ኅዳር ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :aa ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ሰፊ ንግግር፣ ሁሉም የንቅናቄው አባል ድርጅቶች ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉአላዊ አገር የሚቀበሉ መሆናቸውን እና ችግሮቻቸውን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት እንዳለበት ስምምነት ላይ የደረሱ በመሆኑ ተቀራርበው ለመስራት ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
አገራዊ ንቅናቄው የድርጅቶች እንጅ የብሄር ውክልና የለውም ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ ፣ ማናችንም ቢሆን ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የህዝብ ውክልና ባልያዝንበት ሁኔታ የብሄሮችን ውክልና ታሳቢ ያደረገ ጥምረት ልንፈጥር አንችልም ብለዋል። ማንኛውም ድርጅት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከተቀበለና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት ፈቃደኛ ከሆነ በጥምረቱ ውስጥ ገብቶ መስራት እንደሚችሉ ፕሮፌሰሩ በዝርዝር አስረድተዋል። አቶ ሌንጮ በበኩላቸው ለብቻ የሚደረገው ትግል የትም እንደማያደርስ የ25 አመታት ጉዞ ምስክር ነው ብለዋል። ምዕራባውያንም ቢሆኑ ፍላጎታቸው እንድንሰባሰብ ነው ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ይህ ጥምረት ረጅም ርቀት ይሄዳል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ደግሞ “ የአፋር ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ነው “ ያሉ ሲሆን፣ በብሄር ለመደራጀት የፈለጉት አካባቢያቸው ትኩረት እንዲያገኝ እንጅ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ስትመሰረት የብሄር ፖለቲካው ያከትማል ብለዋል። ከኖርዌይ ለስብሰባ ስዊድን የተገኘው አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ ለውድድር ለብሶት የነበረውን የአንዳርጋቸው ጽጌ ምስል የያዘ ቲሸርትና የተሸለመውን ዋንጫ ለንቅናቄው አበርክቷል። በዝግጅቱም ከፍተኛ ገቢ መገኘቱን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment