ሳሞራ የኑስ በአየር ሃይል አባላት ላይ እየዛቱ መሆናቸው ተሰማ
መጋቢት ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አብራሪዎች ባለፉት 6 ወራት ከድሬዳዋ አየር ሃይል ግቢ ጠፍተው ተቃዋሚዎችን መቀላቀላቸውንና መሰደዳቸውን ተከትሎ ኢታማዦር ሹሙ ሳሞራ የኑስ በቀሪዎቹ ላይ የዛቻና የማስፈራሪያ ንግግሮችን በማድረግ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል ።
የአየር ሃይል ምንጮች እንደተናገሩት፦ጀነራሉ <<ከጠፉት የአየር ሃይል አባላት ጋር ግንኙነት ነበራቸው>>ያሏቸውንና <<ሊጠፉ ሲሉ ተያዙ የተባሉ ሌሎች የአየር ሃይል አባላትን>> ለቀሪዎቹ አባላት ሲያሳዩ ሰንብተዋል። ኢታማዦር ሹሙ ሰሞኑንም እነኚህኑ <<ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት አላቸው>> ያሏቸውን አባላት፦ ” የውስጥ ተቃዋሚዎች” ተያዙ በማለት በተለያዩ የአየር ሃይል ግቢዎች እያዞሩ በማሳየት ሌሎችን የአየር ሀይሉን አባላት ለማስፈራራት ሙከራ በማድረግ ላይ መጠመዳቸው ታውቋል።
እንደ ምንጮች ገለጻ፦ <<ሊጠፉ ሲሉ ተያዙ>> የተባሉ የተለያዩ የአየር ሃይል አባላት የእስረኛ ህጋዊ መብታቸው ተገፎ በሌሎች የአየር ሃይል አባላት ፊት ቀርበው እንዲሸማቀቁና ክብራቸው እንዲነካ መደረጉ፤ ብዙ የአየር ሃይል አባላትን አስቆጥቷል።
እነዚሁ የአየር ሀይል ምንጮች፤አብራሪዎቹ እውነት ተቃዋሚዎች ናቸው ቢባል እንኳ ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው፣ ታስረው ሰራዊቱ ፊት እንዲቀርቡ መደረጉ የአገዛዙን ባህሪ ያሳየነ ነው በማለት ለኢሳት ገልጸዋል።
የአየር ሃይል አባላት አምነውበት ማገልገል ሲገባቸው በማስፈራራት በሰራዊቱ ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚደረገው መኩራ ቁጣንና ቅሬታን ከማባባስ ውጭ የሚፈይደው ነገር እንደሌለም እነዚሁ የአየር ሀይል አባላት ተናግረዋል።
ጄ/ል ሳሞራ ከዚያም አልፈው ፦<<ኢሳት ኤርትራ ውስጥ ቃለ-መጠይቅ ያደረገላቸውን አብራሪዎችንና ቴክኒሻኖችን ይዘን እናመጣቸዋለን>> እያሉ ሲዝቱ እንደነበር፤ በግምገማ ተወጥረው የሰነበቱት የአየር ሃይል አባላት ተናግረዋል።
በአየር ሃይል አባላትና- በሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች መካከል መተማመን መጥፋቱን የሚናገሩት እነኚሁ የአየር ሀይል ባልደረቦች፣ በዚህም ምክንያት ጄ/ል ሳሞራና ሌሎች አዛዦች ግራ እንደተጋቡ አክለዋል።
በመጀመሪያ <<ምን እናድርግላችሁ?>> በሚል የማባበል ቃል መቀራረብ ለመፍጠር ቢሞክሩም ሰራዊቱ የሚያነሳው የመብት ጥያቄ በቀላሉ የሚመለስ ሆኖ ባለመገኘቱ ወደ ማስፈራራት መገባቱን የአየር ሃይል አባላቱ ይናገራሉ።
ግምገማውን ተከትሎ ቀደም ብለው ከጠፉ የአየር ሃይል አባላት ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ቁጥራቸው ከ7 የማያንስ የአየር ሃይል አባላት መታሰራቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment