በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከሰራተኞች ጋር የተካሄደ ስብሰባ ያለስምምነት ተጠናቀቀ
በስብሰባው የተካፈሉ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት፤ላለፉት ሁለት ቀናት ከኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ጋር በተደረገው ስብሰባ ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ጥቅመኝነት ፣ብሄራዊ ጥቅምን አሳልፎ መስጠት እና ሴኩሪቲ ክሊራንስ የሚሉ አጀንዳዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ቢሆንም፣ ስምምነት ሳይደረስባቸው ቀርቷል።
የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ አመራራሮች ሰራተኛውን፦ መረጃ ወደ ውጭ አውጥታችሁ ትሰጣላችሁ፣ የሜቴክ ማለትም የኮርፖሬሽኑ እቃ አይረባም እያላችሁ ታወራላችሁ፣ ደሞዛችን ትንሽ ነው እያላችሁ ታሳድማላችሁ በማለት ለማስፈራራት መሞከራቸውን አመልክተዋል።
<<ሜቴክ የውሸት ድርጅት ነው እያላቹ በስፋት ስለምታስወሩም ሰራተኛ በብዛት እየለቀቀብን ነው>>ያሉት የኮርፖሬሽኑ ሀላፊዎች፤ <<በወሬ እየተዳከምን ስለሆነ ፕሮጀክቶችን መጨረስ አልቻልንም >>በማለት አማርረው ተናግረዋል።
በሰብሰባው ላይ የተሳተፉ ሰራተኞች ከፍተኛ ቅሬታ ማንሳታቸውን የጠቆሙት ምንጮቹ፤ ከተሰነዘሩት ጥያቄዎች መካከል የደመወዝ ስኬል ማነስ፣ የአስተዳደር መበላሸትና ለረዥም ጊዜ የደመወዝ ጭማሪ ያለመኖር የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።
አመራሮቹ ሰራተኞቹ ላቀረቡት ጥያቄበቂ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ስብሰባው ያለመተማመን መጠናቀቁን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ከስብሰባው በሁዋላ ሃላፊዎች ለሚቀርቡዋቸው ሰራተኞች- በሃገር ውስጥ ከፍተኛ የምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙ- ኤልሲ ከፍቶ እቃዎችን እምጥቶ መሸጥ እንዳለተቻለ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በጄ/ል ክንፈ ዳኘው የሚመራ ሲሆን አብዛኞቹ የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ባለስልጣናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ለሚገነቡዋቸው ህንጻዎች እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ ለማስገባት እንደ ሽፋን ያገለግላል።
No comments:
Post a Comment