በሃገር ውስጥ ተባብሶ የቀጠለውን የህዝብ አመጽ ለማፈን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ህዝብን እያተራመሰ ያለው ህወሃት በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ አመራር አካላትን፣የዘርፍ ሃላፊዎችንና አባላቱን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በጥብቅ ሚስጥር እያወያየ እንዳለ ታወቀ።
ከቅርብ ምንጮች በተገኘ መረጃ የስብሰባው ዋና አላማ በመላው ሃገሪቱ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ አዲስ አበባ እንዳይዛመትና ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወደሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ ለመከላከልና የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ በጥልቅ ተሃድሶ መንፈስ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለመምከር ነው ተብሎአል ። ኢህአደግ ከአባላቱ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ የጀመረው ይህ ስብሰባ ላለፉት 15 ቀናት ለሚዲያ ዝግ ሆኖ እየተካሄደ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን ስብሰባው ተጀምሮ እስኪያልቅ ከጠዋቱ አንድ ሰአት እስከምሽቱ አንድ ሰአት ድረስ ማንም ተሰብሳቢ ከስብሰባው ግቢ እንደማይወጣና ሞባይል ቴሌፎን ከመጠቀም እንደተከለከለ ተገለጾአል። በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከህዝቡ እየተደመጡ ያሉ ቅሬታዎችንና ብሶቶችን አጉልተው የገለጹ ቢሆንም መድረኩን ለመምራት የተላኩት ሰዎች ግን ሁሉ ነገር ከተረጋጋ በኋላ ሁኔታዎችን እናስተካክላለን ከሚል ድፍን ያለ ምላሽ ውጪ የረባ ነገር ማለት እንዳልቻሉ ታውቆአል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህብረተሰቡ ውስጥ ካሳደረው ቅሬታ በተጨማሪ ለረጅም ግዚ የህብረተሰቡ ችግር የሆኑ የመብራት እና የውሃ አቅርቦት አለመኖር ፣ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች ህዝቡን እያሸበሩ መሆናቸው በስብሰባው ላይ ቀርቦአል እንደ ምንጮቻችን መረጃ ።
በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የአዲስ አበባ አባላቱን በሚስጥር ያወያየው ኢህአደግ ከተሰብሳቢዎች በብዛት የቀረበለትን የህዝብ ብሶትና ጩኸት ሰምቶ እልባት ከመፈለግ ይልቅ በአረጀና በአፈጀ ስልቱ ጥልቅ ተሃዲሶ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ በመስበክ ይባስ ብሎ ላለፉት 25 አመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የድርጅቱን ህገ ደንብ እንደ አዲስ በዚህ ስብሰባ ላይ ለታደሙ አባላቱ ሲያስረዳ መታየቱ ብዙዎችን ተስፋ እንዳስቆረጠ ተያይዞ የደረሰን መረጃ አጋልጦአል።
ካለፈው አመት ህዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ የማስተር ፕላን ጥያቄን መነሻ በማድረግ ወደአማራ ክልልና ወደሌሎች የደቡብ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተስፋፋው ህዝባዊ አመጽ የነጻነትና የፍትህ ጥያቄዎችን በማንሳት ስርአቱን ፈተና ውስጥ የጣለው እንደሆነ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment