ፡፡
ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደብዳቤ መነሻ የሆነውና በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፤ ቤተ ክርስቲናችን ያሏትን ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ጠብቃና የማንንም መብትና ድንበር ሳትነካ ላለንበት ዘመን መድረሷ ታሪክ የሚዘክረው መኾኑን ያስታውስና ከአሉን ታላላቅ ጥንታውያንና ታሪካውያን ገዳማት አንዱ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መሆኑን ያስረዳል፡፡ባለንበት በዚህ ዘመን መንግሥት የሃይማኖቶች እኩልነትን ያወጀበት በመሆኑ አንዱ ቤተ እምነት የአንዱን መብት የማይነካበትመሆኑ ግልጽ ነው፤ የሚለው የብፁዕነታቸው ደብዳቤ፤ ‹‹ ነገር ግን ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት እያለ ለዘመናት ቤተ ክርስቲያናችን በይዞታነት ይዛ መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠችበት በምትገኘበት በዚህ ታሪካዊ ገዳም ይዞታ ላይ የእሬቻ በዓል ሥነ ሥርዐት እንደሚካሄድ በመንግሥት ብዙኃን መገናኛ በመተላለፉ በገዳማውያኑና በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ዘንድ ቅሬታ አስከትሏል›› ይላል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ከክልሉ የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ጋራ በመቀናጀት በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እያደረሰ ያለው ጥፋት ተባብሶ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግም ያሳስባል ፡፡
በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ የተጋረጠው ታሪካዊ እና ይዞታዊ ቁመናን ጠብቆ የመዝለቅ የህልውና አደጋ፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ጋራ በመሆን የእሬቻን በዓል በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አከብራለሁ፤ ብሎ ከተነሣበት ጊዜ እንደሚዘልቅ የሚገልጹት ማኅበረ መነኮሳት፤ በዋናነት ጫናው ከመጋቢት 30 ቀን 2002 ዓ.ም ይጀምራል፤ ብለዋል ፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አጋፋሪነት የክልሉ የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ሓላፊዎች ነን ባዮች ገዳማችን ድረስ በመምጣት፤‹‹ በጠበሉ አከባቢ የገዳ ሥርዐትን የሚዘክር ሐውልት እናቆማለን፤የእሬቻ ሥነ ሥርዐታችንን እናከናውናለን ፡፡›› በማለት ችግር ፈጥረውባቸው እንደነበረም ያስረዳሉ፡፡ ማኅበረ መነኮሳቱም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሲሉ መንፈሳዊ ትኅትናን በተላበሰ ሁኔታ ራሳቸውን ጥፋተኛ አድርገው በማቅረብና ለአባ ገዳዎቹ ካሣ በመክፈል ዕርቅ ቢያወርዱም ችግሩ እስከ አሁን ድረስ ሊፈታ አለመቻሉን ይገልጻሉ ፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ሓላፊዎች በተደጋጋሚ እያስጠሯቸው፤‹‹ … እናንተ እኛ ቦታ ድረስ መጣችኹሁ እንጂ እኛ እናንተ ጋር አልመጣንም፤ሀገራችንን ለቃችሁ ውጡ ፤ገዳሙ የነፍጠኛ ሃይማኖት እንጂ ለኦሮሞው ምኑ ነው ? ቦታው የእኛው እስከሆነ ድረስ አይደለም ሐውልት ማቆም ውሻ እንሰዋበታለን፡፡››እንዳሏቸውም በሐዘን ያስረዳሉ፡፡ የገዳሙ መነኮሳት በቁጥር ዝ/ገ/135/04፣በቀን 28/9/2004 ዓ.ም ለምሥራቅ ሸዋ ዞን መስተዳድር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤም፤ ‹‹ግንቦት 23 ቀን 2004 ዓ.ም በደብረ ዘይት ከተማ በተጠራ ስብሰባ የዞኑ መስተዳደር ተወካዩች እና የጸጥታ ቢሮ ሓላፊዎች በተገኙበት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና የገዳ ሥርዐት ጽ/ቤት ሓላፊዎች ኢትዮጵያዊነታችንና ወንድማማችነታችንን በሚገድልና ጫና ባለበት ሁኔታ በገዳሙ የጠበል እና ታቦት ማክበሪያ ስፍራ ሐውልት እንደሚያቆሙ በዛቻ አሳውቀውናል›› ብለዋል፡፡እንዲህ ዓይነቱን ሕገ ወጥ ድርጊትም፤ ‹‹ታሪክን ሽሮ አዲስ ታሪክ የመትከል ቅዥት›› ብለውታል ፡፡
የዝቋላ ደብረ ክዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ማኅበረ መነኮሳት በቁጥር ዝ/ገ/019/07፣በቀን 21/01/2007 ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በጻፉት ደብዳቤ እንደተመለከተው፤የዝቋላ ተራራ እና የጠበል ሐይቁ ከዛሬ 877 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታነት የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁንና ይህን እውነታ ወደ ጎን በመተውና የገዳሙን ሕጋዊ ባለቤትነት በመናቅ በማን አለብኝነት መንፈስ የተላለፈው ውሳኔ በእጅጉ እንደአሳዘናቸውና ከፍተኛ የሆነ ሥጋትንም እንደአጫረባቸው አትተዋል ፡፡
በዚሁ ደብዳቤ ላይ በዕለተ አርብ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል የጌታን ደም የቀላቀለበት፣ ልዑል እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ብርሃነ ረድኤቱን የሚገልጥበት፣አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለሀገር ሰላምና ደኅንነት ለ262 ዓመታት የጸለዩበት፣ በየጊዜው ሕሙማን ጠበሉን በመጠጣትና በመጠመቅ የሚፈወሱበት፣ የጻድቁ አባታችን ታቦት ከመንበረ ክብሩ ወጥቶና ተፈጥሯዊ የጠበል ሐይቁን ዑደት በማድረግ የሚከብርበት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅዱስ ቦታ መሆኑን የገለጹት ማኅበረ መነኮሳቱ፤ ‹‹አርባ ሚሊዩን ኦርቶዶክሳውያን ሥርዐተ አምልኳቸውን የሚፈጽሙበትን የቤተ ክርስቲያን አንጡራ ሀብት በጉልበት ለመንጠቅ ታስቦ ያለአግባብ የተላለፈው ውሳኔ ጨርሶ ተቀባይነት የለውም፡፡››ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህን ችግር በተደጋጋሚ ጊዜ ለቀድሞው ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና በየደረጃው ላሉት የመንግሥት አካላት ማመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ሆኖም ለችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ እስከ አሁን ድረስ አልተገኘም፡፡ በዚህም የተነሣ አሁን የተከሠተው ችግር እንደደረሰ በደብዳቤያቸው አስገንዝበዋል፡፡ ገዳማውያኑ በቁጥር ዝ/ገ/153/04፣በቀን 28/9/2007 ዓ.ም በአድራሻ ለምሥራቅ ሸዋ ዞን መስተዳደር ጽ/ቤት በጻፉት ድብዳቤም፤ ‹‹የዞኑ አስተዳደር ይህን ችግር በአፅንዖት ተመልክቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ እንዲሰጥበት እና ምእመኑም ኢትዮጵያዊነቱን የሚያፈቅርበትና እምነቱን በነጻነት የሚያካሂድበትን መንገድ እንድታስተካክሉልን ስንል በአክብሮትና በትሕትና እናሳስባለን፡፡›› በማለት መማጸናቸውንም አስታውሰዋል ፡፡
ለዞኑ ባለሥልጣናት በደብዳቤያቸው፤ ‹‹ይህን ገዳም በእምነት ተቋምነቱ ታሪኩን፣ ይዞታውንና ቅርሱን ጠብቀንና አቆይተን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የምንተጋ ጠባቂ መናኒያን እንጂ በቅዱሱ ቦታችን ላይ ከቦታው ቅድስና ጋር አብሮ የማይሄድ ሌላ ባሕል ወይም እምነት ይሁን ብለን ለመደራደር ሥልጣኑም አቅሙም የለንም፤››ያሉት ገዳማውያኑ፤ የቦታውና የታሪኩ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነም አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነት ሲሉ ከ262 ዓመታት በላይ የተጋደሉበት ቦታ፣ ስማቸውና ታሪካቸው ተሽሮ ሌላ ሐውልት ሲተከል በዝምታ ለማየት አቅሙ የለንም የሚሉት ማኅበረ መነኮሳቱ፤ ‹‹ ገዳማችን ታፍሮና ተከብሮ ለእኛም ለማኅበረ መነኮሳቱም አስተማማኝ የሆነ ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ እንዲደረግልን እንጠይቃለን›› ሲሉ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላትን ጠይቀዋል፡፡
ተፈጥሮ የለገሰን በርካታ ሀብቶች ፣ከአያቶቻችንና ከቅደመ አያቶቻችን የውስናቸው የሃይማኖታዊ ፣ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በተለያ መመዘኛዎች የላቀ ብሔራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ጠቀሚታ ካላቸው ብሔራዊ ቅርሶቻችንና የቱሪስት መዳረሻዎቻችን ውሰጥ አንዱ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ነው ፡፡ ገዳሙም ከኦሮሞ መስፋፋት400 ዓመታት በፊት ተገድሞ ከ877 ዓመታት ዕድሜ በላይ ያስቆጠረ፣ከ290 በላይ በሚሆኑ የዕፅዋትና የሣር ዝርያዎች የተሸፈነ፣ከ30 በላይ የሚሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎችና ጉሬዛ፣ ሰስ፣አነር፣ ሚዳቋና ዝንጀሮ የሚገኙበት ታላቅ ገዳም ነው፡፡
