አርብ ሕዳር 2 /1909 በደጋሚ የታሰረው የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት አምደኛ በፍቃዱ ኃይሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ለማስፈፀም በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እዝ ስር እንደሚገኘና የታሰረውም ለአሜሪካ ድምጽ በሰጠው ቃለምልልስ “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በሕዝቡ ላይ ጫና ያሳድራል” የሚል ይዘት ያለው ንግግር አድርገሃል ተበሎ እንደሆነ ለጠበቃውና ሊጠይቁት ለሄዱ ሰዎች መናገሩ ታውቋል።
ዋሽንግተን ዲሲ — የዛሬ ዓመት ከእስር የተለቀቀው የዞን ዘጠኝ የኢንተርኔት የጡመራ መድርክ አምደኛና የውይይት መጽሔት አዘጋጅ በፍቃዱ ኃይሉ በድጋሚ ከታሰረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። በፍቃዱ ኃይሉ አርብ ዕለት በአዲስ አበባ በተለምዶ ፈረንሳይ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ከሚገኘው የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ተወስዶ በአቅራቢያው ወደነበረው ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ የነበረ ሲሆን አሁን የዛኑ ዕለት ወደ ተዛወረበት የየካ ክፍለ ከተማ ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ስር እንደሚገኝ ጠበቃው አቶ አመሐ መኮንን ተናግረዋል።
በፍቃዱ ኃይሉ ዞን ዘጠኝ በተባለው የኢንተርኔት የጡመራ መድርክ ላይ በኢንተርኔት አምደኛነቱ ይታወቃል። በሚያዚያ ወር በ2007 እርሱና አምስት የኢንተርኔት አምደኞች ባሉበት ሌላዋ የኢንተርኔት አምደኛ ወ/ት ሶሊያና ሽመለስ በሌለችበት እንዲሁም ሦስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሽብር ወንጀል ተከሰው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ በመጀመሪያ አምስቱ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ሲለቀቁ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ሦስቱን እና ወ/ት ሶሊያና በሌለችበት ፍርድ ቤት በነፃ አሰናብቷቸው እንደነበር ይታወሳል።
በፍቃዱ ኃይሉን ግን አመጽ በጹሑፍ በማነሳሳት ክስ እዲከላከል ተበይኖበት በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የ20,000 ብር ዋስትና አሲዞ ከእስር እንዲፈታ ከሀገር እንዳይወጣ እገዳ ጥሎበት ነበር፡፡
በፍቃዱ ኃይሉ ከእስር ከተፈታ በኋላ ውይይት የተሰኘ መጽሔት ከጓደኞቹ ጋራ በማዘጋጀት በማሳተም ላይ ይገኝ ነበር። በፍቃዱ ከባልደረቦቹ የዞን ዘጠኝ የድረ ገጽ አምደኞች ጋር በጋራ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሽልማቶችን አግኝቷል። ችልድረንስ ኦፍ ዜር ፓረንትስ (የወላጆቻቸዉ ልጆች) በሚል ርእስ በጻፈዉ ልብ ወለድ መጽሐፍም በግሉ ከአራት ዓመታት በፊት የአፍሪካ የስነጽሑፍ ሽልማት ውድድር ተወዳደሮ ሦስተኛ በመውጣቱ ተሸላሚ እንደነበር ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment