Thursday, November 10, 2016

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም


Bilderesultat for fasil yenealem esatአንዳንዶቻችን ዶናልድ ትራምፕን “ዘረኛ “ በማለት እያወገዝነው ነው፤ ዘረኝነትን መጸየፋችን ጥሩ ነገር ነው፤ ነገር ግን ዘረኝነትን ሌሎች ሲያራምዱት ብቻ ሳይሆን፣ እኛም፣ አውቀንም ሆነ ሳናውቀው ስናራምደው ልንጸየፈው ይገባል። እነሱ ሲያደርጉት እርኩስ መስሎ የታየን ነገር እኛ ስናደርገው ቅዱስ ሊሆን አይችልም። እውን ስንቶቻችን ነን የዘመናት የጋራ ታሪካችንን በመናድና የሌሉ ታሪኮችን በመፍጠር እርስ በርስ እንድንባላ ዘረኝነትን ነጋ ጠባ የምናቀነቅነው? ዘረኝነት የሚጀምረው ከአንደበታችን በሚወጡ ያልተገሩ ቃሎች ነው። ዶናልድ ትራምፕ ዘረኛ ሃሳቡን ወደ ተግባር ገና አልለወጠውም፣ ነገር ግን በልቡ ያለውን ተናግሮታልና ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያግደው ነገር ላይኖር ይችላል። ገና ሃሳቡን ወደ ተግባር ሳይለውጠው ውግዘት እየደረሰበት ያለውም ለዚህ ነው። ሂትለር ፣ ሙሰሎኒ ሌሎችም በርካታ የአለም አምባገነኖችና ጨፍጫፊዎች ስልጣን የያዙት ትራምፕ በመጣበት መንገድ ተጉዘው ነው። እነዚህ ገዢዎች ዘረኝነትን ቀስቀስዋል፣ ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸው ሃሳባቸውን ወደ ተግባር በመለወጥ በሰው ዘር ላይ ብዙ ውድመት አድርሰዋል። እስካሁን እንዳየሁት የትራምፕን ማሸነፍ በብቸኝነት የነቀፈች አገር ጀርመን ናት። ጀርመን የዘረኝነት ፖለቲካ ያመጣባትን እዳ ከማንም በላይ አይታዋለችና የትራምፕን መመረጥ ብትቃወም አይፈረድባትም። ህወሃትም ስልጣን የያዘው ዘረኝነትን አራግቦ ነው፤ ይኸው ታዲያ ዛሬ የዘረኝነትን አስከፊነት በቁማችን እያሳየን ነው። አሁንም በዚህ ዘረኛ አካሄድ ስልጣን ለመያዝ የሚቋምጡ አሉ። እነዚህ ሰዎች በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ መጨረሻው ጥፋት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። እነዚህ ሰዎች በትራምፕ ልብ ውስጥ ያለውን ዘረኝነት ብቻ ሳይሆን፣ በራሳቸው ልብ ውስጥ ያለውን ዘረኝነትም አይተው ራሳቸውን ሊያነጹ ይገባል። ይህ ካልሆነ ትርፉ ማስመሰል ነው። የዘረኝነት ህዋሱ ልባችን ውስጥ እንዳለ ለማወቅ ቀላሉ ዘዴ የምንናገረውንና የምንጽፈውን ማየት ነው።
ልብ በሉ! ዘረኝነትን መቃወም ዘረኝነት አይደለም፣ ዘረኝነትን መቃወም ዘረኝነት የሚሆነው ዘረኝነትን እየተቃወሙ ዘረኛ አስተሳሰብን ሲያራምዱ ከተገኙ ብቻ ነው።
ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም

No comments:

Post a Comment