አገራችን ኢትዮጵያ በጎጠኛና ዘረኛ ቡድን መዳፍ ስር ወድቃ ህዝቦቿ ከመቼውም እጅግ የከፋ የመከራና ስቃይ ፅዋ እየጠጡ ተዋርደውና ተንቀው በመኖር እነሆ 25 የግፍ አመታት ተቆጠሩ፤ ዘረኛውና አምባገነኑ ቡድን ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ማህበራዊ እሴቶችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ በማንአለብኝነት፣ ቅጥ በአጣ ትምክህትና አረመኔያዊነት በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ሂትለራዊና ፋሽስታዊ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል።
ይህ አይነት ዘረኛ ቡድን በማነኛውም መለኪያ እንዲሁም ታሪካዊ ዳራ ኢትዮጵያን ያክል ታላቅ ታሪክ ያላት ሀገር ለማስተዳደርም ሆነ ለመምራት ፈጽሞ ብቃትና ሞራል እንደሌለው ከፈጸማቸውና ከሚፈጽማቸው እኩይ ተግባር በተጨባጭ ለማየት ችለናል፤ በድርጊቱም እጅግ አዝነናል፣ ተቆጭተናል፣ የበለጠ እልህ ውስጥም ገብተናል። ይህም የወያኔ አረመኔያዊነት በቅርቡ በአገራችን ተቀጣጥሎ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ህዝባዊ እምቢተኝነት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
እንደ አገዛዙ ሥርዓት የፖለቲካ ዓለማና ግብ ኢትዮጵያዊያን በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለው እርስ በእርስ እየተጋጩና እየተናቆሩ ለአገዛዙ የሥልጣን ማራዘሚያ የሚጠቀምበት ከንቱ ስልት ተዳክሞ የአንድነት ኃይሉ ተጠናክሮ በጋራ የኢትዮጵያ ታላቅ ጠላት በሆነው በወያኔ ሥርዓት ላይ በቁርጠኝነት እንዲነሳ ጊዜ የማይሰጠቅ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህን የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ስልት ከመጨረሻው ግብ ለማድረስ የተያዘው የነጻነት ትግል ለውጤት እንዲበቃ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ዋና ሃሳብ በመያዝ ሁሉም ለኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲ መስፈን፣ ዲሞክራሲያዊና ሰባዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ህዝባዊ ተቋማትና የእያንዳንዳችን እንደግለሰብ ልናበረክት የሚገባን አስተዋጾ ላይ ለመምከር ይህ ዛሬ የተጠራው ህዝባዊ ውይይት እጅግ ጠቃሚ ወቅታዊ ጉዳዮችና የመፍትሄ ሃሳቦች የተነሱበት፣ ከፍተኛ የትግል መነቃቃትና አብሮነት የተንጸባረቀበት ነበረ።
የተጀመረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ከጫፍ ደርሶ አረመኔያዊ አገዛዝ ከህዝባችን ጫንቃ አውርደን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ሁለገብ እንቅስቃሴ አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ከቀረቡ የውይይት ርዕሶች፣ ነጥቦችና በተሳታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶችና የሃሳብ ልውውጦች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ተችሏል። በተጋባዥ እንግዶች በዶ/ር ሙሉዓለም አዳም፣ በዶ/ር ተክሉ አባተ እና ወጣት ኤልሳቤጥ ግርማ የቀረቡ የመወያያ ነጥቦችም በሚገባ ወቅቱን ያገናዘቡና የታለመላቸውን ግብ ማሳካት እንደሚችሉ ከውይይቱ በአጽንኦት ተረድተናል።