አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም
ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ በጀመሩት የኦሽኒያ አካባቢ የወያኔን ሴራ ማክሸፍ አላማዉ ያደረገ እንቅስቃሴ በኒዉዚላንድ ዌሊንግተን ፓርላማ በመገኘት በዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዳይሬክተር በመካከለኛዉ ምስራቅ እና የአፍሪካ ከፍል ሃላፊ ከሆኑት የተክበሩ ስቲዋርት ሆርኒ ጋር 2 ሰዓት የፈጀ በአገራችን የወቅቱ ጉዳይና በኢትዮጵያና በኒዉዚላንድ አገር ስላለዉ ግኑኝነትን አስመልክቶ ከዛም በተጨማሪ በኒዉዚላንድ ለሚኖሩት ኢትዮጵያዉያን ወያኔ ካሰማራቸዉ ሰላዮችንና ሆድ አደሮችን በተመለከተ ዙሪያ ሰፊ የሆነ ዉይይት ያካሔዱ ሲሆን ዉይይቱም በተጠቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ እጅግ ዉጤታም እንደነበር ክስፍራዉ የደረሰን ዜና ያመላክታል።
በዚህ ዉይይት በርካታ የሆኑ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ የጠቀሱት አቶ ኦባንግ አሁን ያለዉ የሕዉሐት አስተዳደር ላለፉት 26 አመታት በአገራችን ዉስጥ ምንም ዓይነት የተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይኖር አጥብቆ የሠራበት መሆኑን ገልፀዉ በተለያየ ጊዜ ድርጅት አቋቁመዉ ለመንቀሳቀስ የሞከሩትን ከፊሉን በማሰር ከፊሉን በመግደል ከፊሉን እንዲሁ ከአገር እንዲሰደድ በማድርግ ስልጣኑን ያለተቀናቃኝ ለመያዝ እየሰራበት መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም እኩይ ምግባር የፀር ሽብር አዋጅ በማዉጣት ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ ወከባ በመፍጠር ከአገር እንዲሰደዱና ለሥራቸዉ ክብር ሰጥተዉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ወደ እስር ቤት በማስገባት የዜጎችን ነፃ አስተሳሰብ መገደብ እና ኢፍትሃዊ በመሆን አፍኖ ለመግዛት የሚሞክረዉ ሙከራ በማስተር ፕላን በተነሳዉ ተቃዉሞ በኦሮምያ ከዚያም የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ጨምሮ ዛሬ ላይ ከሕዉሐት ቁጥጥር ዉጭ የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በዚህ አጣብቂኝ ጊዜ ኢትዮጵያንና ሕዝቡን መርዳት ከሞራል አኳያ ግድ የሚል በመሆኑ ኒዉዚላንድም መርዳት በምትችለዉ ነገር ሁሉ መርዳትና ከሕዉሐት ጋር እያደረገች ያለዉን የኢኮኖሚ ስምምነት ለጊዜዉም ቢሆን ጋብ በማድረግ ከሕዝቡ ጎን መቆም እንዳለባቸዉም አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በአገር ዉስጥ ባለዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት እና ቀደም ብለዉ በወሰዱት የአሸባሪ አዋጅ መሠረት ተቃዋሚዉ ምንም መስራት እንደማይችል ቢታወቅም በዉጪ ያለዉን የኢትዮጵያ ሕዝብ በመርዳት ትግሉን መደገፍ መቻል እንዳለባቸዉም እንደ መፍትሔ ማቅረባቸዉም ታዉቋል። በተለይ ከአገራቸዉ ሲወጡ አሁን ያለዉን የሕዉሐት መንግስት ችግር አደረስብኝ በማለት ተሰደዉ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ተመልሰዉ አሰቃየን ላሉት መንግስት የስለላና በማሕበረሰቡ ዉስጥ ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ እንዳሉ በምስል የተደገፈ ማስርጃ በማቅረብ ለቀረበላቸዉም አቤቱታ ይህንን ጉዳይ አዉስትራሊያ ዉስጥም በተደረገዉ ሁኔታ ኢንፎርሜሽኑ እንዳላቸዉ በመጥቀስ ጉዳዩን በደንብ እንደሚከታተሉትና በቀላሉ እንደማያዩት ጠቅስዉ በኒዉዚላንድ የሚገኘዉ ማሕበረሰብም ጉዳዩን እየተከታተሉ ለሚመለከተዉ ክፍል ያለመታከት መስራት እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።
አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፅ ምክንያት ቁጥራቸዉ ትንሽ የማይባሉ የአበባ እርሻ መቃጠላቸዉ ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚነሳዉ በዚህ ኢንቨስትመንት አብዛኛዉን ተጠቃሚዉ ከዚሁ ስርዓት ጋር ትሥሥር ያላቸዉና የሥርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ካልሆኑ በስተቀር ሕዝብ ተጠቃሚ ያልሆነበት እና በሕብረተሰቡ ቁጭትን የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። ሕዉሐት ስልጣኑን ላለመልቀቅ በሚል ሰበብ ብቻ በሁለቱ ትልልቅ የአገሪቱ ዘዉጎች ከፍተኛ የሆነ የማጋጨት ሥራ እንደሚሰራም አስርድተዋል። ለዚህም የኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ሃላፊ የነበረዉ አቶ ጌታቸዉ ረዳ በሚዲያ ቀርቦ የአማራና የኦሮሞ ማሕበረሰብ እሳትና ጭድ ናቸዉ በማለት መናገሩን እና የሕዉሐት አስተዳደር ሃላፊነት የማይሰማዉ መሆኑንም በዝርዝር አስረድተዋል።
በማያያዝም የተከበሩ ስቷርት ሆርኒ የተደረገላቸዉን ማብራሪያ ካዳመጡ በኋላ በሰጡት መልስ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት መንግስታቸዉ እየተከታተለ መሆኑን እና አገራቸዉ ማድረግ የምትችለዉን ሁሉ ከማድረግ እንደማትቆጠብ አስረድተዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶም ከፓርላማ መልስ እሑድ November 13 2016 በ 56 ኪልበርኒ በሚገኘዉ የኮሚዩኒቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዉስጥ ከኢትዮጵያዊዉ ማሕበረሰብ ጋር በተደረገዉ ስብሰባ ከፓርላማ አባላት ጋር ስለነበረዉ ዉይይት ገለፃ በማድረግ እና በዉጭ ያለነዉ ኢትዮጵያዉያኖች ትግሉን በምን ዓይነት መደገፍ እንዳለበት እና መተባበርን በተመለከተ ስፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የዊሊንግተን ማሕበረሰብን ወክለዉ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ደጉ ባሰሙት ንግግር ትግሉን ወደ ኋላ ከጎተቱት ምክንያቶች በማለት በዋናነት የገለፁት ሕዝባዊ ተሳትፎ አለመኖሩን ሲሆን ይኽም የሆነበት ምክንያት
- ሕዝቡ በአገዛዙ ላይ ጥገኛ እንዲሆን ወያኔ አጥብቆ በመስራቱ
- የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማጥፋት እና የስለላ መረቡን በሰፊዉ በመዘርጋት ሕዝብን ማሸበር መቻሉ
- የዘር ጥላቻን በሕብረተሰቡ ዉስጥ በማስረፅ አንድነትን እንዲሸረሸር ለማድረግ የሞከረዉ ሙከራ ናቸዉ በማለት ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል።
በቀጣይም የክራይስት ቸርችን ኢትዮጵያዊ በመወከል ንግግር ያደረጉት ዶክተር አዲሱ ሲሆኑ በገለፃቸዉም ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚደረገዉን የወያኔን መሰሪ ምግባር አስመልክተዉ ቁጥራቸዉ ትንሽ የማይባሉ ኢትዮጵያዉያኖችን አስተባብረዉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጆን ኪ በርካታ ዶክመንቶችን በማያያዝ በፃፉት ደብዳቤ መሰረት አጥጋቢ ምላሽ ያገኙ መሆናቸዉን እና ከአካባቢያቸዉ ካለዉ ቀደምት የፓርላማ አባል ጋር ሌሎች ኢትዮጵያዉያኖችንም ጨምሮ ባደርጉት ስብሰባ እጅግ በጣም አመርቂ የሆነ ምላሽ ማግኘታቸዉንና ይህንንም በማስረጃ በማቅረብ በቀጣይም ይህንን ሁኔታ ከሌሎች ጋር በጋራ ሆነዉ የበለጠ እንደሚሰሩም ለተስብሳቢዉ ሲገልፁ አቶ መሳይም ኮሚኒቲዉም የሰራቸዉን ሥራዎች ለተሰብሳቢዉ ገልፀዋል። በመጨረሻም አቶ አለማየሁ ሽፈራሁ የእለቱን ፕሮግራም በወንድማዊ ምክር እና አንድነትን በሚያጠናክር ምክር ስብሰባዉን ሲያጠናቅቁ ስብሰባዉን በተሳካ እንዲጠናቀቅ ለተባበሩት የዌሊንግቶን የሴቶች ሕብረት ለኢትዮጵያ ምስጋናቸዉን በማቅረብ አጠናቀዉታል።
ክዚሁ ጋር በተያያዘ ዜናም ኒዉዚላንድ በደረሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በንብረት ላይ እና ትራንስፖርት መስመሮች ላይ አደጋ የደረሰ ቢሆንም በኒዉዚላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያኖች ላይ ምንም አይነት አደጋ እንዳልደረሰም ታዉቋል። –
No comments:
Post a Comment