።።የእሳት አደጋ በሆሳዕና ማርያም ።።።
በቅርቡ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በኩል ጣና ሐይቅ ላይ በሚገኘው ጥንታዊው የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ውስጥ ተነስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በእግዚአብሔር ቸርነት በመጥፋቱ ሁላችን እጅግ ደስስ ብሎን የነበረ ቢሆንም እሳቱ እጁን አርዝሞ አሁን ደግሞ ወደ ደቡብ ክልል ወርዷል ።
በትናንትናው እለት ደግሞ ከወደ ደቡብ በሃድያና ስልጤ ሃገረ ስብከት ከሆሳዕና ከተማ የተሰማው ዜና እጅግ የሚያሳዝንም የሚያስቆጭም ነው። ለጊዜው የእሳቱ መንስኤ ባይታወቅም ከተመሰረተች 106 ዓመት የሆናት የታሪካዊቷ የሆሳዕና ደብረ ገነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በእሳት መውደሙን ከስፍራው የደረሰኝ በቪድዮ የተደገፈ መረጃ ያሳያል።
ጉዳዩን የበለጠ ለማጥራት እኔም የሀገረ ስብከቱን ዋና ስራ አስኪያጅ ክቡር ቆሞስ አባ ቢንያም ማንቾ እና የደብሯን አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቀሲስ አስናቀን በስልክ አግኝቼ አነጋግሬያለሁ ። ሁለቱም አባቶች የእሳት አደጋው መንስኤ አሁን ላይ እንዲህ ነው ብለን መናገር ባንችልም የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑ ግን ሚዛን እየደፋ በመሄዱ ግን ይስማማሉ ።
በተለይ የደብሯ አስተዳዳሪ እንደነገሩኝ ከሆነ ፤ ዕለቱ ቀዳሚት ሰንበት ፣ በዓሉም የእመቤታችን ወርሃዊ በዓል በመሆኑ ሥርዓተ ቅዳሴው በጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ተፈጽሞ እኛም ቤተክርስቲያኑን ዘግተን ቢሮ እንደተቀመጥን ፣ ምእመናንም ቤተክርቲያኗን ከብበው ጠበል ጻዲቁን እየቀመሱ ሳለ ነው ከቤተመቅደሱ ውስጥ እሳቱ ተነስቶ ሁሉም ተጯጩሆ ለማጥፋት ርብርብ የተደረገው ብለው አጫውተውኛል ።
የእሳቱን መነሳት ዐይተን የድረሱልን ጥሪ ደወል በመምታት እንዳሰማን ፣ ጭሱን እና ጥሪውን የሰሙ ሁሉ ዘር እና ሃይማኖት ሳይለዩ በሙሉ መጥተው በእሳት ማጥፋት እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፏል ።
እሳቱ ከባድ ጉዳት በቤተክርስቲያኗ ላይ አያድርስ እንጂ በቤተመቅደሱ ውስጥ ጽላቱ ምንም እንዳልሆኑ የደብሩ አስተዳዳሪ አክለው ነግረውኛል ። እግዚአብሔር ይመስገን ።
በቤተክርስቲያኗ ቅፅር ግቢ ውስጥ በተደረገው ጊዜያዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ ላይም የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያንና የእስልምና እምነት ተከታዮችና መሪዎች እንዲሁም የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ደገለ ኤርጌኖ ፣ የዞኑ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አበራ አይደሞና የከተማዋ ከተማ ከንቲባም በግንባር በመቅረብ በግላቸው አስተዋፅኦ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ እስከመጨረሻው በቤተክርስቲያኗ ሥራ ላይ በግላቸው ጭምር ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ብለውኛል እኒህ ሁለቱ የቤተክርስቲያን አባቶች አባ ቢንያም እና ቀሲስ አስናቀ ።
በሁኔታው ማዘን እና ማለቀሱ ብቻውን ዋጋ የለውም ። ይልቁንም ለተሻለ ሥራ እንድንነሳ ያስፈልጋል ።እናም በዚህ አጋጣሚ እኔ አንድ ኃሳብ በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን በትህትና አቀርባለሁ ።
።።።። ባለሙያዎች ።።።።
፩ኛ ፣ የቤተክርስቲያን ልጆች የሆናችሁና የአርክቴክቸር ሙያ ያላችሁ የቤተክርስቲያን ልጆች ግሩምና ድንቅ ታሪካዊ የሆነ ዘመን ተሻጋሪ የቤተክርስቲያን ዲዛይን በነፃ ብታዘጋጁ ።
።።።። ምእመናን ።።።።
፪ኛ፣ ይህን ዜና የሰማን እኛ በመላው ዓለም ያለን የቤተክርስቲያን ልጆች ሀብታም ድሃ ሳንል ሁላችን በአንድነትና በአጭር ጊዜ ውስጥ እግዚአብሔር ከሰጠን ውስጥ ያለንን ገንዘብ ብናዋጣ ፣
።።።። የደብሩ አስተዳደር ።።።።
፫ኛ፣ የደብሩ አስተዳደር ቤተክርስቲኗን መልሶ ለመገንባት ይቻል ዘንድ አንድ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ቢያዘጋጅ ። በአስቸኳይም የህንፃ አሰሪ ኮሚቴ አቋቁሞ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ይፋ ቢያደርግ ።
።።።። ማኅበራት ።።።።
በባለሙያዎች የተደራጀው የቤተክርስቲያናችን መመኪያ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ፈጣን የሆነ ምላሹን እንጠብቃለን ። የጉዞ ማኅበራት ያላችሁ ወንድሞች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መንገዶችን ሁሉ ወደ ሆሳዕና ማድረግ ይጠበቅባችኋል የሚል ሓሳቤን አቀርባለሁ ።
በእኔ በኩል የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛም ዝግጁም መሆኔን እገልፃለሁ ። ለጉባኤው መሳካት ይረዳ ዘንድ ወዳጆቼን ፣ እኔን ራሴን ጨምሮ ጓደኞቼን በማካተት ስፖንሰር በማፈላለግ ለቅድስት ቤተክርስቲያን እንድረስላት ።
ሆሳዕናዎች አይዟችሁ አለን ከጎናችሁ ። አበው " ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው እንዲሉ ፣ እኛም እንረባረብ ።
አሁን በደረሰኝ ዜና መሰረት ኮሚቴ እስኪቋቋም ድረስ ደብሩ በጊዜያዊነት ዝግ የባንክ አካውንት በሆሳዕና ከተማ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባቴና ቅርንጫፍ የባንክ ሂሳብ ተከፍቷል ። ቁጥሩም 1000110719969 እንደሆነ ይፋ ሆኗል ።
እኔ ይህን ብያለሁ እናንተም የምትሉትን በሉ በዚህ ጽሑፍ ላይ Comment አና Share ይበረታታሉ ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
የካቲት 22 /6/2007 ዓም
አዲስአበባ — ኢትዮጵያ
የካቲት 22 /6/2007 ዓም
አዲስአበባ — ኢትዮጵያ
No comments:
Post a Comment