የአሜሪካና የብሪታኒያ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ የተደረጉና በአውሮፕላን ውድድር ላይ የነበሩ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች እንዲለቀቁ ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ሃሙስ አስታወቁ።
የተለያዩ ሃገራት ዜግነት ያላቸው እነዚሁ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ፓይለቶች አፍሪካን በሚሸፍን የአውሮፕላን ውድድር ላይ የነበሩ አዘጋጆች ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የውድድሩ አዘጋጆች ረቡዕ አንድ ብሪታኒያዊ ፓይለት ከሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል በመጓዝ ላይ እንዳለ ደብዛው መጥፋቱን አስታውቆ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ይሁንና ቪንቴጅ ኤይር ራሊ የተሰኘው የውድድሩ አዘጋጅ አስር የአፍሪካ ሃገራትን በሚሸፍን ጉዞ ላይ የነበሩ ሁሉም የፓይለቶች ቡድን በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል አርፈው ከክልሉ እንዳይወጡ መደረጉን እንደገለጸ ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በበኩሉ 20 ቀላል የሲቪል አውሮፕላኖች ከሱዳን ተነስተው የኢትዮጵያ ድንበርን አቋርጠው መግባታቸውን አረጋግጠዋል።
ፓይለቶቹ በአሁኑ ወቅት ማንነታቸውና ድንበር የመጣሳቸው ምክንያት እየተጣራ ነው ሲል ባለስልጣኑ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የፓይለቶቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር እየተወያየ መሆኑን እንዳስታወቀ አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ከጋምቤላ ክልል እንዳይወጡ ተደርገዋል የተባሉት የፓይለቶች ቁጥር ይፋ ያልተደረገ ሲሆን የአሜሪካ፣ የብሪታኒያ፣ አየርላንድና የሌሎች ሃገራት ዜጎች በቡድኑ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።
10 የአፍሪካ ሃገራትን በሚሸፍነው የአውሮፕላን በረራ ውድድር ላይ የነበሩት ፓይለቶች፣ ከግሪክ መነሻቸውን አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ የማቅናት ዕቅድ እንደነበራቸው አዘጋጆቹ ይገልጻሉ።
የፓይለቶቹ ቡድን በጋምቤላ ክልል በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ የግል ኮምፒውተሮቻቸውን ጨምሮ የእጅ ስልኮቻቸው በጸጥታ ሃይሎች እንደተወሰደባቸው አዘጋጆቹ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በበረራ ውድድር ላይ ከነበሩት ሲቪል አውሮፕላን በተጨማሪ ሁለት ሄሊኮፕተሮች እና ስድስት ዘመናዊ አውሮፕላኖች የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመያዝ አብረው ይጓዙ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና እነዚህ ድጋፍ ሰጪ ሄሊኮፕተሮችና አውሮፕላኖች በጋምቤላ ክልል ይሁኑ አይሁኑ የታወቀ ነገር የለም።
No comments:
Post a Comment