Friday, February 6, 2015

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) http://www.goolgule.com/light-rail-and-its-future/

ባቡር

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
http://www.goolgule.com/light-rail-and-its-future/
ትናንትና (እሁድ) የከተማ መለስተኛ የባቡር መጓጓዣ አገልግሎት ተጠናቆ ለአገልግሎት ተመረቀ፡፡ አሄሄሄ! ውስጡን ለቄስ! አሉ፡፡ ይሄ የባቡር ሥራ ብቻ ሳይሆን በወያኔ እጅ የሚሠራ ሥራ ሁሉ ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛና አሳሳቢ የጥራት ችግር እንዳለባቸው በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ቢሊዮኖች ዶላር (ብልፎች ዶላር) ልብ በሉ ቢሊዮን (ብልፍ) ነው ያልኩት ሚሊየን (አእላፋት) አይደለም ፈሶበት ቴሌ ላይ የተሠራውን ሥራ እና ውጤቱን ዐይተናል፣ መብራት ኃይል ላይም አሁንም እንዲሁ በቢሊዮኖች (ብልፎች) ዶላር ወቶበት ከህንድ እንዲገባ ያደረጉት ትራንስፎርመር (ማስተላለፊያ) በሙስና ምክንያት ከጥራት ደረጃ በታች እንዲሠራ የተደረገ በመሆኑ በተገጠመ ቁጥር እየተቃጠለ ምን ዓይነት ችግር ላይ እንዳለን ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡ በዚህ በባቡር ሥራው ላይም የጅብነታቸው ጅብነት የሸክላ ሀዲድ ዘርግተው ገደል እየከተቱ ሊጨርሱን ከማለቁ በፊት የበሉትን ገንዘብ ሲከፋፈሉ ቅር ያለው ነበር መሰለኝ አንዱ የዘረጉት ሀዲድ የሸክላ ሀዲድ መሆኑን በማጋለጡ እንደገና እያነሡ አሁን በትክክለኛው የብረት ሀዲድ ቀየርን፤ ይሄንን ያደረጉትንም አባረርን አሉ፡፡ ሲሉ ሰማን እንጅ በትክክልም የሸክላው ሀዲድ ተነሥቶ በትክክለኛው የብረት ሀዲድ ስለመቀየሩ ያረጋገጥነው ነገር የለም፡፡ መቸስ ሰው አስቀርበው?
እነዚህ ሥራዎች የሚወጣባቸው በብድርና በእርዳታ የተገኘ ገንዘብ ዓለማቀፋዊ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሊያሠራ የሚያስችል ቢሆንም ከሙሰኞቻችን ባለሥልጣናት ጅብነት የተነሣ 10 በመቶውን እንኳን እንዲሠራበት ስለማይፈቅዱ እንዲህ እንዲህ ዓይነቶች ከባባድ የጥራት ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ባጠቃላይ በዚህ አገዛዝ የሚሠራ ሥራ ሁሉ ወይ ገንዘቡ አልዳነ ባለ ዕዳ ሆነን ወይ ብድሩ መጥቶም ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ተሠርቶበት ተጠቃሚ የማንሆንበት ሁኔታ ስለ ሆነ ያለው ነገር በዚህ የገማ አገዛዝ እጅ ምንም ነገር ባይሠራ ሽ ጊዜ ተመራጭ ነው፡፡ እስኪ አስቡት ለእነኝህ የማይረቡ ብላሽ ቆልኮሌ ሥራዎች ሀገሪቱ በትውልደ ትውልድ ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ ውስጥ እየሰጠመች እኮ ነው!
እንግዲህ ያው በሸክላ ሀዲድ እየተጓዝን ለማለቅ እንኳን አደረሰን ልበል ይሆን? ባለሥልጣኖቻችንም በዚህ ስንት ጉድ በታየበት የባቡር ሥራ ምረቃ ላይ “ቢያንስ በአዲስነቱ ምንም አይል” ብለው ነው መሰለኝ በድፍረት ሲጓዙበት ሳይ በጣም ነበር የገረሙኝ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment