በባለቤት አልባዋ ድሬዳዋ – መሬት በገፍ እየተቸበቸበ ነው (Gemeda Bona) ድሬዳዋ ባለቤት የሌላት አሰተዳደር ሆና ከፌዴራል መንግስት በTPLF ስራ አስፈፃሚ በቀጥታ ትዕዛዝ የምትተዳደር
ከተማ ናት:: ለምን በየአምስት ዓመታት ምርጫ በድሬዳዋ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ነገር የለም:: ምክንያቱም አሸናፊ (ኢህአዴግ – 114 ወንበሮች) እና ተሸናፊ (ሶህዴፓ – 75 ወንበሮች) በየሁለት አመት ተኩል ከተማዋን በፈረቃ ያስተዳድራሉ:: በጣም የሚገርመው “ኢህአዴግን ምረጡ መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው!” ብሎ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጎ ለአምስት ዓመታት ‘የተመረጠው’ ኢህአዴግ የማስተዳድራችሁ ለሁለት ዓመት ተኩል ብቻ ነው ማለቱ ከየት አገር ልምድ እንደወሰደ የሚያውቅ ካለ ለድሬዳዋ ህዝብ ቢያስረዳ መልካም ነው:: እ.አ.አ. 2007 በተደረገው የህዝብ ቆጠራ የድሬዳዋ አስተዳደር ካላት 342,827 ህዝብ ውስጥ 46.08% (157,991) የኦሮሞ ብሄር ሲሆን 24.24% (83,114) ደግሞ የሶማሌ ብሄር ናቸው:: በአስተዳደሩ ካሉት የገጠር ነዋሪዎች የኦሮሞ ብሄር 73.61% (80,949) ሲሆን የሶማሌ ብሄር ደግሞ 25.94% (28,531) ነው:: ሰፊው የአስተዳደሩ ገጠራማ ቦታ (73.61%) በኦሮሞዎች የተሞላውን ከምስራቅ ሃረረጌ ዞን መሬት ቆርሶ በመውሰድ ነው የድሬዳዋ አስተዳደር የተዋቀረው:: ይህ ሰፊ የኦሮሞ መሬት ከከተማዋ በስተሰሜን እስከ 50 ኪሎሜትር (መልካ ቄሮ) በስተደቡብ እስከ 17 ኪሎሜትር (ደንገጎ) እና በስተምዕራብ 10 ኪሎሜትር (መልካ ጀብዱ) በከተማዋ ክልል ውስጥ ይገኛሉ:: ምርጫ በመጣ ቁጥር አስተዳደሩ ካሉት 189 የከተማዋ ምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ ኢህአዴግ ለ114 ወንበሮች እና ሶህዴፓ ደግሞ ለ75 ወንበሮች በመወዳደር እንዲያሸንፉ ይደረጋል:: ሆኖም 60% የአስተዳደሩ ህዝብ ኢህአዴግን ቢመርጥም ከአምስት አመቱ ውስጥ ኢህአዴግ የሚያስተዳድረው ሁለት ዓመት ተኩሉን ብቻ ሲሆን የተቀረውን ሁለት አመት ተኩል ደግሞ 40% ወንበር ያለው ሶህዴፓ ያስተዳድራል:: መንግስት ለምን ለምርጫ በሚሊዮን የሚገመት ብር በየአምስት ዓመታት እንደሚያወጣና ኢህአዴግን ምረጡ እያለ የከተማዋንና የገጠሩን ህዝብ ቁም ስቅሉን እንደሚያሳይ ግራ የሚያጋባ ነው:: የድሬዳዋ ህዝብ በመረጥነው ፓርቲ እንተዳደር ብሎ ኢህአዴግን ቢጠይቅ ምን መልስ ይሰጠው ይሆን? ጥያቄውንና መልሱን ለድሬዳዋ ነዋሪዎችና ለኢህአዴግ ሰዎች ትቼ ሰሞኑን በመቸብቸብ ላይ ስላለው የድሬዳዋ መሬት ጉዳይ ላምራ:: ከላይ እንደተገለጠው በገጠሪቱ የድሬደዋ አስተዳደር የኦሮሞ ህዝብ (80,949 ህዝብ) በሚኖርበት ከከተማዋ እስከ 50 ኪሎሜትር ርቀት ድረስ የከተማዋ አካል ሲሆን ከድሬዳዋ ከተማ በ12 ኪሎሜትር ርቀት የምትገኘው የሺኒሌ ከተማ በሶማሌ ክልል ውስጥ በመካተት የሺኒሌ ወረዳ ተብሎ በሲቲ ዞን (በቀድሞው ሺኒሌ ዞን) ስር የተዋቀረ ነው:: በጣም የሚገርመው የሺኒሌ ወረዳ ዳር ድንበር ከድሬዳዋ ከተማ 50 ሜትር ርቀት መሆኑ ነው:: የሺኒሌ ወረዳ የመጨረሻ ድንበር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አጥር ነው:: ይህ ቦታ መርማርሳ ይባላል (በኦሞምኛ የቀጥታ ትርጉሙ ዙሪያ እንደማለት ነው):: ይታያችሁ ድሬዳዋ የኦሮሞን መሬት እስከ 50 ኪሎሜትር (መልካ ቄሮ) በእቅፋ ይዛ ከከተማዋ በ50 ሜትር ርቀት ላይ ያለውን የኦሮሞ መሬት ለሶማሌ ክልል በማድረግ የኦሮሞን መሬት መቸብቸብ ተጀመረ:: ባሳለፍነው ሳምንት መርማርሳ (ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ጎን) ሄጄ ያየሁት ሁኔታ ነው ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ:: በመርመርሳ 500 ካሬ ሜትር ለቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ ከብር 100,000 እስከ ብር 130,000 እየተቸበቸበ ነው:: የሚገርመው ደግሞ የስም ማዛወሩ ሂደት በሁለትና ሶስት ሰዓታት ውስጥ በ12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሺኒሌ ከተማ ለሶማሌ ክልል መንግስት ብር 4,000 በመክፈል ካርታና ፕላን መሬት ገዠዎች እየተረከቡ ነው:: መሬቱን የሚሸጡትና ገንዘቡን የሚረከቡት ሁሉም የሶማሌ ብሄር አባላት ሲሆኑ የሚገዙት ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው:: በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሌ ብሄረሰብ አባላትን በኢኮኖሚ ለመጥቀም ታስቦ ለዚሁ ብሄር አባላት ተሸንሽኖ የታደለውን መሬት ለመግዛት የምትሹ በሞባይል ቁጥር +251 939600211 (አቶ ሃሰን) ብላችሁ ብትደውሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለ 500 ካሬ ሜትር የኦሮሞ መሬት ለቤት መስሪያ ቦታ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ጎን (መርማርሳ) ታገኛላችሁ:: ጎበዝ የኢህአዴግ ህገ መንግስት መሬት አይሸጥም አይለወጥም ይላል:: መርማርሳ (ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ጎን) ያለውን መሬት ህገ መንግስቱ አያውቀውም ማለት ነው? ለማንኛውም ለአቶ ሃሰን (+251 939600211) ደውላችሁ የ500 ካሬ ሜትር ባለቤት መሆን ትችላላችሁ በባለቤት አልባዋ – ድሬዳዋ:: Show less
No comments:
Post a Comment