Thursday, November 3, 2016

የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ምሥረታ መግለጫ


የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለፍትህ የሚያደርጉት ትግል እጅግ ወሳኝ ወደሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ሁላችንም የምንገነዘበዉ ነዉ፡፡ በሕወሐት ግፈኛ አገዛዝ ሥር ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት በሕዝቦቻችን ላይ የወረደዉ ግፍና መከራ ከልክ በማለፉ የተቀጣጠለዉና ላለፈዉ አንድ ዓመት ካለማቋረጥ የቀጠለዉ የእምቢተኝነትና የአልገዛም ባይነት ሕዝባዊ የተቃዉሞ ትግል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረስ መገለጫ ነዉ፡፡ በዚህ ዛሬም ድረስ እየተካሄደ ባለዉ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዳግም በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ትገኛለች፡፡
በአንድ በኩል መሠረታዊ የሆነ የሥርዓት ለዉጥ የሚፈልጉ ሕዝቦች እስከ አፍንጫዉ ከታጠቀ ጨካኝ የገዢ ቡድን ጋር የሞት ሽረት ትግል የሚያደርጉበት፤ በሌላ በኩል ሕወሐት መራሹ ቡድን በመሣሪያ ኃይልና በሕዝብ ሃብት ዝርፊያ ያገኛቸዉን ወታደራዊና የኢኮኖሚ የበላይነት ብቻ በመተማመን የሚቃወመዉን ሕዝብ በጅምላ እየጨፈጨፈ፣ እያሠረ እና ከአገር እያባረረ በገዢነት ሥልጣን ላይ ለመቆየት እየተንቀሣቀሰ ባለበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህን እጅግ አሣሣቢ የሆነ ሁኔታ ዝም ብሎ ማየት አይገባም ብለን የተነሣንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲመለሱ ለማድረግ በልዩ ልዩ መንገዶች እየታገልን ያለን የፖለቲካ ድርጅቶች እየተካሄደ ያለዉን ሕዝባዊ ትግል መልክ ለማስያዝና የኢትዮጵያ ጉዳይ ባለድርሻ የሆኑ ወገኖች ሁሉ የሚስማሙበትንና የሚሣተፉበትን የሽግግር ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችሉ ወሳኝ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችለንን የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ በመባል የሚታወቅ ንቅናቄ መሥርተናል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ራዕይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት፤ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መብት ሳይሸራረፍ የሚከበርበት፤ ባህላቸዉ፣ ታሪካቸዉና ማህበራዊ እሴቶቻቸዉ የሚንፀባረቁበት፤ ሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች በዜግነታቸዉ ተከብረዉ በህግ ፊት በእኩልነት የሚስተናገዱበት እና ዕድገትና ብልፅግና የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት ነዉ፡፡
የንቅናቄዉ ተልዕኮ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አስተባብሮ በአንድ አገራዊ ዓላማ ሥር በማሰባሰብ ከሕዝቦች ፍላጎት ዉጭ በጠመንጃ ኃይል የያዘዉን ሥልጣን በመጠቀም የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ተቋማት በበላይነትና በብቸኝነት የተቆጣጠረዉን አምባገነን ሥርዓት በተባበረ ሕዝባዊ ትግል አስወግዶ ዕዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት የሚለዉን የአገራዊ ንቅናቄዉን ራዕይ ከግብ ማድረስ ይሆናል፡፡
እኛ የዚህ አገራዊ ንቅናቄ መሥራቾች ከዚህ ትልቅ ዉሳኔ ላይ የደረስነዉ የአገሪቱን ዉስብስብ ችግሮች በመመርመር፣ ያለፉትን ጉዟችንን በመዳሰስ፣ የአገራችን የዛሬ ሁኔታ ብሎም የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ባሣሰባቸዉና ከየትኛዉም የፖለቲካ ድርጅት ወይም ቡድን ባልወገኑ ገለልተኛ ኢትዮጵያዉያን አደራዳሪነት ወራትን የፈጁ ግልጽ ዉይይቶችን፣ ምክክሮችንና ድርድሮችን ካደረግን በኋላ መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን፡፡ ስለሆነም በአገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ የተለመዱ አላስፈላጊ ትችቶችን እና ለሕዝቦቻችን ተጋድሎ ዉጤታማነት የማይጠቅሙ አፍራሽ አካሄዶችን ከወዲሁ ለማስቀረት ይቻል ዘንድ ይህ አገራዊ ንቅናቄ የሆነዉንና ያልሆነዉን ግልፅ አድርገን ማስቀመጥ እንወዳለን፡፡

1. የንቅናቄዉ መሥራቾች የሆንን ድርጅቶች ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንወክላለን የሚል አመለካከት የለንም፡፡ ነገር ግን ታዋቂ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለማካተት በእኛ በመሥራች ድርጅቶቹም ሆነ በአደራዳሪዎቹ ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻችን በኩል ያልተቆጠቡ ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ መሆናቸዉን ሳንገልፅ ለማለፍ አንፈልግም፡፡ የተገኘዉ ዉጤት ግን ዉስን ነዉ፡፡ ስለሆነም የሀገራችን ችግሮች ከቀን ወደቀን እየሰፉ ስለሄዱ፣ ሕዝቦቻችን አበክረዉ የሚጠይቁት የፖለቲካ ድርጅቶች ተባብሮ መንቀሳቀስ እስከዛሬ ከወሰደዉ ጊዜ የበለጠ መዉስድ ስሌለበት እና ወደምንፈልገዉ ግብ ለመድረስ የሚያስችለንን የጋራ እንቅስቃሴ ማድረግ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ እየሆነ ስለመጣ የዛሬዉ የጋራ ንቅናቄያችን ያለፉትን ስህተቶች በማይደግም መልኩ ከአንድ ቦታ ላይ መነሣት እንዳለበት በማመን ከታች ስማችን የተዘረዘረዉ አራት ድርጅቶች ይህን እርምጃ ለመዉሰድ ችለናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አገራዊ ንቅናቄዉ በሂደት ሁሉንም የሀገር ባለድርሻ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን ወገኖች እንዲያካትት ለማድረግ ያልተቆጠቡ ጥረቶችን ከማድረግ እንደማንቆጠብ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
2. የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄን የመሠረትነዉ ድርጅቶች በተለያየ መልኩ በሕዝባችን ዉስጥ ገብተን እየታገልን መሆናችን እንደተጠበቀ ሆኖ የተለያዩ የትግል ስልቶችን የምንከተል ነን፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ድርጅት ሌላዉ ድርጅት የመረጠዉን የትግል ስልት እንደማያወግዝና እንደማይቃወም በመግባባት ነዉ፡፡ ይህም ማለት የንቅናቄዉ መሥራቾች የሆንነዉ የፖለቲካ ድርጅቶች ፕሮግራሞቻችንን መሠረት በማድረግ የምንታገልለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይጠቅማሉ የምንላቸዉን የትግል ስልቶች በግል የመጠቀም ነፃነታችን የተጠበቀ እንደሆነ ተስማምተናል፡፡
3. ይህን የጋራ አገራዊ ንቅናቄ ስንመሠርት የኢትዮጵያን የሃያ-አምስት ዓመታት መከራ ለማስወገድና ለሕዝቦቻችን የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት እና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለመስጠት አሁን በሥልጣን ላይ ያለዉ የሕወሐት ገዢ ቡድን ከመሠረቱ መቀየርና ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚፈቅዱትና በሚስማሙበት ፍፁም አዲስ የሆነ ዲሞክራሲያዊ የፌዴራል ሥርዓት የመተካት አስፈላጊነት ለምንም ዓይነት ድርድር የማይቀርብ መሆኑን በመስማማት ነዉ፡፡
እነዚህን ሶስት ነጥቦች ከግምት ዉስጥ በማስገባት በአገራችን ጉደይ ላይ ባለድርሻ የሆኑ ወገኖች ሁሉ የሚስማሙበትንና አምነዉ የሚቀበሉትን የሽግግር ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ በተቀናጀ መልክ ለመሥራት የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄን መመሥረታችንን በይፋ ስንገልፅ የሕወሐት-መራሹ ቡድን ኢሰብዓዊ የሆኑ የግፍ ሥራዎችና የማንአለብኝነት አገዛዝ አንገፍግፏቸዉ ባዶ እጃቸዉን ዘመናዊ መሣሪያዎችን የታጠቀዉን ጨካኝ የገዢ ቡድን በመታገል ላይ ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተነሣንለትን ዓላማ ትክክለኛነት ተረድተዉ ከጎናችን እንደሚሰለፉ በመተማመን ነዉ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታችሁ የአገር ጉዳይ ባለድርሻ የሆናችሁ የፖለቲካ ደርጅቶች፣ ቡድኖችና ስብስቦች ዛሬ በአገራችን የመንግሥትን ሥልጣን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና የፀጥታ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ሕዝባችንን አፍኖና ጨቁኖ የሚገዛዉን የጥቂቶች ሥርዓት ለማስወገድ ተባብሮ መታገል ለነገ የሚባል ጉዳይ አለመሆኑን ተረድታችሁ በዚህ አዲስ አገራዊ ንቅናቄ ጥላ ሥር በመሰባሰብ አብረን እንድንታገል ወገናዊ ጥሪያችንን ደግመን ደጋግመን እናቀርብላችኋለን፡፡
ነፃነት፣ ዲሞክራሲ እና ፍትህ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች!! የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ መሥራቾች፡-
- የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ)
- የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ
- የአፋር ሕዝባዊ ፓርቲ
- የሲዳማ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ምሥረታ መግለጫ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለፍትህ የሚያደርጉት ትግል እጅግ ወሳኝ ወደሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ሁላችንም የምንገነዘበዉ ነዉ፡፡ በሕወሐት ግፈኛ አገዛዝ ሥር ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት በሕዝቦቻችን ላይ የወረደዉ ግፍና መከራ ከልክ በማለፉ የተቀጣጠለ...
OROMODEMOCRATICFRONT.ORG

No comments:

Post a Comment