ይሁንና ለክልሉ ቅርስና ቱሪዝም ልማት ተገቢው ትኩረት መስጠት፣ ለዚህም መሪ ዕቅድና መርሐ ግብር መቀየስ፣በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ያሉትን ብሔራዊ ቅርስ የሚገኙባቸውን የቱሪስት መዳረሻዎች (Tourist Destinations) በቅደም ተከተልና ዓለም ዐቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ የሚለሙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚገባው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፤ በብሔርተኝነት መንፈስ ብሔር ዘለል የሆነውን ብሔራዊ ቅርስ ማጥቃቱ እያስተቸው ይገኛል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ርእዮተ ዓለማዊ እና ፖለቲካዊ ጥላቻ ባደረበት ጠባብ አመለካከት ተጽዕኖ ሥር ወድቆ እንጂ፤ እንደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማ ያለ ቅርስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሚታዎች ያሉት፤አብዛኛውን ጊዜ መተኪያ የማይገኝለት፣በይዘቱ፣በዓይነቱ ስፋትና ጥልቀት ያለው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት እንደሆነ መገንዘብ ተስኖት ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የብሔራዊ ቅርሳችን አስደናቂነትና አስደማሚነት የባዕድ አገር ተመራማሪዎች በጥናት ወረቀቶቻቸው እንደሚከተለው አስፍረዋል ፡፡
ጂነር የተባለው ዕውቅ ተመራማሪ እ.ኤ.አ.በ1991 ‹‹ Sacred Volcano Lakes:-Reflections Comparing Zeqwala and Nemi>>በተባለው የጥናት ወረቀቱ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከመንፈሳዊ ጠቀሚታው በተጨማሪ፤ መልክኣ ምድራዊ አቀማመጡና ኅብራዊ ባሕላዊ እሴቱ ከፍተኛ መሆኑን፤ ‹‹ ሰፊ የሆነውን የማኅበረሰብ ክፍል የሚወክሉ ምእመናን ገና ከዋዜማው በዓሉን ለመታደም መጥተው ነበር፤ አብኛዎቹ ከአዲስ አበባና ከአጎራባች ከተሞች ነበሩ፤ በአከባቢው የሚኖሩ የገጠር ነዋሪዎችም ነበሩ ፡፡ ከቢሾፍቱ፣አዳማና አርሲ አካባቢ የመጡ አርሶ አደሮች በሚያምር ቀለም ይታዩ ነበር፡፡በክብረ በዓሉ ላይ የእስልምና እና የባሕላዊ እምነት ተከታዩችም ተገኘተው ነበር፡፡ … ምእመናኑን ጭነው የሚያመላልሱት ተሸከርካሪዎች ከቢሾፍቱ ጀምሮ እስከ ዝቋላ ተራራ መዳረሻ ድረስ ያለውን የጥርጊያ መንገድ አቋርጠውና አዋራውን እያጨሱ ሲሽከረከሩ ማየት ድባብ የሚሰጥ ነበር›› ሲል ገልጧል ፡፡በዚሁ የጥናት ወረቀቱ ላይ፤‹‹ዝቋላን በጽሞናና በአንክሮ ስመለከታት በእሳተ ጎሞራ የተፈጥሮ ሐይቅ ተከባ በዓለ ቅዱሳን የሚከበርባትንና በደቡብ ሮም የምትገኘውን (የእኛኑ) አሚ በምትባል ስም የምትታወቀውን ቅዱስ ስፍራ ታሰታውሰኛለች›› ሲል የበዓሉን ዓለም አቀፋዊ ባሕርይም አስረድቷል ፡፡
ምንም እንኳን ይህ የተቀደሰ ቦታ የቱሪስት መዳረሻነቱ ተዘንግቶ፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የጥቃት ሰለባ ቢሆንም፤ በውስጡ በያዘው ሀብት ለአገሪቱ የብዝኃ ሕይወት እና የቱሪዝም ዕድገት የራሱን በጎ አስተዋጽዖ እያበረከተ የሚገኝ ትኩረትና ክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ ቅርስና ብሔራዊ ሃብት ለመሆኑ፤ሕገ መንግሥታዊ መብትና ጥበቃ የተሰጣቸው የሃገሪቱ ዜጎች የሚያምኑበት፤ ዓለም አቀፍ ምሁራንና ተመራማሪዎችም የሚመሰክሩለት ታላቅ ቦታ ነው፡፡
በመሆኑም በቦታው ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ከመባባሱ በፊት ቤተ ክህነቱም ሆነ ቤተ መንግሥቱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው፤ በተለይ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና የገዳ ሥርዓት ጽ/ቤት ሓላፊዎች የሚደርስበትን ጥቃት ሊያስታግሱልን ይገባል፤ የሚለው የገዳሙ አስተዳደር ጽ/ቤት ተማጽኖ፤ ‹‹ ይህ ታላቅ ገዳም በገዳሙ ውስጥ ያሉት የአበው መነኮሳት እና እማት መነኮሳይያት ብቻ ሳይሆን የአርባ ሚሊዮን ኦርቶዶክሳውያን እና የሀገር ሀብትና ንብረት ነው፡፡ይህንንም በመገንዘብ ምእመኑ አባቶቹ የሰጡትን አክሊል ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ ይገባል›› ሲሉ ገዳማውያኑ በደብዳቤያቸው ተማጽኖአቸውን አሰምተዋል ፡፡
No comments:
Post a Comment