Monday, September 26, 2016

የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ቀውስ አስመልክቶ ከአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር መወያየታቸው ተገለጸ ኢሳት (መስከረም 16 ፥ 2009)


Bilderesultat for hailemariam desalegnበኦሮሚያና አማራ ክልል እየተከሰተ ባለው ህዝባዊ እምቢተኝነትና እሱን ተከትሎ የመጣው አለመረጋጋት በአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ላይ ስጋት መፍጠሩን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሃላፊ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ገለጹ። ችግሩ በሚፈታበት ሁኔታ ከአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር መነጋገራቸውንም የአሜሪካን አቋምን በሚተነትነው ርዕሰ አንቀጽ አስፍረዋል።

ኒውዮርክ እየተደረገ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሃላፊ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ-ግሬንፊልድ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ እጅግ ከባድ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዋዋሚዎች ጋር የሰላም ንግግር እንዲጀምሩ ሲያበረታቱ እንደነበር የገለጹት ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት እንዲኖር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲያንሰራሩ፣ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱና በተመሳሳይ ጉዳዮች ከአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ላይ መነጋገራቸውን አመልክተዋል።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው አለመረጋጋት ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል እንደሚረዳ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ችግሮቹ ካልተፈቱ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ እየተባባሰ ሄዶ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል እንደሚገነዘቡ ባለስልጣኗ መናገራቸው ተመልክቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ሊሳተፉ ከመጡት ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በጎንዮሽ ተገናኘተው በጉዳዩ ላይ እንደተወያዩ የገለጹት ሊንዳ ቶማስ-ግሬንፊልድ፣ የአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መንግስት ችግሩን በጥልቀት መርምሮ ዕልባት እንዲሰጠው እንዳበረታቷቸው መናገራቸውን ገልጸዋል።
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰተ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በቅርቡ ዕልባት ካላገኘ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሻገር እንደሚችል ሚስ ሊንዳ-ቶማስ ግሪን ፊልድ ማሳሰባቸው ተመልክቷል።
ከሶስት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በተቃዋሚዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው አደገኛ እርምጃ መንግስታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሣሰቡንና  በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ  መጠየቃቸውን በተመድ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛና የፕሬዚዳንት ኦባማ ካቢኔ አባል የሆኑት አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በጁባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ሲገልጽ ቢቆይም፣ ስለጉዳዩ አሳሳቢነት በተደጋጋሚ ሲናገር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተሰናባች አምባሳደር ፓትሪሽያ ሀስላክ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ያለህግ እንደሚታሰሩና የኤምባሲው ሠራተኞች ጭምር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነገር እንደሚፈሩ መናገራቸው አይዘነጋም።
ከአሜሪካ መንግስት በተጨማሪ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከወራት በፊት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ማጣራት እንዲደረግበት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት ቢጠይቅም በኢትዮጵያ መንግስት እምቢተኝነት ሳይሳካ መቅረቱን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment