የኢትዮጵያ መንግስት ሳኡዲ አረቢያን መማጸኑ ተነገረ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ቡድን እሁድ ህዳር 11 ቀን 2009 ወደ ሳኡዲ አረቢያ አምርቶ የነበረ ሲሆን፣ በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል በተደረገው ውይይት ላይም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለሳኡዲ ተማጽኖ ቢጤ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኢኮኖሚያዊ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ቢሆንም፣ በተለይ ግን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መቀመጫውን በኤርትራ ባደረገው የአረብ ሀገራት ወታደራዊ ጦር ሰፈር ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተዋል ተብሏል፡፡
የየመንን የውስጥ ቀውስ ለመቅረፍ በሳዑዲ የሚመራው የአረብ አገሮች ጥምረት በኤርትራ ወታደራዊ ጦር ሠፈር መመሥረቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ ነገር ግን በዚህ ወታደራዊ ጦር ሠፈር አማካይነት የኤርትራ መንግሥትና መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያገኘ መሆኑ እንደሚያሳስባቸው በአቶ ኃይለማርያም የተመራው ልዑክ ለሳኡዲ ባለስልጣናት አስረድቷል፡፡ የኤርትራ መንግስት በዚህ የጦር ሰፈር ምክንያት በሚያገኘው ከፍተኛ ገንዘብ የተነሳ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ ሳኡዲም በዚህ ጉዳይ ላይ እንድታስብበት ተማጽኖ ቢጤ አቅርበዋል፡፡
ይህን ጉዳይ ለማስረዳት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናው የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ጨምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ሱፊያን አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛ አቶ ብርሃነ ገ/ክስቶስን ያካተተ ነበር፡፡ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በኤርትራ በከፈቱት የጦር ሰፈር፣ የአየር ኃይልና የባህር ኃይል ጦር ያቋቋሙ ሲሆን፣ ይህም ለኤርትራ መንግሥት እና ወታደራዊ ኃይሉ ትልቅ አቅም እየፈጠረለት እንደመጣ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአስር ቀናት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ላይ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በኤርትራ የከፈቱት የጦር ሰፈር ለኤርትራ መንግስት እና ወታደራዊ ኃይሉ አቅም እየፈጠረለት እንደመጣ ጠቅሶ፣ ይህም እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማራዘሙ ይታወቃል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ካሉት 15 አባል ሀገራት አስሩ የማዕቀቡን መራዘም ሲደግፉ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ግብጽ፣ አንጎላ እና ቬንዙዌላ ድምጸ ተዐቅቦ አድርገው ነበር፡፡ ኤርትራ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የተጣለባት ‹‹አልሸባብ ለተሰኘው አሸባሪ ቡድን ድጋፍ ታደርጋለች›› በሚል ምክንያት ሲሆን፣ በዚህ ማዕቀብ ስርም ላለፉት ስድስት ዓመታት ቆይታለች፡፡BBN
No comments:
Post a Comment