ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የመንግስትን መልካም ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊደርጉ ይችላሉ በሚል ተከታታይ ስልጠና ተሰጥቷቸው የነበሩት የህዝብ ግንኑነት ባለሙያዎች (ኮምኒኬተሮች) እና የመንግስት ባለስልጣናት፤የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም መባላቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖ ጠቆሙ፡፡
ለመንግስት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ለካድሬዎች በአቶ ሬድዋን ሁሴን በሚመራው የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት አማካይነት ከአራት ወር በፊት በማህበራዊ ድረገጾች አጠቃቀምና በመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ተከታታይ ስልጠና መሰጠቱ ይታወቃል።
ሰልጣኞቹ ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የመንግስትን አዎንታዊ ሚና አጉልተው በመጫወት የገጽታ ግንባታ ሥራ እንዲያከናውኑ የተሰማሩ ቢሆንም፤ እንደታሰበው ውጤት ሊያስገኙ አለመቻላቸው ተመልክቷል።
ጉዳዩን በቅርበት የኒያውቁ አካላት እንደሚሉት፦
ውጤት ላለመገኘቱ ዋነኛው ምክንያት ብዙዎቹ “ኮምኒኬተሮች” በአቶ በረከት ስምኦን የሚኒስትርነት ዘመን ከየክልሉ በፖለቲካ ብቃት ብቻ ተመልምለው፣ በለብለብ ሥልጠና ወደሕዝብ ግንኙነት ሙያ የገቡከ መሆናቸው አኳያ ከፍተኛ የአቅም ችግር ስላለባቸው ነው።
ቀሪዎቹም በቤት አሰጣጥ፣ በደመወዝ ጭማሪና እና በመሳሰሉት ጉዳዮች በሚስተዋሉ አድሎአዊ የጥቅማጥቅም አሰጣጥ ያኮረፉ መሆናቸው ተገልጿል።
<<ኮምኒኬተሮቹ>> ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በየመስሪያ ቤቱ ሲመደቡ ፤ ቀደም ሲል በየመስሪያ ቤቶቹ ከነበሩ ብቃት ካላቸው የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች አንዳንዶቹ ከቦታቸው እንዲነሱ ሲደረግ ፤የተቀሩት በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
አብዛኛዎቹ<<ኮምኒኬተሮች>> ከተሰጣቸው ሥልጠና በሁዋላ እንደፌስቡክ ባሉ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የራሳቸውን ወይንምየድርጅታቸውን አካውንት ለመክፈት ሙከራ ከማድረግ በዘለለ ምንም ማከናወን ሳይችሉ መቅረታቸው፤ የአቶ ሬድዋንን ቢሮ ማበሳጨቱ ተጠቁሟል፡፡
በተለይ በፌስቡክ የሚሳተፈውን ዲያስፖራ እና የተቃውሞ ሃይሉን በአንድ ላይ በመጨፍለቅ «አክራሪ ሃይሎች» በሚል የፈረጀው ኢህአዴግ ፤ይህን ሃይል ቢቻል ጸጥ ለማሰኘት ካሰማራቸው ስልጣኞች ባሻገር ከ25 በላይ የሚሆኑ ሚኒስትሮች ሳ ማህበራዊ ድረገጾችንእንዲጠቀሙ ሲወተውት ቆይቷል።
ይሁንና እስካሁን በግልጽ የራሳቸው አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው አኳያ ለኢህአዴግ እንቅፋት የሆነውን ሃይል የሚገዳደሩ አለመሆናቸው ቢሮውንና ኢህአዴግን እንዳሳሰበው ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
No comments:
Post a Comment